ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

11ኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ በደረሰው ፕሪምየር ሊጉ በዚህኛው ሳምንት የታዘብናቸው ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮች የተዳሰሱበትን ፅሁፍ አነሆ።

👉ጅማ አባ ጅፋር ግቦችን ማስቆጠር ጀምሯል

በሊጉ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከድል ጋር የታረቁት ጅማ አባ ጅፋሮች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ አራት ግቦችን በአንድ ጨዋታ በማስቆጠር የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድል ማስመዝገብ ችለዋል።

ሀዲያ ሆሳዕናን በረቱበት ጨዋታ በተጋጣሚያቸው አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶባቸው እንዲሁም ወደ ራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ተገፍተው አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ ቢያሳልፉም በመልሶ ማጥቃት ግን የሚቀመሱ አልነበሩም።

በተለይም ከመሀል ሜዳ ከሚነሱ እና በይበልጥ ፈጣኖቹ መሀመድኑር ናስር እና እዮብ አለማየሁን ታሳቢ ባደረጉ የተመጠኑ ኳሶች መነሻነት ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ተደጋጋሚ ስጋቶችን ሲደቅኑ ተስተውሏል ፤ ሁለቱ ተጫዋቾችም አራቱን ግቦች ዕኩል ዕኩል ተካፋለዋቸዋል።

በሊጉ የአስር ሳምንታት ጉዞ በድምሩ ሦስት ግቦችን ብቻ አስቆጥረው የነበሩት ጅማ አባ ጅፋሮች በአስራ አንደኛ የጨዋታ ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕና ላይ አራት ግቦችን በማስቆጠር በውድድር ዘመኑን ያስቆጠሩትን የግብ ብዛት ከእጥፍ በላይ በማሳደግ ነጥባቸውን በ15ኛ ደረጃ ከሚገኘው ሰበታ ጋር ሲያስተካክሉ በግብ ዕዳም ብቻ በአንድ ተበልጠው በነበሩበት 16ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።

የሊጉ ውድድር ወደ ድሬዳዋ ከማምራቱ በፊት በአንድ ነጥብ እና በአስራ አራት የግብ ዕዳ የሰንተረዡ ግርጌ ላይ የነበሩት ጅማዎች ድሬዳዋ ከተማ የተስማማቸው ይመስላል ፤ በድሬዳዋ ስታዲየም እስካሁን ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች ድል በማድረግ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ እስተንፋሳቸው መሰማት ጀምሯል።

👉የባህር ዳር ከተማ ደካማ መከላከል

በመጨረሻዎቹ ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት ባህርዳር ከተማዎች በተለይ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች የተመለከትንባቸው የመከላከል ድክመት ቡድኑ በአፋጣኝ ሊያርመው ካልቻለ ቡድኑን ዋጋ እንዳያስከፍል የሚያሰጋ ነው።

መከላከል አጥቂ እስከ ግብጠባቂ በጋራ የሚከወን ነው ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ የተሰናሰለ የመከላከል መዋቅር ለየትኛውም ውጤታማ ለመሆን ለሚያስብ ቡድን አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሆነም ይታመናል።

ጥሩ የመከላከል መሰረት መገንባት ጨዋታዎችን ከማሸነፍ ባለፈ ቢያንስ በጨዋታዎች ላለመሸነፍ ከመርዳቱ አንፃር ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጠዋል ፤ ታድያ በዚህ የመከላከል መዋቅር ግንባታ ውስጥ የመሀል ተከላካዮች ተግባቦት እና ውህደት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከኃላ አራት ወደ ሶስት የመሀል ተከላካዮችን ጥቅም ላይ ማዋል ከጀመሩ ጥቂት የማይባሉ የጨዋታ ሳምንታት አልፈዋል ነገርግን በዚህ ሂደት ቡድኑ በተለይ ከጨዋታ ጨዋታ የሚታይ መሻሻሎችን በተለይ በመከላከሉ ወቅት እየተመለከተንበት እንገኝም።

በጊዮርጊስ በተሸነፉበት ጨዋታ ሁለቱ ግቦች የተቆጠሩበት መንገድ በመከላከሉ ረገድ ጥያቄ እንዲነሳ የሚያስገድዱ ናቸው ፤ በመጀመሪያው ግብ የቡድኑን ያልተደራጀ የመከላከል ሂደት በግልፅ የሚያሳይ የነበረ ሲሆን ከመሀል ተከላካዮቹ የመነሻ ቦታ አያያዝ እና የቁጥር ብልጫ ኖሯቸው እንኳን የነበራቸው ያልተቀናጀ የመከላከል ሂደትን የታዘብንበት ሲሆን በሁለተኛው ግብ ሂደት ውስጥ በፈቱዲን ጀማል እና ሰለሞን ወዴሳ መካከል የነበረው የተግባቦት ችግር በግልፅ የተመለከተንበት ነበር።

