ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 11ኛ ሳምንት ምርጥ 11

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን እንዲህ አሰናድተናል።

አሰላለፍ፡ 4-2-3-1

ግብ ጠባቂ

ቻርለስ ሉኩዋጎ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በጨዋታ ሳምንቱ ሁነኛ የግብ ጠባቂ ተመራጭ ማግኘት ከባድ ነበር። በርካቶች በሜዳ ላይ በሰሩት ስህተት ግብ ሲቆጠርባቸው መረባቸውን ሳያስደፍሩ የወጡ ግብ ጠባቂዎች ደግሞ ብዙ ፈተና ሳያገኛቸው አልፏል። ሆኖም ግብ ካላስተናገዱ አራት የግብ ዘቦች መሀል ባደረግነው ምርጫ ዩጋንዳዊውን ግብ ጠባቂ በቡድናችን አካተነዋል። ተጫዋቹ ግብ ካስተናገደ አምስት ጨዋታዎች አልፈዋል።

ተከላካዮች

ሰዒድ ሁሴን – ፋሲል ከነማ

በዚህ ሳምንት ቡድናችን ውስጥ በመስመር ተከላካዮች በተለይም በቀኝ በኩል በርቀት ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋቾች ባናገኝም ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ አሰላለፍ የተመለሰው እና በጨዋታው አንድ ግብ ያስቆረው ሰዒድን በመከላከሉ ረገድ የነበረውን ጥንቃቄ ከግምት በማስገባት በምርጫችን አካተነዋል።

ምኞት ደበበ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን በቋጨበት ጨዋታ በማጥቃቱ በኩል ከነበረው ስልነት በላይ የኳስ ቁጥጥርን የሚወደው ተጋጣሚው ባህር ዳር የወገብ በላይ ተጫዋቾች ወደ ውስጥ ገብተው ልዩነት እንዳይፈጥሩ ማድረግ አስፈላጊው ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ከስህተት ነፃ የሆነ ቀን በማሳለፍ እና ማጥቃቱን የሚያግዙ ኳሶችን በማስጀመር ኃላፊነቱን የተወጣው ምኞት በቡድናችን ውስጥ ተካቷል።

ሚሊዮን ሰለሞን- አዳማ ከተማ

በዚህ ሳምንት ግብ ሳይቆጠርባቸው ከወጡ ቡድኖች ውስጥ አንዱ አዳማ ከተማ ነው። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ የተጋጣሚ ቅብብሎች አደጋ እንዳይፈጥሩ በማድረግ የተረጋጋ ቀን ያሳለፋው ሚሊዮን ሌላኛው የመሀል ተከላካያችን ሆኗል። ተጫዋቹ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የነበረው ንቃት ቡድኑ ከባድ ሙከራዎች እንሳያገኙት እገዛ አድርጓል።

ዳዊት ማሞ – መከላከያ

ጦሩ ወልቂጤን በረታበት ጨዋታ በግራ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈው ዳዊት በተለይም ከቢኒያም በላይ ጋር በሜዳው ቁመት የፈጠረው ጥምረት ለቡድኑ ጥሩ የማጥቃት አማራጭን ሲፈጥር ታይቷል። ከዚህ ባለፈ ቡድኑ ከመመራት ወደ አቻ መምጣት የቻለባት ወሳኝ ግብ ላይ ጥሩ የቆመ ኳስን ወደ አደጋ ዞን በማድረስ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል።

አማካዮች

ዳዊት እስጢፋኖስ – ጅማ አባ ጅፋር

ባሳለፍነው ሳምንት ምርጥ ቡድናችን ውስጥ ተካቶ የነበረው አንጋፋው አማካይ በዚህም ሳምንት በሳየው ድንቅ አቋም ዳግም ተምርጧል። ጅማ ሆሳዕናን በረታበት ጨዋታ ዳዊት በማጥቃት ሂደቱ ላይ በነበረው ከፍ ያለ ድርሻ ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት ይገለፃል። በተለይም ለአራተኛው የመሀመድኑር ጎል ያደረሰው ኳስ የዕይታውን ጥራት ያሳየ ነበር።

