[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የ12ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መጀመራቸውን የሚያበስረውን መርሐ-ግብር እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለደረሰበት አሰቃቂ ሽንፈት በሰበታው ጨዋታ ምላሽ የሰጠው የወቅቱ የሊጉ ባለክብር ፋሲል ከነማ በአሸናፊነት ዘልቆ በጊዜያዊነት መሪነቱን ለመጨበጥ አዳማ ከተማን ማሸነፍ የግድ ይለዋል።
የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለብ የሆነው ፋሲል ከነማ (18) በጨዋታ ሂደት በሚፈጠሩ ቅፅበቶች የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት መልካም ነው። በክፍት ጨዋታ ኳስን በማንሸራሸር፣ ከቆሙ ኳሶች፣ በፈጣን ሽግግሮች፣ በቀጥተኛ እና በመልሶ ማጥቃት አጨዋወቶች ተጋጣሚ ላይ ጫና ለማሳደር የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ጨዋታም ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት 7 የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካቶ ከነበረው ሰበታ ጋር ተጫውተው በብዙ መመዘኛዎች ጥሩ ሆነው ሦስት ነጥን እና ሦስት ጎል ሸምተው ወጥተዋል። በሁለት መደበኛ 6 ቁጥሮች ለመጫወት የሞከረው ቡድኑም በትዕግስት ኳስን ለማንሸራሸር እና ተጋጣሚን ለማስከፈት ከሞከረው አጨዋወት ባለፈ የቆሙ ኳሶችን በአግባቡ ፍሬያማ ሲያደርግ ነበር። ከዚህ ውጪ ሱራፌል ዳኛቸው ከአጥቂ ጀርባ በመሆን የሚያመቻቻቸውን የመጨረሻ ኳሶችም ኦኪኪን ጨምሮ በረከት እና ሽመክት ለመጠቀም ሲጥሩ ነበር። ቡድኑ በነገውም ጨዋታ ከአዳማ ከተማ ጥንቃቄ አዘል አጨዋወት ሊጠብቀው ስለሚችል ይህንኑ ስልት ሊደግመው ይችላል።
ኳስን በመቆጣጠር ረገድ እምብዛም የማይታማው ፋሲል ጨዋታን በመቆጣጠር ረገድ ግን መጠነኛ ክፍተት አልፎ አልፎ ይታይበታል። ከምንም በላይ ደግሞ በተጋጣሚ ሜዳ በቁጥር በርከት ብሎ እያጠቃ ባለበት ሰዓት ኳስ በሚያጣበት ጊዜ በሽግግር እና መልሶ ማጥቃት ሲጠቃ ይታያል። በተለይ ፈጣን እና በትንሽ ቅብብል ወይም ቀጥተኛ ኳስ ወደ ላይ ጠጋ ብሎ የሚከላከለው የተከላካይ ክፍል ጀርባ ያለው ቦታ ለመጠቀም የሚጥሩ ቡድኖችን ምቾት አለመስጠት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል። የነገው ተጋጣሚ አዳማም ፈጣን አጥቂዎች ያሉት ክለብ በመሆኑ ይህ ክፍተቱ አደጋ ላይ እንዳይጥለው ያሰጋል።
ያለፉትን ስምንት ጨዋታዎች ያልተሸነፈው ነገርግን በሊጉ በርካታ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ያገባደደው አዳማ ከተማ (7) የሊጉን ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ በማሸነፍ ወደ ድል ለመመለስ እና በደረጃ ሰንጠረዡ መሻሻል ለማግኘት ጠንክሮ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል።
በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ስብስብ በ11ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተጫውቶ ያለ ግብ አቻ ሲለያይ ለትችት የሚዳርገው እንቅስቃሴ ነበር ያደረገው። የጨዋታን ብልጫ ለማወቅ በሚጠቅሙ በርከት ያሉ መመዘኛዎችም የወረደ ነገር ማሳየቱ ተስተውሏል። ከምንም በላይ ደግሞ እስካሁን ካደረጋቸው 11 የሊጉ ጨዋታዎች አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አለማድረጉ በማጥቃቱ ረገድ ምን ያህል ተዳክሞ እንደነበር ይነግረናል። እርግጥ በጨዋታው በርከት ያሉ አጥቂ እና የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቢያሰልፍም ስል የመሆን ችግር ታይቷል። ይህ የጎል ፊት ያለ ችግርም በቡናው ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ከዛም በፊት የሚታዩ ነበሩ። ዘንድሮ ካደረጋቸው ጨዋታዎችም 2 ጎል እና ከዛ በላይ ያስቆጠሩት አንድ ጊዜ መሆኑ ብዙ ምስል የሚሰጠን ይመስላል። ይህ ቢሆንም ግን በግል ብቃታቸው ጥሩ የሆኑት እና ፈጣኖቹ አጥቂዎች ከምንም አደጋ የሚፈጥሩ ስለሆኑ ፋሲል መዘናጋት የለበትም።
በእንቅስቃሴ ደረጃ ለክፉ የሚሰጥ ብቃት ሲያሳይ የማይታየው ክለቡ በመከላከሉ ረገድ ጠጣር ይመስላል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠልም ትንሽ ግብ (6) ያስተናገደ ክለብ ነው። በቡድናዊ መዋቅርም ሆነ በግል ከወገብ በታች ያሉት ተጫዋቾች ጠንካራ ብቃት በነገው ጨዋታ ለፋሲል ከነማ ምቾት ላይሰጥ ይችላል። ከዚህ ውጪ ታታሪው ዳዋን ዒላማ ያደረጉ ቀጥተኛ ኳሶች እና የመስመር ላይ ጥቃቶችን በመከተል አዎንታዊ ውጤት ለማምጣት እንደሚጥሩ ይታሰባል።
ፋሲል ከነማ አምበሉ ያሬድ ባየህን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ አማካዩ በዛብህ መለዮ ደግሞ ጉዳት በማስተናገዱ ከጨዋታው ውጪ ሆኗል። በአዳማ ከተማ በኩል ግን ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና አለመኖሩን አረጋግጠናል።
ይህንን ጨዋታ ሄኖክ አክሊሉ በመሐል አልቢትርነት ሲመራው ትግል ግዛው እና ክንፈ ይልማ ረዳት ለሚ ንጉሴ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች 2000፣ 2009፣ 2010፣ 2011 እና 2013 ላይ በአጠቃላይ ዘጠኝ ጊዜ ተገናኝተዋል። በግንኙነታቸውም 5 ጊዜ አቻ ሲለያዩ 3 ጊዜ ፋሲል 1 ጊዜ ደግሞ አዳማ አሸንፏል። በእርስ በእርስ ግንኙነቱ የተሻለ ብልጫ ያላቸው ዐፄዎቹ 9 ግቦችን ሲያስቆጥቱ አዳማዎች ደግሞ 4 አግብተዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)
ሚኬል ሳማኬ
ሰዒድ ሁሴን – አስቻለው ታመነ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው – ሀብታሙ ተከስተ
ሽመክት ጉግሳ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ
ኦኪኪ አፎላቢ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ጀማል ጣሰው
ጀሚል ያዕቆብ – ሚሊዮን ሰለሞን – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ዮሐንስ
አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው
አቡበከር ወንድሙ – ዳዋ ሁቴሳ – አሜ መሐመድ