ቅድመ ዳሰሳ | አዲስ አበባ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

መቀመጫቸውን በመዲናችን ያደረጉት አዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ነገ አመሻሽ 10 ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታን እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉት አዲስ አበባ ከተማዎች ዳግም ሦስት ነጥብ በማግኘት ከሚገኙበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት እና ካሉበት የውጤት ቀውስ ለመላቀቅ ነገ ጠንካራ ብቃታቸውን ማሳየት ይገባቸዋል።

በሊጉ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ከተሸነፉ በኋላ ሳይጠበቅ ለተከታታይ አራት ጨዋታዎች ሳይሸነፉ ተጉዘው የነበሩት አዲስ አበባዎች ከዛ በኋላ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ እንከን ያጋጠማቸው ይመስላል። በተለይ ደግሞ በመከላከሉ ረገድ በየጨዋታዎቹ ግቦችን ማስተናገዳቸው ሁነኛ አስተማማኝ የኋላ መስመር እንደሌላቸው የሚጠቁም ነው። አብዛኛውን ጊዜ በ4-3-3 የተጫዋች አደራደር ቅርፅ ወደሜዳ የሚገባው ቡድኑም አስገራሚ የሽርፍራፊ ሰከንድ ክስተቶች ተስተውለው በወላይታ ድቻ በተረታበት ጨዋታ እስካሁን ያልሞከረውን የአጥቂ አጠቃቀም አስመልክቶን ነበር። በዚህም በተደጋጋሚ የመስመር አጥቂ ሆኖ ሲጫወት የነበረው ፍፁም ጥላሁንን እንደ ሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ለመጠቀም ጥረው ነበር። ነገርግን ይህ ዘዴ እምብዛም ሳያዋጣ በሁለተኛው አጋማሽ ለውጥ አድርገው ነበር። የነገ ተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ወደ ላይኛው ሜዳ ተጠግቶ በድፍረት የሚጫወት ቡድን ስለሆነ ለፈጣን እና ቀጥተኛ አጨዋወት የሚመች የፊት መስመር ተመራጭ እንደሚኖራቸው ይገመታል።

እንደ ተጋጣሚው ድል የራቀው ኢትዮጵያ ቡና አምስት ደረጃዎችን በጊዜያዊነት ለማሻሻል እና የአሸናፊነት መንገዱን ለማግኘት ነገ ከሌላኛው የመዲናው ክለብ የሚጠብቀውን ብርቱ ትግል ማለፍ የግድ ይለዋል።

ከመከላከያ እና ጅማ በመቀጠል በሊጉ ሁለተኛው ትንሽ ግቦችን (8) ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረ ክለብ የሆነው ቡና (ከሰበታ እና አርባምንጭ ጋር በጣምራ) ከዓምናው በተቃራኒ ወጥ ያልሆነ ብቃት በሊጉ እያሳየ ይገኛል። በመጀመሪያ አራት ጨዋታዎች ድል ከራቀው በኋላም ተከታታይ አራት ጨዋታዎችን አሸንፎ በድጋሜ የውጤት ማጣት ውስጥ ተዘፍቋል። ከምንም በላይ ደግሞ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ያ የሰላ የፊት መስመር መዶልዶሙ ዋና እያስከፈለው ይገኛል። በሦስቱ ጨዋታዎችም በድምሩ አምስት ብቻ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር ያደረገው። ይህ ክፍተት ደግሞ የፊት መስመር ችግር ብቻ ሳይሆን የአማካይ መስመሩ አስፈላጊ ድጋፍ አለማድረጉም ነው። በተለይ ፔኔትሬሽን ኳሶችን ወደፊት በመላክ ረገድ እጅግ ተዳክሟል። ይህ ደግሞ ቡድኑ ከመስመር አጨዋወት ብቻ የግብ ዕድሎችን ለማግኘት እንዲገደድ አድርጎታል። ምናልባት ይህ ከሆነ አዲስ አበባዎች የቡናን የማጥቃት አጨዋወት ገምተው እንዲዘጋጁም ሊያደርግ ይችላል። ከምንም በላይ ግን የአማካይ መስመሩ ሪትም እንደ ዓምናው አለመሆኑ ቡድኑን ያሳሳው ሲሆን አቡበከር ናስር ነገ የሚሰለፍ ከሆነ ግን በእንቅስቃሴ ክፍተቶች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል።

አዲስ አበባ ከተማ በነገው ጨዋታ ለኳስ ቁጥጥር እምብዛም ፍላጎት እንደማይኖረው ይታሰባል። ይልቁንም ከኳስ ጀርባ በቁጥር በዝቶ በመቆም በመጨረሻው የሜዳ ክፍል ቡና የሚያደርገውን የኳስ ቅብብል በማቋረጥ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እና ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረግ ሽግግርን መከተል ሀሳባቸው ሊሆን ይችላል። ኢትዮጽያ ቡናዎች ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር ሲጫወቱ ተጋጣሚያቸው ቁጥብ ሆነ እንጂ ለመልሶ ማጥቃት ተጋልጭ ነበሩ። አዲስ አበባም እንዳልነው የመልሶ ማጥቃቶችን ከመሰንዘሩ በተጨማሪ ሪችሞንድን ዒላማ ያደረጉ ኳሶች ሊጠቀም ይችላሉ። ከዚህ ውጪ ግን ቡናማዎቹ ተጋጣሚን ከኳስ ውጪ በማዳከም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀሱ ይታሰባል። እንዳልነው የአቡበከር ናስር ቡድኑን ለማገልገል ብቁ መሆን ደግሞ አንድም ግብ ሳያስቆጥር ሦስት ጨዋታዎች ላለፉት ስብስብ መልካም ዜና ይሆባል።

በአዲስ አበባ በኩል አሁንም ፈይሰል ሙዘሚል እና ነብዩ ዱላ ረጅም ጊዜ ከፈጀባቸው ጉዳታቸው አለማገገማቸው ሲገለፅ በኢትዮጵያ ቡና በኩል እንደገለፅነው ወደ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የሚያደርገውነወ ዝውውር አገባዶ ዓመቱን ለመጨረስ የመጣው አቡበከር ናስር ለጨዋታው ቡቁ መሆኑ ትልቁ ዜና ነው።

አርቢትር ሚካኤል ጣዕመ ጨዋታው በመሐል ዳኝነት ሲመሩት ካሳሁን ፍፁም እና ትንሳኤ ፈለቀ ረዳት የመስመር ዳኛ ዳንኤል ግርማይ ደግሞ አራተኛ ዳኛ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ብቻ ተገናኝተዋል (2009)። በሁለቱም ግንኙነቶች ባለድል የሆነው ኢትዮጵያ ቡና (1-0 እና 2-0) ነበር።
ግንታዊ አሠላለፍ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ሳሙኤል አስፈሪ – ዘሪሁን አንሼቦ – ሳሙኤል ተስፋዬ

ኤልያስ አህመድ – ቻርለስ ሪባኑ – ሙሉቀን አዲሱ

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ አዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረተንሳይ – አበበ ጥላሁን – ቴዎድሮስ በቀለ – ሥዩም ተስፋዬ

ታፈሠ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊልያም ሰለሞን

አቤል እንዳለ – አቡበከር ናስር- አስራት ቱንጆ