ሁለቱን ግቦች ለአብነት ለማሳያነት አነሳን እንጂ ከዚህ ባለፈም በተለይ በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች የመስመር ተመላላሾች በተለይ በመከላከል ሽግግር ወቅት እንዲሁም በመከላከል አደረጃጀት ወቅት ያላቸው የሁኔታዎችን የመገንዘብ እና የቦታ አያያዝ ደካማ መሆኑ በግቦቹ ሂደት ሆነ በሌሎች የጨዋታ ቅፅበቶች በስፋት እየተመለከትን እንገኛለን ፤ በተጨማሪም የተከላካይ መስመሩን ወደ መሀል ሜዳ የማስጠጋት ፍላጎት ያለው ቡድን ከፊት ያሉት ተጫዋቾች ግን በሚገባ ተጋጣሚ ተጫዋቾች ላይ ጫና ማሳደር ባለመቻላቸው በተደጋጋሚ በረጅሙ ከመከላከል መስመራቸው በስተጀርባ በሚጣሉ ኳሶች እየተቸገሩ ይገኛል በመሆኑም ቡድን በሰንጠረዡ አናት ለመፎካከር ያለውን ህልም እውን ለማድረግ እነዚህን የመከላከል ክፍተቶችን መቅረፍ ይገባዋል።

👉በመጨረሻ ደቂቃ ያሸነፉት ሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ

በመጨረሻዎቹ ሽርፍራፊ ሰከንዶች የሚቆጠሩ ግቦች እግርኳስ ከምንወድባቸው ምክንያቶች አንዱ ናቸው ፤ የዘጠና ደቂቃ ልፋት በመጨረሻ ሰከንድ በሚቆጠሩ ግቦች መና ሲቀሩ እንዲሁም ብዙ ያልተጠበቁ ነገሮች በመጨረሻ ሰከንዶች ሲሆኑ በእግርኳስ ተመልክተናል።

የሀገራችን እግርኳስ ግን በዚህ ረገድ የጨዋታ ውጤቶች በዚህ ደረጃ እስከመጨረሻው ሰከንድ ሲያመሩ ግን ብዙ አንመለከትም ፤ ነገርግን በዚህኛው የ11ኛ የጨዋታ ሳምንት ሶስተኛ ቀን ውሎ የተመለከትናቸው ጨዋታዎች ውጤት ግን መደበኛው ደቂቃ ከተጠናቀቀ በኃላ በተሰጡ ተጨማሪ ደቂቃዎች የተወሰኑ ነበሩ።

በ9 ሰአቱ ጨዋታ ወላይታ ድቻ እና አዲስአበባ ከተማ 1-1 ሆነው መደበኛው ዘጠና ደቂቃ ቢጠናቀቅም በ90+4ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም ከማዕዘን ከተሻማ ኳስ የተገኘችውን ኳስ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ለወላይታ ድቻዎች ጣፋጭ ሶስት ነጥብ አስገኝቷል።

የምሽቱ ጨዋታ ላይ የሆነው ደግሞ ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ነበር ፤ ድሬዳዋ ከተማን ከሀዋሳ ባገናኘው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ በሁለት አጋጣሚዎች በ17ኛው እና በ78ኛው ደቂቃ በተቆጠረ ግቦች መምራት ቢችሉም ሀዋሳ ከተማዎች በስምንት እና በአምስት ደቂቃዎች ልዮነት አቻ መሆን ችለዋል።

በተለይ በ84ኛው ደቂቃ መስፍን ታፈሰ ባስቆጠራት ግብ ይበልጥ የተነቃቁት ሀዋሳ ከተማዎች በአቻ ይጠናቀቃል ተብሎ በተጠበቀው ጨዋታ 90+1ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት አውሽ ከማዕዘን ምት መነሻዋን ያደረገችን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ትልቅ ትርጉም ያለውን ድል ለቡድኑ ማስገኘት ችሏል።

ከሁለቱም አስደናቂ የመጨረሻ ደቂቃዎች ድራማዊ ክስተቶች በስተጀርባ የተመለከትናቸው ጠንካራ የማሸነፍ ፍላጎት እና እስከመጨረሻው ደቂቃ ያለን ሁሉ ለቡድን የመስጠት ቁርጠኝነት በጣም የሚደነቅ እና በሊጋችን በስፋት ልንመለከተው የሚገባ የጨዋታ ወቅት ስነልቦናዊ ዕሴቶች ናቸው።

👉አስገራሚው የሰበታ ከተማ የመጀመሪያ 11

በ8ኛ የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ከረቱ ወዲህ በተከታታይ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት ሰበታ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማን ሲገጥሙ የተጠቀሙበት የመጀመሪያ 11 አሰገራሚ ስብጥር የነበረው ነበር።

በጨዋታው ሰበታ ከተማዎች በመጀመሪያ 11 ስብስባቸው ይፋ ሲያደርጉ ሰባት ተፈጥሮአዊ ተከላካዮችን በአንድ ላይ ለጨዋታው በመጀመሪያ ተሰላፊነት መሰየም ችለዋል ፤ በዚህም 4-5-1 በሚመስል የተጫዋቾች አደራደር በተለይ የፋሲል ከነማን የመስመር ሆነ መሀል ለመሀል የሚደረጉ ጥቃቶችን ለመመከት ጥረት አድርገዋል።

