[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ሀድያ ሆሳዕና ሦስት ነጥብ ከሰበታ ከተማ ላይ ካገኘበት የምሽቱ ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ሰበታ ከተማ
ስለ ጨዋታው
“የጨወታውን መንገድ እንግዲህ በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛው ከፍተኛ የግብ አጋጣሚዎችን የተጠቀመ ቡድን ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ የተሸነፈ ቡድን ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
ስለ መጀመሪያው አጋማሽ ጥንካሬ እና ስለ ሁለተኛው አጋማሽ መዳከም
“በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን አግኝተናል፡፡ ልጆቹ የሚፈለግባቸውን ነገር አድርገዋል ፤ ምንም እንኳን ውጤቱ ጥሩ ባይሆንም። በሁለተኛው አጋማሽ በተለይ ፍፁም ቅጣት ምት ከተቆጠረብን በኋላ በተደጋጋሚ ግቦች ተቆጥረው ሽንፈት የሚመጣው ነገር ውስጣቸው ስላለ ይሄ ደግሞ ስሜትን በጣም ነው የሚበርዘው፡፡ በዚህ መነሻነት የመቀዛቀዝ ነገሮች ታይቷል፡፡ ካገባን አግብተን እናሸንፋለን የሚለው ሥነ ልቦና በተደጋጋሚ ሽንፈቶች የጠፉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከዛ መነሻነት የመጡ ነገሮች ናቸው። እንደ አጠቃላይ ግን ልጆቹ የሚችሉትን አድርገዋል፡፡ ምናልባት ስታስቲኩም ሊናገር ይችላል፡፡ ፍፁም ያለቀላቸውን የግብ አጋጣሚዎች አግኝተናል፡፡ ነገር ግን ኳስን ከመረብ ጋር የማገናኘት አቅማችን የአቅም ውስንነት ብቻ ሳይሆን ዕድለኝነቱም ከእኛ ቡድን ጋር አለ ለማለት አይቻልም፡፡ በዛሬ ጨዋታ ብቻ አይደለም በበርካታ ጨዋታዎች ነጥብ የምንጥልባቸው ጨዋታዎች የግብ አጋጣሚዎችን እናገኛለን ግን ተጠቅሞ ወይም ነጥብ መያዝ ላይ ብዙም አንሳተፍም ፤ ለዚህም ነው ዛሬ ታች ያለነው፡፡ ሲጀመር እንደ አጠቃላይ ደማምረህ ስታየው የመጨረስ አቅም ውስንነት ብቻ ሳይሆን ዕድለኝነቱ ከእኛ ጋር አልነበረም ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
ለሰበታ እዚህ ጋር መገኘት ምክንያቱ
“እንግዲህ አሁን በተለያየ መንገድ መውሰድ ይቻላል፡፡ አሁን ዋናው ነጥብ ወደ ሌላው ጣትህን የምትቀስርበት አይደለም ችግሩ ያለው እኛ ጋር ነው፡፡ እኛ ነን ይሄን መለወጥ ፣ መስራት ያልቻልነው። ስለዚህ ይሄ እንደዚህ አድርጓል ያ እንደዚህ አድርጓል ወደ ሚል መጠቋቆም አንሄድም። ነገር ግን እኛ በተደጋጋሚ ነጥብ አስቆጥሮ የመውጣት ሂደት ላይ ቅድም ባልኩት መንገድ የዕድለኝነቱ ጉዳይ ላይ ምን አልባት ደግሞ እጅግ በጣም በጥቂቱ ተፅእኖ ፈጣሪ ተጫዋቾች በቡድኑ ማሟላት ባለመቻላችን ድክመት መስሎ ይታየኛል፡፡ ነገር ግን ለዚህም ድክመት ተጠያቂው እኛ ነን ፤ ሌላው አይደለም። እኛ ነን ያልሰራነው ስለዚህ ወደ ሌላው የምንጠቋቆምበት አንዳች ነገር አይኖርም፡፡”
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀድያ ሆሳዕና
በአንድ ጎል ወደ አሸናፊነት ስለ መመለስ
“አዎ በሚገባ ለምን ያው ተነጋግረን ስንመጣም የነበረው ቢያንስ ድሬዳዋ ከመጣን አላሸነፍንም አንድ አቻ አንድ መሸነፍ ነው እና ዛሬ አሸንፈን አሁን ካለንበት ደረጃ ከፍ ለማለት ነው የመጣነው። እና ከሌላው ጊዜ ለየት የምትለዋ ኢቺን ሦስት ነጥብ ማግኘታችን ነው ዛሬ ይገባናል፡፡
ሚካኤል ጆርጅን ረጅም ሰዓት ሜዳ ላይ ስለማቆየት
“እኛ የምንፈልገው አግኝተናል መጀመሪያም ታክቲካሊ የምንፈልገው ነገር ነበር ፤ ከሰበታ ጋር ስንጫወት። ግን እንዲያውም ከጠበቅነው በላይ እጅግ በጣም ጥሩ ነበር ብዬ ነው የማምነው። ትንሽ የሰበታ ተከላካዮች አግሬሲቭም ናቸው፣ በኳሊቲም ጥሩ ናቸው፡፡ ቢያንስ ከእነርሱ ጋር ቻሌንጅ አድርጎ የሚጫወት ሰው ነበር የሚያስፈልገን ሚካኤል ጆርጅ ደግሞ ይሄን በአግባቡ ተወጥቶታል ብዬ ነው የማምነው፡፡
ስለ ቀጣይ
“ያው በዚሁ ነው የምንቀጥለው። በቂ ዝግጅት አድርገናል የተዘጋጀነውም ለሁሉም በአንድ ዓይነት ግምት ነው፡፡ ለሰበታም ለጊዮርጊስም ለኢትዮጵያ ቡናም እኛ አንድ ዓይነት አመለካከት ነው የሚኖረን። እና አሁንም ያለንበት ቦታ ኮንፈርት ስላልሆነ ግዴታ እያሸነፍን መሄድ ነው የኛ አላማ። ቀጠይ ተጋጣሚያችንን ደግሞ ቻሌንጅ አድርገን ተጫውተን አሸንፈን ካለንበት ደረጃ ተሻግረን ለመሄድ እንጂ የተለየ ግምቶች እየሰጠን ለሁሉም ክለቦች አንመጣም ተመሳሳይ ነገርን ነው ይዘን የምንመጣው፡፡