በላይ ዓባይነህ – ጅማ አባ ጅፋር

ጅማዎች በደመቁበት በዚህ ሳምንት በላይ የቡድኑ የማጥቃት ሂደት ፍጥነት ሞተር ሆኖ ውሏል። የአጥቂ አማካይነት ሚና የነበረው ተጫዋቹ ለአንድ ግብ መገኘት ምክንያት መሆን ሲችል በእንቅስቃሴ እና በቆመ ኳስ ሙከራዎች አድርጓል። በላይ በሜዳው ቁመት ሰፊ ርቀት ሸፍኖ በመጫወት የአማካይ ክፍሉ ጠጣር እንዲሆን ሲያስችል ሆሳዕናዎች ከጥልቅ ቦታ ላይ ኳስ እንዳይመሰርቱ በማድረግ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።

እዮብ ዓለማየሁ – ጅማ አባ ጅፋር

የመስመር አጥቂው በጉዳት የተዋጠ የእግርኳስ ህይወቱ ዳግም እየፈነጠቀ ይመስላል። በጅማ አሰላለፍ ውስጥ ብቅ ባለባቸው ያለፉት ጨዋታዎች ጥሩ ጥረት ሲታይበት የቆየ ሲሆን በዚህ ሳምንት በግሩም አጨራረስ ሁለት የተለያየ መልክ ያላቸው ድንቅ ግቦችን በሆሳዕና ላይ አስቆጥሯል።

ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ

በግቦች ላይ ያለው ተሳትፎ ተቀዛቅዞ የነበረው የአጥቂ አማካዩ ሱራፌል ፋሲል ሰበታ ላይ ባሳካው ድል ውስጥ ወሳኙን ሚና ተወጥቷል። የቡድኑን ቅብብሎች ከማሳለጥ ባለፈ ከቆሙ ኳሶች ጥራት ያላቸው ኳሶችን በማድረስ የሚታወቀው ሱራፌል ለሦስቱም ግቦች መነሻ መሆን ችሏል።

በረከት ደስታ – ፋሲል ከነማ

ከተጋጣሚያቸው ሰበታ የተጫዋቾች ምርጫ እና አጠቃላይ አቀራረብ አንፃር ፋሲል ከነማዎች እንደሌላው ጊዜ ሰብረው ለመግባት በተቸገሩበት ጨዋታ በረከት ሳይታሰብ ልዩነት ፈጣሪ ሆኗል። በቁመት አጠር የሚለው ተጫዋቹ ራሱን ነፃ በማድረግ ከቆሙ ኳሶች መነሻቸውን ያደረጉ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ፋሲል በቶሎ ከሽንፈት እንዲያገገም ቁልፍ ሚና ተወጥቷል።

አጥቂ

መሀመድኑር ናስር – ጅማ አባ ጅፋር

ወጣቱ አጥቂ ከጅማ የክረምቱ ፈራሚዎች መካከል ዘንድሮ ጥሩ ጊዜ ያሳልፋል ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን ደብዛዛ ቆይታ ነበረው። ጅማ ሀዲያ ሆሳዕናን በረታበት በዚህ ሳምንቱ ጨዋታ ግን ሁለት ግቦችን በማስቆጠር እና በሌላ አንድ ግብ ላይ ዋና ተሳታፊ በመሆን ድንቅ ዕለትን አሳልፏል።

አሰልጣኝ

አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር

በሊጉ ግርጌ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ተከታታይ ድል በማስመዝገብ ነፍስ የዘራ መስሏል። በተለይም እስካሁን ግብ ማስቆጠር ዳገት ሆኖበት የነበረው ቡድኑ በአራት ግቦች ተንበሽብሾ ሀዲያ ሆሳዕናን የረታበት አኳኋን አስገራሚ ነበር። ከዚህ ቀደም በነበሩ ጨዋታዎች በእንቅስቃሴ እየተሻሻለ መጥቶ ለውጤት እንዲመጣ ዋናውን ሚና የተወጡት አሰልጣኝ አሸናፊ የሳምንቱ ምርጣችን ሆነዋል።

ተጠባባቂዎች

ዮሐንስ በዛብህ – ጅማ አባ ጅፋር
ያኩቡ መሀመድ – ሲዳማ ቡና
መድኃኔ ብርሀኔ – ሀዋሳ ከተማ
ኢማነኤል ላሪያ – መከላከያ
ወንድምአገኝ ኃይሉ – ሀዋሳ ከተማ
ቢኒያም በላይ – መከላከያ
ተሾመ በላቸው – መከላከያ
መስፍን ታፈሰ – ሀዋሳ ከተማ