[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ከወራት በፊት የአልጄሪያውን ክለብ ጄኤስ ካቢሊ ተቀላቅሎ የነበረው ኢትዮጵያዊው አጥቂ ሙጂብ ቃሲም ከክለቡ ጋር ተለያይቷል?
በሲዳማ ቡና በተከላካይ መስመር በመጫወት ብዙሃኑን የስፖርት ቤተሰብ የተዋወቀው ሙጂብ ከዛም ወደ ሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ በማምራት በኢትዮጵያ እግርኳስ ስሙን ከፍ እንዳደረገ ይታወቃል። በተለይ በዐፄዎቹ ቤት ሦስት ተከታታይ ዓመታትን ድንቅ ብቃቱን በማሳየት የሊጉንም ዋንጫ ከፍ አድርጎ እንደነበር አይዘነጋም። ከወራት በፊት ደግሞ ከሰሜን አፍሪካው ክለብ ጄኤስ ካቢሊ የእናስፈርምህ ጥያቄ ቀርቦለት ከፋሲል ጋር የነበረውን የአንድ ዓመት ውል አቋርጦ ወደ አልጄሪያ ማምራቱ የሚታወስ ነው።
በአልጄሪያ ሊግ እስካሁን ሦስት ጨዋታዎችን (አጠቃላይ 108 ደቂቃ) ብቻ ያደረገው ተጫዋቹ (ሁለቱን ተቀይሮ በመግባት) ከክለቡ ጋር ሊለያይ እንደሚችል መረጃዎች ሲደርሱን ነበር። አሁን ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ደግሞ መረጃዎቹ ልክ ሆነው ግዙፉ አጥቂ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰ ሲሆን ከክለቡ ጋር ውሉን ሙሉ ለሙሉ ማቋረጡንም ለማወቅ ችለናል። ጄኤስ ካቢሌም በእርሱ ምትክ የቡርኪና ፋሶ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ላሚን ኦታራን በማስፈረሙ በቦታው ሰው ተክቷል።
ክለቡ እና ሙጂብ ውላቸውን ለማቋረጣቸው በርከት ያሉ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ የሚገኘው ተጫዋቹን አግኝተን እንደጠየቅነው ክለቡ የሦስት ወር ደሞዝ ስላልከፈለው መለያየቱን ጠቁሞናል። የተጫዋቹ ቀጣይ ማረፊያንም እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን እንገልፃለን።