[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በ11ኛ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች የሁለተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።
👉 የግብ ጠባቂዎች ስህተት መበራከት
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከወትሮው በተለየ በርከት ያሉ የግብ ጠባቂዎች ስህተቶችን ተመልክተናል። በጨዋታ ሳምንቱ አምስት ግቦች በቀጥታም ሆነ በተዋዋሪ ግብ ጠባቂዎች በሰሯቸው ስህተቶች የተገኙ ናቸው።
ሶሆሆ ሜንሳ ሀዲያ ሆሳዕና በጅማ አባ ጅፋር 4-2 በተሸነፈበት ጨዋታ መሀመድኑር ናስር ያስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ስትቆጠር በላይ አባይነህ ከሳጥን ውስጥ የመታትን ኳስ ተቆጣጠረው ሲባል በእግሩ መሀል ኳሷ መሽለኳን ተከትሎ መሀመድኑር ወደ ግብነት ቀይሯታል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ባህርዳር ከተማን 2-0 በረታበት ጨዋታ የባህር ዳሩ የግብ ዘብ አቡበከር ኑሪ የቡድን አጋሩ ወደ ኋላ ገጭቶ የሰጠውን ኳስ ቀልቦ ወደ መሬት ሲያርፍ ኳሷ ከእጅ መውጣቷን ተከትሎ በቅርብ ርቀት ሆኖ ያገኛት ከነዓን ማርክነህ ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል።
ፋሲል ከነማ ሰበታን 3-0 በረታበት ጨዋታ የመጀመሪያዋ የማዕዘን ምት ግብ ስትቆጠር የለዓለም ብርሃኑ የቦታ አጠባበቅ ስህተት የታከለበት ነበር።
ወላይታ ድቻ አዲስ አበባ ከተማን በረታበት ጨዋታም እንዲሁ የአዲስ አበባ ከተማ የአቻነቷ ግብ ስትቆጠር ወንድወሰን አሸናፊ ሳይጠቅ ኳሱ በእግሮቹ መሀል የሾለከበት መንገድ እና ወልቂጤ በመከላከያ 3-1 በተረታበት ጨዋታ የኤርሚያስ ኃይሉ ግብ ስትቆጠር ሰዒድ ሀብታሙ የሰራው ስህተት በሳምንቱ የተመለከትናቸው ወደ ግብነት የተቀየሩ የግብ ጠባቂዎች ስህተት ናቸው።
እግርኳስ የስህተቶች ስፖርት እንደመሆኑ ዝቅተኛውን ስህተት የፈፀመው ቡድን ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ እንመለከታለን። ነገር ግን በተለይ ግብ ጠባቂዎች የሚሰሯቸው ስህተቶች መልሶ የመታረም ዕድላቸው ጠባብ መሆኑን ተከትሎ ብዙ ጊዜ የግብጠባቂዎች ስህተት ጎልቶ ሲነገር እናስተውላለን።
በእኛ ሀገር አውድ ግን በጨዋታዎች ግዴታ ይመስል ተደጋጋሚ የግብጠባቂ ስህተቶችን መመልከት የተለመደ ሂደት ነው። ስህተቶቹን ደግሞ የበለጠ የሚያጎሏቸው ተጫዋቾቹ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ወስደው ለመጫወት በሚያደርጓቸው ጥረቶች የሚፈፀሙ ሳይሆን መሰረታዊ የግብ አጠባበቅ ክህሎቶች ላይ የሚፈፁ ስህተቶች የመሆናቸው ነገር ነው።
ግብ ጠባቂዎች እንደሚሰሯቸው ስህተቶች ቢሆን በርካታ ግቦች ከእነዚህ ስህተቶች መነሻነት በተቆጠሩ ነበር። ነገር ግን በሊጉ የሚገኙ ክለቦች የማጥቃት አፈፃፀም ደካማ በመሆኑ እነዚህ ስህተቶች ብዙ ጊዜ ሲቀጡ አይስተዋልም። በመሆኑም ስህተቶቹ እንደ መደበኛ ነገር እየተቆጠሩ በመምጣታቸው ለማረም ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ አንመለከትም።
እነዚህ ስህተቶች ታድያ ብሔራዊ ቡድናችን ሆነ ክለቦቻችን ስህተቶችን በአግባቡ መቅጣት ከሚችሉ በተፃፃሪነት የጥራት ደረጃቸው ከላቁ በአህጉራዊ ተጋጣሚዎች ጋር ሲሆን እንዴት እንደምንቸገር በቅርቡ እንኳን በአፍሪካ ዋንጫው የተመለከተነው እውነታ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
በመሆኑም ስህተቶችን መሉ ለሙሉ ማስቀረት ባይቻልም ለመቀነስ የሚረዱ ጠንካራ ሥራዎችን እንደ ሀገር ግብ ጠባቂዎቻችን ላይ መስራት የግድ የሚለን ጊዜ ላይ እንገኛለን። ታድያ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የእነዚህን ጥቃቅን የሚመስሉ ስህተቶችን ድምር ውጤት በአህጉራዊ ውድድሮች ዋጋ እያስከፈሉን መቀጠላቸን የሚቀር አይመስልም።
👉 ምርጥ የነበሩት መሐመድኑር ናስር እና እዮብ ዓለማየሁ
