[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ጎፈሬ ከአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽን በመቀጠል ከሌሎች ፌዴሬሽኖች ጋር አብሮ ለመስማት ተስማምቷል።
በሀገራችን የሊግ ዕርከኖች ከሚገኙ ክለቦች እንዲሁም በተለያዩ የእግርኳስ ውድድሮች ላይ ከሚሳተፉ ቡድኖች ጋር አብሮ በመስራት ላይ የሚገኘው ሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ኩባንያ ጎፈሬ ከክልል እግርኳስ ፌዴሬሽኖች ጋርም ስምምነት እየፈፀመ ይገኛል። ተቋሙ ከዚህ ቀደም ከአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ዘርፈ ብዙ የሆነ ስምምነት መፈፀሙ ሲታወስ አሁን ደግሞ በተመሳሳይ ከኦሮሚያ እና ሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር ውል አስሯል።
የኦሮሚያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በአቶ ፍሮምሳ የሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ በአቶ አንበስ ተወክለው ከትጥቅ አማራቹ ኩባንያ ጋር ዛሬ ማለዳ ያደረጉት ስምምነት የሚቆየው ለቀጣይ ሦስት ዓመታት ይሆናል። በስምምነቱ መሰረት ጎፈሬ በክልሎቹ ውስጥ ለሚገኙ የወረዳ እና የዞን ክለቦች የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ የሚገልፁ ትጥቆችን ለማቅረብ ተስማምቷል።
ከዚህ ውጪ ተቋሙ የክልሎቹን የእግርኳስ ዕድገት ለማሳለጥ የሚረዱ የማርካቲንግ ሥራዎችን የሚሰራ ሲሆን ክለቦች ራሳቸውን የሚችሉባቸው መንገዶች እንዲፈጠሩም እገዛ እንደሚያደርግ ታውቋል። በተጨማሪም ከስፖርቱ ጋር የተያያዙ ሁነቶች ሲኖሩ ጎፈሬ የማሰናዳቱን ድርሻ ሲወስድ ከእግርኳስ ፌዴሬሽኖቹ በተጨማሪ ከክልሎቹ አስተዳደሮች ጋር በጋራ በመሆን ሌሎች ስፖርታዊ ክንውኖችን የማሰናዳት ውጥን እንዳላቸው ተገልጿል።