ከላይ በጠቀስነው ቅርፅ ታፈሰ ሰርካ ፣ አንተነህ ተስፋዬ ፣ በረከት ሳሙኤል እና አለማየሁ ሙሉታ አራቱ ተከላካዮች ሲሆኑ ከእነሱ ፊት ደግሞ ጌቱ ሀይለማርያም ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና ሃይለሚካኤል አደፍርስ አምስቱ አማካዮች ሲሆን የአጥቂ መስመሩን ዘካርያስ ፍቅሬ በብቸኝነት ለመምራት የተመረጠው ተጫዋች ነበር።

በጨዋታውም በቀኝ እና ግራ መስመሮች በኩል ሰበታዎች በሁለት የመስመር ተከላካዮች ማለትም ታፈሰ ሰርካ እና ጌቱ ሃይለማርያም ከበረከት ደስታ መነሻቸውን ያደረጉ ጥቃቶችን በተቃራኒ አቅጣጫ ደግሞ አለማየሁ ሙለታ እና ሃይለሚካኤል አደፍርስ ሽመክት ጉግሳ የሚደቅነውን ስጋት ለማስቀረት ጥረት ያደረጉ ሲሆን መሀል ለመሀል ያለውን ጥቃት ደግሞ በመሀል ተከላካዮ ወልደአማኑኤል ጌቱ የሚመራው የሶስት ተጫዋቾች ጥምረት ለመመከት ሲጥር ተስተውሏል።

ይህም ጥረታቸው በተለይ በክፍት ጨዋታ ፋሲል ከነማዎች እንደከዚህ ቀደሙ ዕድሎችን እንዳይፈጥሩ በማድረግ ረገድ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ውጤታማ ነበር ፤ ነገርግን በክፍት ጨዋታ ጥሩ ሲከላከል የነበረው ቡድኑ በሶስት አጋጣሚዎች የቆሙ ኳሶችን በአግባቡ መከላከል ባለመቻላቸው ሶስት ግቦችን አስተናግደው ለመሸነፍ በቅተዋል።

በውጤት ደረጃ ከመዘነው የተጫዋቾች ምርጫቸው ሆነ የጨዋታ ዕቅዳቸው ውጤታማ ባይመስልም በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ፋሲሎች በክፍት ጨዋታ በሚፈልጉት ደረጃ የግብ እድሎችን መፍጠር አለመቻላቸው በተወሰነ መልኩ ለጥረታቸው ዕውቅና መስጠት ተገቢ ይመስላል።

👉 መከላከያ ከቆይታ በኋላ አሸንፏል

ዘንድሮ ከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው መከላከያ አጀማመሩ መልካም የሚባል ነበር። ከመጀመሪያዎቹ አምስት ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት ብቻ አስተናግዶ የነበረው ጦሩ አስር ነጥቦችን በመሰብሰብ ዓመቱን በጥሩ ተፎካካሪነት እንደሚቀጥል ምልክት ሰጥቶ ነበር።

ቀጣዮቹ የጨዋታ ሳምንታት ግን ለአረንጓዴ እና ቀይ ለባሾቹ መልካም አልሆኑም። በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ይጠቀምባቸው ከነበሩ ተጫዋቾች ውስጥ በቅጣት እና በጉዳት ለውጦችን ለማድረግ እየተገደደ እና በወጣት ተጫዋቾቹ ላይ ኃላፊነቱን እያከበደ የመጣው ቡድኑ ለተከታታይ አምስት ሳምንታት ድል ከማስመዝገብም ሆነ ግብ ከማስቆጠር ለመራቅ ተገዶ ነበር። አንድ ነጥብ ብቻ ባገኘባቸው በእነዚህ ሳምንታት ያሳየው ደካማ አቋም ወደ ወራጅ ቀጠናው ሲገፋው በቶሎ ማገገም የሚችልም አይመስልም ነበር።

ይሁን እንጂ በ11ኛው ሳምንት ወልቂጤ ከተማን 3-1 የረታበት መንገድ ለቀጣይ ጉዞው ስንቅ የሚሆን ዓይነት ነበር። በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ግብ ቢያስተናግድም ከኋላ ተነስቶ ሙሉ ውጤት ማሳካቱ ፣ እንደተሾመ በላቸው ያሉ ወጣት ተጫዋቾቹ አንፀባርቀው መታየታቸው መከላከያ ቢያንስ ከአደጋው ክልል ርቆ ለመጨረስ አቅሙ እንዳለው ፍንጭ የሰጠ ሆኖ አልፏል። ይህ እንዲሳካ ግን ቡድኑ አሁንም በወጥነት ጥሩ ብቃቱን በማስቀጠል እንዲሁም የመከላከል ስህተቶችን ቀንሶ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከሚሰለፉ ተጨዋቾቹ እና ከክፍት ጨዋታም ግቦችን ማግኘት መቻል ላይ አብዝቶ ሊሰራ የግድ ይለዋል።