[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የ12ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ እና ተጠባቂ መርሐ-ግብር የሆነው የአዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በ10ኛ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰባቸው አሰቃቂ ሽንፈት ያገገሙት ፋሲል ከነማዎች ሰበታን ሦስት ለምንም ሲረቱ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድም ለውጥ ሳያደርጉ ወደሜዳ ሲገቡ የውድድር ዓመቱ 7ኛ የአቻ ውጤታቸውን ያስመዘገቡት አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለግብ ከተለያዩበት ፍልሚያ ሁለት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ዮሴፍ ዮሐንስን በታደለ መንገሻ እንዲሁም አሜ መሐመድን በአብዲሳ ጀማል ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች የተሻለ ብልጫ የነበራቸው አዳማ ከተማዎች የሚያገኟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደግብ በመውሰድ ቀዳሚ ለመሆን ሲጥሩ ታይቷል። በዚህም ተደጋጋሚ የመዓዘን ምቶችን እና ከሳጥን ውጪ የሚገኙ ኳሶችን ለግብ ምንጭነት ሲጠቀሙ ነበር። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመምጣት የጣሩት ፋሲሎች በበኩላቸው በ11ኛው እና በ15ኛው ደቂቃ ከሱራፌል ዳኛቸው በተነሱ የቅጣት ምቶች ወደ ግብ ቀርበው ተመልሰዋል። በ20ኛው ደቂቃ ደግሞ የመስመር አጥቂው ሽመክት ጉግሳ ከሱራፌል የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ቢሞክረውም የአዳማው የግብ ዘብ ጀማል ጣሰው እምብዛም ሳይቸገር ተቆጣጥሮታል። ይህንን ሙከራ ያደረገውን ሽመክት ቦታ የቀየረው በረከት ደስታ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሰዒድ ሁሴት ያሻማውን ኳስ መረብ ላይ ለማሳረፍ ዳድቶ ለጥቂት ወጥቶበታል።
ጨዋታው ግማሽ ሰዓት ሲደርስ በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው አዳማ ከተማ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ በጨዋታው መሪ ሆኗል። በዚህም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ጀሚል ያቆብ ያሻገረውን ኳስ አሜ መሐመድ በድንቅ ሁኔታ በቀኝ እግሩ መረብ ላይ አሳርፎታል። ግብ ካገኙ በኋላም እምብዛም ለጥንቃቄ ቅድሚያ ያልሰጡት አዳማዎች መጠነኛ ጫና ቢበዛባቸውም ተቋቁመው ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ሲጥሩ ነበር። ፋሲሎች ደግሞ በዋናነት በሱራፌል አማካኝነት ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም የጀማልን መረብ ማግኘት ሳይችሉ አጋማሹ ተገባዷል።
ወደጨዋታው ለመመለስ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሁለት ተጫዋቾችን የለወጡት ፋሲሎች የማጥቃት ሀይላቸውን አሻሽለው ግብ ፍለጋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። የአዳማ የግብ ክልልንም ቶሎ ቶሎ እየጎበኙ አጋጣሚዎችን መፍጠር ተያይዘዋል። በተለይ በ58ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት የሞከረው ኳስ እጅግ ለግብነት ከጫፍ የደረሰ ነበር። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በረከት ለኦኪኪ አፎላቢ ኳስ አሻግሮ ግዙፉ አጥቂ በግንባሩ ኳስ እና መረብን ሊያገናኝ ነበር።
አሁንም ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ ለመውጣት የጣሩት ዐፄዎቹ በ74ኛው ደቂቃ ውጥናቸው ሰምሮ አቻ ሆነዋል። በዚህም ከመልስ ውርወራ የተገኘውን ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ ሰዒድ ሁሴንን ቀይሮ የገባው ዓለምብርሐን ይግዛው ወደ ሳጥን አሻግሮት ግብ ጠባቂው ጀማል የወረደ የውሳኔ አሰጣጥ እና የሰዓት አጠባበቅ ስህተት ፈፅሞ ኦኪኪ ኳስ መረብ ላይ አሳርፏል። በቀሪ ደቂቃዎች ፋሲሎች ወደ መሪነት ለመምጣት ታትረው ቢንቀሳቀሱም ጎል ፊት መጣደፍ ታይቶባቸው ጎል ማግኘት አልቻሉም። አዳማም ጨዋታው ሲጀምር ይዞት የገባውን አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት በከፍተኛ ሁኔታ በመከላከል ጨዋታውን ለመፈፀም ጥረዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች ከድር ኩሊባሊ እና ፋቃዱ ዓለሙ እጅግ ለግብ የቀረበ ኳስ ቢሞክርም ሳይሳካለት ጨዋታው ተጠናቋል።
የአቻ ውጤቱን ተከትሎ በጊዜያዊነት የሊጉ መሪ ለመሆን ውጥን ይዞ ወደ ሜዳ የገባው ፋሲል ከነማ ሀሳቡ ባይሰምርም በ22 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ፀንቶ ተቀምጧል። አዳማ ከተማም ነጥቡን 17 አድርሶ ያለበት አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።