ጅማ አባ ጅፋር ሀዲያ ሆሳዕናን በረታበት ጨዋታ ለቡድናቸው ሁለት ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩት መሀመድኑር ናስር እና እዮብ አለማየሁ ድንቅ የጨዋታ ዕለትን ማሳለፍ ችለዋል።
ለወትሮው ውጤት ማስመዝገብ አይቻሉ እንጂ ከተጋጣሚያቸው ጋር የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ለመውሰድ የሚገዳደሩት ጅማ አባ ጅፋሮች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ይበልጥ የመልሶ ማጥቃት ዓይነት መልክ ይዘው በቀረቡበት የማጥቃት ሂደት አስፈሪ የነበሩ ሲሆን በዚህ የጨዋታ ዕቅዳቸው ውስጥ ሁለቱ ተጫዋቾች ቁልፍ ሚና ነበራቸው።
እዮብ አለማየሁ የመጀመሪያዋን ግብ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ አክርሮ በመምታት ሲያስቆጥር ሁለተኛዋን ደግሞ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሂደት ሀዲያ ሳጥን የደረሰውን ኳስ ተረጋግቶ አንድ ተጫዋችን በመቀነስ በግሩም ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል።
በጉዳት ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ የእግርኳስ ህይወቱን ዕድገት ማስቀጠል ያልቻለው እዮብ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት በመጣበት ጨዋታ የሜዳ ላይ ቆይታውን በግብ ማጀቡ በቀጣይ ይበልጥ ያነሳሳዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በተመሳሳይ መሀመድኑር ናስርም የመጀመሪያዋ ግብ ከሶሆሆ ሜንሳ በስጦታ የተበረከተችለት ሲሆን ሁለተኛዋን ደግሞ በግሩም አጨራረስ በማስቆጠር በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ የሆኑትን ግቦች አስመዝግቧል።
ብዙ ተስፋ የተጣለበት ወጣቱ መሀመድኑርም አሁን ይበልጥ ሊጉን እየተላመደ ይመስላል። በቀጣይም ለጅማ አባ ጅፋር በሊጉ የመቆየት ጉዞ ከፍተኛ ሚና ሊኖረው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
👉 ትልቅ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚታትረው ፍፁም ጥላሁን
ከዚህ ቀደም በሊጉ በኢትዮጵያ ቡና የተመለከትነው ፍፁም ጥላሁን አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ በትልቅ ኃላፊነት የቡድኑን ማጥቃት እየመራ ይገኛል።
ቡድኑ በወላይታ ድቻ በተሸነፈበት ጨዋታ ፍፁም ጥላሁን በግሉ የነበረው እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነበር። በጨዋታው መጀመሪያ እንደ ሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ሪችሞንድ አዶንጎ ተቀይሮ ከገባ በኋላ ደገሞ ከግዙፉ አጥቂ ጀርባ እንዲጫወት የተደረገው ፍፁም ጥላሁን የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማሳለጥ ረገድ እንደሁልጊዜው ጥረቶችን ሲያደርግ ተመልክተነዋል።
በግሉ ተደጋጋሚ ዕድሎቹን ለቡድን አጋሩ ይፈጥር የነበረው ፍፁም በተለይ ኳሶችን ወደ ኋላ ተስቦ ከተቀበለ በኋላ ወደ ቀኝ እየሮጠ በግራ እግሩ ወደ ግራ የሚያቀብላቸው ኳሶች አዲስ አበባ ከተማ የአቻነቷን ግብ ሲያስቆጥሩም ሆነ ከግቧ በኃላ ለሪችሞንድ አቀብሎት ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ የተጫዋቹን እይታ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ አጋጣሚዎች ነበረ።
በመጀመሪያው አጋማሽም ሦስት ተጫዋቾች በግሩም ሁኔታ አልፎ ሳጥን ከደረሰ በኃላ ያደረጋት ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመለሰችበት እንጂ አስደናቂ ግብ መሆን የምትችል አጋጣሚ ነበረች።
ሦስት ግቦችን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ማስቆጠር የቻለው ፍፁም ይህን የአዲስ አበባ ከተማ ስብስብ በሊጉ ለማቆየት ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል።
👉 የሀቢብ ከማል የጨዋታ ቀን ከፍታ እና ዝቅታ
