​ሪፖርት | ቡናማዎቹ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ሁለቱን የመዲናችን ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ከሽንፈት የመጡት አዲስ አበባ ከተማዎች ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ለመታረቅ ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ፍልሚያ እንዳለ ከበደን በቢኒያም ጌታቸው ብቻ ሲለውጡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ አቤል እንዳለን በዊሊያም ሰለሞን እንዲሁም እንዳለ ደባልቄን በአቡበከር ናስር ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቡናዎች ኳስን ለመቆጣጠር ሲጥሩ አዲስ አበባዎች ደግሞ ወደራሳቸው ሜዳ ተስበው የሚያገኟቸውን ኳሶች በረጅሙ በመላክ ግብ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ ነበር። በ5ኛው እና 8ኛው ደቂቃም የጨዋታው ሁለት የመጀመሪያ ሙከራዎች በኢትዮጵያ ቡና በኩል በአስራት ቱንጆ እና አበበ ጥላሁን አማካኝነት ተሞክረው ዒላማቸውን ስተው ወጥተዋል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ቡናዎች በአዲስ አበባ የግራ መስመር በኩል ገብተው እጅግ ለግብ የቀረበ ጥቃት በአቡበከር አማካኝነት ፈጥረው ተመልሰዋል።

ኳሱን ለቡናማዎቹ ሙሉ ለሙሉ በሚመስል መልኩ ትተው መጫወት የያዙት የአሠልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ተጫዋቾች መልሶ ማጥቃት ላይ ትኩረት ሰጥተው የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። እስከ ግማሽ ሰዓት ድረስ የሰላ ጥቃት ያላስተናገደው ጨዋታው በ33ኛው ደቂቃ በተፈጠረ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ግብ አስተናግዶ መሪ አግኝቷል። በዚህም ከተፈጥሮዋዊ ቦታው ወደ ቀኝ አዘንብሎ የማጥቃት እንቅስቃሴውን እንዲያግዝ ሀላፊነት ተሰጥቶት ወደ ሜዳ የገባው ዊሊያም ሰለሞን ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ሮቤል ተክለሚካኤል በግንባሩ ሲያመቻቸው በሩቁ ቋሚ አግኝቶ በአንድ ንክኪ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡናን ወደ መሪነት አሸጋግሯል። ዊልያም ሰለሞን ጎል ካስቆጠረ በኋላ በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው ሞሮኳዊ ታዳጊ ረያን ኦራምን መለያው ስር ፅፎ ባስገባው መልዕክት አስቧል።

ግብ ያስተናገዱት አዲስ አበባዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላም የአጨዋወት ለውጥ ሳያደርጉ በመከላከል ቅኝት ጨዋታውን ቀጥለዋል። በ35ኛው ደቂቃ ግን የቡድኑ አምበል ዘሪሁን አንሼቦ ከመዓዘን ምት የተነሳን ኳስ በግንባሩ ለመጠቀም በመጣር ቡድኑን አቻ ሊያደርግ ነበር። በቀሪ ደቂቃዎች ሮቤል ከሳጥን ውጪ አክርሮ ከመታው እና አስራት በግራ የሳጥኑ ክፍል ተገኝቶ ከሞከረው ኳስ ውጪ ሌላ የግብ አጋጣሚ ሳይፈጠር አጋማሹ ተገባዷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያላደረጉት አዲስ አበባዎች ሁለተኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሲጀምሩ ሁለት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው በማስገባት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል። በ48ኛው ደቂቃም የመጀመሪያ የቡናን ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ የፈተነ ኳስ በፍፁም ጥላሁን አማካኝነት ሰንዝረው አቻ ሊሆኑ ነበር። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሙሉቀን አዲሱ በቀኝ መስመር ተገኝቶ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ተቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ሪችሞንድ አዶንጎ እና እንዳለ ከበደ በግንባራቸው ለመጠቀም እጅግ ቀርበው ለጥቂት ሳይሳካላቸው ቀርቷል። አዲሰወ አበባዎች በሁለቱ ሙከራዎች ያላቆሙት ሲሆን በ51ኛው ደቂቃም አሰጋኸኝ ጼጥሮስ ከሳጥን ውጪ ሌላ ሙከራ አድርጎ ነበር።

ጫናዎች የበዛባቸው ቡናዎች በፈጣን ሽግግር ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው መሪነታቸውን ለማሳደግ ያገኙትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በ59ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ተስፋዬ ጎል አስቆጣሪው ዊሊያም ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት በመጠቀም ታፈሰ ጥሩ የቅጣት ምት መትቶ ዳንኤል ተሾመ አውጥቶታል። አጀማመሪ ጥሩ የነበረው ይህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ከግብ ሙከራዎች የራቀ ነበር። በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተቆራረጥ የኳስ ፍሰት ስንመለከት ደቂቃው ነጉዷል። ከረጅም ደቂቃዎች በኋላም ተቀይሮ የገበው አላዛር በ83ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የቡናን መሪነት ሊያሳድግ ነበር። በ87ኛው ደቂቃ ደግሞ አዲስ አበባ በእንዳለ አስደናቂ ሙከራ አድርጎ አቤል ሲያወጣው የተመለሰውን ኳስ ደግሞ ኤሊያስ በግንባሩ ሞክሮ ሥዩም ግብ ከመሆን አግዶታል። አዲስ አበባዎች በቀሪ ደቂቃዎችም አቻ ለመሆን ያላቸውን ሰጥተው ቢጫወቱም ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል። ኢትዮጵያ ቡናም በ33ኛው ደቂቃ ያስቆጠሩትን ጎል አስጠብቀው ጨዋታውን አገባደዋል።

ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ የራሳቸው ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጊዜያዊነት ከነበሩበት ዘጠነኛ ደረጃ ወደ አምስተኛ ከፍ ሲሉ እጅ የሰጡት አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ በ11 ነጥቦች ያሉበት 11ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።

ያጋሩ