[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉት ሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ በአስገራሚ ሁኔታ ለሊጉ አስተዳዳሪ አካል ባስገቡት ደብዳቤ መነሻነት በስታዲየም የደጋፊዎቻቸውን ድጋፍ የሚያጡ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይነት እየተደረገ የሚገኘው የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በድሬዳዋ ስታዲየም ማከናወን እንደጀመረ ይታወቃል። የሊጉ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ በ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የታዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶችን በመንተራስ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን የሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ ደጋፊዎች በጨዋታቸው የዕለቱን አልቢትር አፀያፊ ስድብ ሰድበዋል የሚል ሪፖርት እንደቀረበባቸው በመግለፅ እያንዳንዳቸው 75 ሺ ብር ቅጣት እንዲተላለፍባቸው እንደተደረገ ይታወቃል። ሁለቱ ክለቦች ውሳኔው ከደረሳቸው በኋላ ለሊጉ የላኩት የምላሽ ደብዳቤ ግን በአስገራሚ ሁኔታ ለሌላ ውሳኔ በር ከፍቷል።
በዚህም ክለቦቹ ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ባስገቡት ደብዳቤ የተመዘገበ ደጋፊ እንደሌላቸው የገለፁ ሲሆን በቅድሚያ ወላይታ ድቻ በፃፈው ደብዳቤ “በድሬዳዋም ሆነ ከዚህ በኋላ በሚደረጉት ቀሪ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ-ግብር ጨዋታዎች ላይ በስፖርት ክለቡ ተመዝግበው በህጋዊነት የሚደግፉን ደጋፊዎች የሌሉን ስለሆነ በሜዳ ውስጥ በሚደረጉ በማንኛውም ድርጊቶች እና ተግባራት ስፖርት ክለቡ ኃላፊነት የማይወስድ መሆኑን እናሳውቃለን” ይላል። ሀዲያ ሆሳዕናም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ደብዳቤ ያስገባ ሲሆን በመጠኑ ከድቻ የሚለየው በድሬዳዋ በሚደረጉ ጨዋታዎች ብቻ ኃላፊነት እንደማይወስድ በመጠቆሙ ነው።
ክለቦቹ በፃፉት ደብዳቤ መሰረትም ባሳወቁት ደብዳቤ ምክንያት ከዚህ በኋላ በሚደረጉ ጨዋታዎች በስታዲየም ደጋፊዎቻቸውን እንደማያገኙ ተጠቁሟል። አክሲዮን ማኅበሩም በክለቦቹ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ደጋፊዎቻቸውን ወደስታዲየም እንዳይገቡ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
ክለቦቹ ለአክሲዮን ማኅበሩ ያስገቡት ደብዳቤ ከስር ተያይዟል 👇👇