አርባምንጭ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር አንድ አቻ በተለያየበት ጨዋታ የጨዋታው መነጋገርያ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ የሀቢብ ከማል ለ33 ደቂቃዎች የዘለቀው የሜዳ ላይ ቆይታው ነበር።
ጨዋታውን በተጠባባቂነት የጀመረው ሀቢብ ከማል በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ኬኒያዊውን ኤሪክ ካፓይቶን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ሜዳ ላይ ብዙም ሳይቆይ በ49ኛው ደቂቃ ደግፌ አለሙ ላይ በሰራው ጥፋት የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ኳሶችን በሜዳው የላይኛው ክፍል ላይ በተደጋጋሚ መልሰው ማግኘት ቢችሉም ኳሶቹን ተጠቅመው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ነበሩት የአርባምንጭ ከተማ ቡድን አባላት በማጥቃቱ ረገድ ከሀቢብ መግባት በኃላ በሚታይ መልኩ መሻሻሎችን ማሳየት ችለዋል።
ታድያ ሀቢብም በ70ኛው ደቂቃ ከርቀት አርባምንጮች ያገኙትን የቅጣት ምት በአስደናቂ መልኩ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ አርባምንጮች ይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን ቢቀጥሉም በ79ኛው ደቂቃ ግን ይህንን ሂደት የሚያደናቅፍ አጋጣሚ ተፈጥሯል።
ግብ አስቆጣሪው ሀቢብ ከማል መሀሪ መና ላይ በፈፀመው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ለመወገድ በቅቷል። ይህም ተጫዋቹ የፈጠረውን አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚያደበዝዝ ከመሆኑ ባሻገር አርባምንጮች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ውጤት ይዘው ለመውጣት የሚያስችል ብልጫ የመውሰዳቸውን ዕድል ያጠበበ ሆኖ አልፏል።
👉 ህልም የሚመስለው የተሾመ በላቸው አጀማመር
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የመከላከያ ከ20 ዓመት በታች ተጫዋች የነበረው ተሾመ በላቸው በዋናው ቡድን የመጀመሪያውን ጨዋታ ባደረገበት የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ የመጀመሪያ ግቡን ማስቆጠር ችሏል።
እንደ ቡድን ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ግብ ለማስቆጠር ተቸግረው የቆዩት መከላከያዎች ባለፉት ጨዋታዎች ይህን የማጥቃት ኃይል ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ተጫዋቾች እየቀያየሩ ለመሞከር ጥረት ቢያደርጉም ውጤታማ ለመሆን ተቸግረው ቆይተዋል።
ነገር ግን እንደቡድን በተሻለ የማጥቃት ፍላጎትን ተላብሰው ለተጫወቱት መከላከያዎች የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረግ የቻለው ተሾመ በላቸው በመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታ 37 ያህል ደቂቃዎች በኃላ በሊጉ የመጀመሪያውን ለቡድኑ ደግሞ ከአምስት ጨዋታዎች በኃላ የተቆጠረችውን የመጀመሪያ ግብ ማበርከት ችሏል።
የሁነኛ የፊት አጥቂያቸው የሆነው ኡኩቱ ኢማኑኤል አለመኖሩን ተከትሎ ብዙ ነገራቸው የተፋለሱት መከላከያዎች በብሩክ ሰሙ እና ተሾመ በላቸው የተመራው የአጥቂ መስመራቸው ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል።
በመጀመሪያ ጨዋታ የመጀመሪያ ግቡን ያስቆጠረው ተሾመ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሊጉ በመጀመሪያ ጨዋታው እምብዛም እንዳልከበደው ፣ የምንይሉ ወንድሙ አድናቂ መሆኑን እና በቀጣይ ከመከላከያ ጋር ብዙ ድሎችን ለማሳካት እንደሚያልም በልበ ሙሉነት ተናግሯል። ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበረው በዚህ ቆይታ ወጣቱ አጥቂ ይነበብት የነበረው ከክለቡ ጋር ያለው ቁርኝት ውጤት የሚመስል ደስታ ለጦሩ ቀጣይ ጊዜያት ተስፋ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ የሰጠም ነበር።