[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የነገ ምሽቱን ጨዋታ አስመልክተን ያዘጋጀነው የጨዋታ በፊት ዳሰሳችን ይህንን ይመስላል።
ድሬዳዋ በተለያየ የውጤት ገድ የተቀበለቻቸው ባህር ዳር እና ሀዋሳ የሚያደርጉት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚያስመለክተን ይጠበቃል። ዋና አሰልጣኙን ከአፍሪካ ዋንጫ አህጉራዊ ተልዕኮ መልስ የሚያገኘው ባህር ዳር ከውጤት ከራቀ አራት ጨዋታዎች አልፈውታል። ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ያገኘኙት ቡድኑ ከተሰጠው ግምት በተቃረነ ሁኔታ ከሰንጠረዡ ወገብ ሸርተት ብሎ በመገኘቱ የነገው ውጤት እጅግ አስፈላጊው ነው። በሌላ ጎን ሦስት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ እዚህ የደረሰው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ከሦስተኛ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ የሚልበትን ዕድል በራሱ ለመወሰን ወደ ጨዋታው ይቀርባል።
ባህር ዳር ከተማ በሰሞኑ ሽንፈቶቹ የታየበት ድክመት ለነገው ግጥምያ ትልቁ ስጋቱ ነው። የተከላካይ ክፍሉን ወደ መሀል ሜዳ አስጠግቶ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት መውጣትን ምርጫው የሚያደርገው ቡድኑ ለፈጣን መልሶ ማጥቃት የሚጋለጥባቸው አጋጣሚዎች ተደጋግመው እየታዩ ነው። ይህ ድክመት ከተከላካዮች አለመናበብ እና ግለሰባዊ ስህተቶች ተጨምረውበት ቡድኑ በቀላሉ ግብ የሚያስተናግድ አድርገውታል። ይህ ተንከባሎ የመጣ ችግር ለነገ ተጋጣሚው ሀዋሳ ከተማ ጠንካራ የመልሶ ማጥቃት አቅም አንፃር ሲታይ ደግሞ ይበልጥ ትኩረትን ይስባል።
የመስፍን ፣ ብሩክ እና ኤፍሬም ጥምረትን ይዞ የቀጠለው ሀዋሳ ከተማ በውጤት ጥሩ ጊዜ ላይ ከመገኘቱ ባሻገር የማጥቃት አቅሙ የአጋጣሚ አለመሆኑን በሚያስቆጥራቸው ግቦች አካሄድ ድግግሞሾች እያሳየ ነው። በነገውም ጨዋታ ሦስቱ አጥቂዎች ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችንም ሆነ በባህር ዳር አማካይ እና የኋላ ክፍል መሀል ኳስ ሲቀበሉ አደገኛ ዕድሎች የመፍጠር አቅማቸው ከፍተኛ ይሆናል። በዚህ ረገድ ባህር ዳር በመከላከል ሽግግር ወቅት የሚኖረው ስኬት በጨዋታው እጅግ ወሳኝ ይሆናል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የጣና ሞገዶቹ መናፍ ዐወልን በመጠቀም በሦስት ተከላካዮች ወደሚጀምር አሰላለፍ የሚመጡበት ዕድል ቢኖርም ኋላ ላይ የቁጥር ብልጫን ከማግኘት ባለፈ ሽግግራቸው ላይ ትልቅ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሀዋሳ ከተማ በጨዋታው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለመያዝ ብዙ ጉልበት ላያወጣ ይችላል። ይልቁኑም ተጋጣሚውን ወደራሱ ሜዳ ስቦ ኳስ ማስጣል ይበልጥ ሊያዋጣው ይችላል። የጣና ሞገዶቹ የፈጣኑ አጥቂያቸው ዓሊ ሱለይማንን ፍጥነት ለድንገተኛ ጥቃት ባይጠቀሙም በፍፁም ዓለሙ እንቅስቃሴ ላይ የሚመሰረተው የማጥቃት ቅብብላቸው የሀዋሳ የኋላ ክፍል ክፍተት እንዲፈጥር እና ስህተት እንዲሰራ የማድረግ አቅም ሊኖራቸው የግድ ይላል።
ከታክቲካዊ ጉዳዮች በላይ ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋን በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ሲያሸንፍ የተፈጠረው የስሜት መነሳሳት በነገው ጨዋታ ይንፀባረቃል ወይስ ባህር ዳሮች ከአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ መመለስ እና ከተደጋጋሚ ሽንፈቶች የሚመነጭ የቁጭት ንቃት ያሳያሉ የሚለው ጉዳይ ፍልሚያው ላይ ተፅዕኖው ቀላል የሚሆን አይመስልም።
ባህር ዳር ከተማ በነገው ጨዋታም የኦሴይ ማዉሊ እና መሳይ አገኘሁን በጉዳት ግርማ ዲሳሳን ደግሞ በቅጣት የማያገኝ ሲሆን ተከላካዩ መናፍ ዐወል ማገገሙን ግን ሰምተናል። በሀዋሳ በኩል በተመሳሳይ አብዱልባስጥ ከማል ከመጠነኛ ጉዳቱ መልስ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።
ተካልኝ ለማ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ሲመሩት ሶርሳ ዱጉማ እና ሻረው ጌታቸው ረዳቶች ኤፍሬም ደበሌ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ሀዋሳ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች ማሸነፍ ችሏል። እስካሁንም ሀዋሳ አራት ባህር ዳር ደግሞ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።
ባህር ዳር ከተማ (3-5-2)
ፋሲል ገብረሚካኤል
ፈቱዲን ጀማል – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል
ሳለአምላክ ተገኘ – አብዱልከሪም ንኪማ – አለልኝ አዘነ – አህመድ ረሺድ
ፍፁም ዓለሙ
ዓሊ ሱሌይማን – ተመስገን ደረሰ
ሀዋሳ ከተማ (4-2-3-1)
መሀመድ ሙንታሪ
ዳንኤል ደርቤ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – መድሀኔ ብርሀኔ
አብዱልባስጥ ከማል – በቃሉ ገነነ
ኤፍሬም አሻሞ – ወንድማገኝ ኃይሉ – መስፍን ታፈሰ
ብሩክ በየነ