[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በ12ኛው ሳምንት መጀመሪያ ቀን ምሽት ላይ በሚከናወነው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ጉዳዮች ተመልክተናል።
ባሳለፍነው ሳምንት በየፊናቸው ሽንፈት የገጠማቸው ሀዲያ እና ሰበታ ነገ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥብ ርቀት ላይ የተቀመጠው ሀዲያ ሆሳዕና በውጤት ካገገመባቸው አራት ጨዋታዎች በኋላ ነበር በጅማ አባ ጅፋር ሽንፈት ያስተናገደው። ሰበታ ከተማ ደግሞ ከዘንድሮው ውድድር ብቸኛ ድሉ በኋላ በፋሲል ከነማ የተሸነፈበት ጨዋታ ሦስተኛ ተከታታይ ሽንፈቱ ሆኖ ተመዝግቦ በአደጋ ዞኖ ለመቆየት ተገዷል። ከዚህ አንፃር የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ከታችኛው የፉክክር እርከን ከፍ ለማለት የሚደረግ ፉክክር አድርገን ልንመለከተው እንችላለን።
ያልተጠበቀው የጅማ ሽንፈት ለሀዲያ ሆሳዕና ትልቅ መልዕክት ትቶ ያለፈ ይመስላል። ቡድኑ አሁንም ግለሰባዊ ስህተቶች እና በተጋጣሚ ፈጣን ጥቃት የሚሰነዘርባቸው አጋጣሚዎች ሰለባ መሆኑን በዛ ጨዋታ የተረዳ ይመስላል። በማጥቃቱ ረገድ በሁለቱ የመስመር ተመላላሾች የሜዳውን ስፋት በመጠቀም መሀል ለመሀል በሚሰነዘሩ ጥቃቶችም ወቅት ለፊት አጥቂዎቹ እና ለአማካዮቹ ሰፊ የመንቀሳቀስሻ ክፍተት በመፍጠር የማያስከፋ ብቃትን እያሳየ ይገኛል። ሆኖም ከዚህ በማይተናነስ መልኩ በተለይም በሦስቱ መሀል ተከላካዮች ግራ እና ቀኝ የሚገኙ ቦታዎችን የቡድኑን የማጥቃት ሚዛን በጠበቀ መልኩ መከላከል ለነገ የተተው የቤት ስራው ይመስላል።
በጅማው ጨዋታ ቡድኑ ከጥልቅ የአማካይ ክፍል ማጥቃትን የሚጀምርባቸው ዕድሎች መታፈንም ጨዋታውን አክብዶበት እንደነበር አይዘነጋል። በመሆኑም የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ስብስብ በነዚህ ነጥቦች ላይ ተሻሽሎ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። ከዚህ አንፃር ሀድያ ሀሳዕና ለነገው ጨዋታ አስቻለው ግርማን ከቤተሰብ ሀዘን ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስን ከጉዳት እንዲሁም ፍሬዘር ካሳን ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት መልስ ማግኘቱ በየጨዋታ ክፍሎቹ ላይ የስብስቡን ጥልቀት እንደሚጨምርለት ሲጠበቅ መላኩ ወልዴ ግን አሁንም በቤተሰብ ሀዘን እና ጉዳት ጋር በተያያዘ በስብስቡ አይገኝም።
ውጤት ከራቀው የሰነበተው ሰበታ ከተማ ከሆሳዕና በባሰ የመዋቅር ችግር ውስጥ ይመስላል። የተሻለ የማጥቃት ተነሳሽነት ወስዶ በአመዛኙ ለኳስ ቁጥጥር በቀረበ አጨዋወት ጨዋታዎችን ሲያደርግ የነበረው ቡድን በሚፈልገው መጠን ግቦችን እና የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ከብዶት ቆይቷል። በመጨረሻው የፋሲል ከነማ ጨዋታ ደግሞ ሰባት የሚደርሱ የመከላከል ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች አስገብቶ የተጋጣሚውን ጥቃት ለማፈን ቢጥርም ከቆመ ኳስ መነሻነት ሦስት ግቦች አስተናግዶ ተሸንፏል።
በእርግጥ ቡድኑ በተለይ በሁለቱ መስመሮች በቁመት የተከላካይነት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች በመጠቀም የፋሲልን የኮሪደር እንቅስቃሴ ማዳከሙ ተመሳሳይ የመስመር ጥንካሬ ባለው ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ለሚኖረው ስትራቴጂ ጠቃሚ ግብዓት አግኝቶ ሊሆን ይችላል። ሆኖም የመከላከል መዋቅሩ ሳይናጋ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ቡድኑ አዲስ መፍትሄ ይዞ መምጣት ያስፈልገዋል ፤ እንዳለፈው ሳምንት ብዙ ለውጦች የተደረጉበት አሁን ግን ማጥቃትን የሚያበረታታ የተጨዋቾች ምርጫ እንደሚኖረውም ይጠበቃል። ለዚህም አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከቢያድግልኝ ኤልያስ ውጪ ቀሪ ስብስባቸው ዝግጁ መሆኑ እንደሚያግዛቸው ይታመናል።
ጨዋታው በማኑሄ ወልደፃዲቅ የመሀል ዳኝነት የሚደረግ ሲሆን ይበቃል ደሳለኝ እና አብዱ ይጥና ረዳቶች ኃይለየሱስ ባዘዘው ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበውበታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች አምና ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ የተገናኙ ሲሆን ቀዳሚው ጨዋታ ያለግብ ሲጠናቀቅ በሁለተኛው ጨዋታ ሰበታ ከተማ በዱሬሳ ሹቢሳ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል 3-2 መርታት ችሏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)
ያሬድ በቀለ
ቃለዓብ ውብሸት – ፍሬዘር ካሳ – ሄኖክ አርፊጮ
ብርሃኑ በቀለ – ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ኢያሱ ታምሩ
ባዬ ገዛኸኝ – ሀብታሙ ታደሰ
ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)
ለዓለም ብርሀኑ
ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ታፈሰ ሰርካ
በኃይሉ ግርማ – ወልደአማኑኤል ጌቱ
ሳሙኤል ሳሊሶ – አንተነህ ናደው – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
ዘካሪያስ ፍቅሬ