ሪፖርት | አሰልጣኙን መልሶ ያገኘው ባህር ዳር አሸንፏል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በምሽቱ ጨዋታ አሰልጣኛቸውን ከአፍሪካ ዋንጫ መልስ ያገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ከጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጋር ከሦስት ጨዋታዎች በኃላ ወደ ድል የተመለሱበትን ውጤት ሀዋሳ ከተማ ላይ አስመዝግበዋል።

ባህር ዳር ከተማዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈው ስብስብ ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑሪ እና ተመስገን ደረሰን አስወጥተው በምትካቸው ፋሲል ገ/ሚካኤል እና ፉአድ ፈረጃን የተኩ ሲሆን ተጋጣሚያቸው ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ድሬዳዋን ከረታው ቡድን ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ዳዊት ታደሰ ወጥቶ በምትኩ አብዱልባሲጥ ከማልን ወደ ሜዳ አስገብተዋል።

ባህር ዳር ከተማዎች ከባለፉት ጨዋታዎች በተሻለ ድንቅ የነበረ የመጀመሪያ አጋማሽ ባሳለፉበት ጨዋታ ባህር ዳሮች የተሻለ የጨዋታ ቁጥጥር ነበራቸው ፤ ገና በሁለተኛው ደቂቃ ፍፁም ዓለሙ ካደረሰው ኳስ መነሻ አብዱልከሪም ኒኪማ ባደረጋት አስደናቂ ሙከራ ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን በአጋማሹ ኳሱን በተሻለ መጠን በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ተደጋጋሚ ጥረቶችን አድርገዋል።

በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች ይበልጥ በቁጥር በዝተው ለመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በሦስቱ ፈጣን አጥቂዎቻቸው ለመጠቀም ያሰቡ ቢመስልም ባህር ዳር ከተማዎች ኳስ በሚያጡበት ቅፅበት ሀዋሳዎች የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን እንዳይፈጥሩ በማድረግ ረገድ እንደ ቡድን ያደረጉት የተቀናጀ ጥረት አስደናቂ ነበር።

በ26ኛው ደቂቃ ባህርዳር ከተማዎች ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ ሳላዓምላክ ተገኝ ከግራ መስመር ወደ ፊት ያሻማውን ኳስ አዲስዓለም ተስፋዬ ቢመልስም የተመለሰውን ኳስ ሀዋሳ ከተማዎች በአግባቡ መከላከል አለመቻላቸውን ተከትሎ ያገኙትን አጋጣሚ አብዱልከሪም ኒኪማ ተጠቅሞ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ቀሪ ደቂቃዎች የግብ አጋጣሚዎችን መመልከት ባንችልም ሁለቱም ቡድኖች በተለይ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ይበልጥ ሀይል ቀላቅለው እንደመጫወታቸው ተደጋጋሚ ጥፋቶች የተመለከተን ሲሆን በዚህ ሂደት መነሻነትም የባህር ዳር ከተማው አለልኝ አዘነ እና አሀመድ ረሺድ በጉዳት መነሻነት ተቀይረው ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል።

ባህር ዳር ከተማዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ፍፁም ዓለሙ ባደረጋት እና መሀመድ ሙንታሪ ባዳነበት ኳስ ሁለተኛውን አጋማሽ ቢጀምሩም ቀስ በቀስ ግን ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ጨዋታው እያደጉ መምጣት ችለዋል።

ተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠር የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች ግን የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ጥድፊያ ውስጥ መግባታቸው የማጥቃት ሂደታቸው ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።

ታድያ ሀዋሳ ግብ ያስቆጥራል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ባህር ዳሮች ሳይጠበቁ መሪነታቸውን አሳድገዋል ፤ 72ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ፉአድ ፈረጃ ቄንጠኛ በሆነ መንገድ አስቆጥሮ ሳይጠበቅ ባህር ዳር ከተማዎች 2-0 እንዲመሩ አስችሏል።

በተቀሩት ደቂቃዎች ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥረው በመጫወት ከሙሉ ሥስት ነጥብ ጋር ከሦስት ሽንፈቶች በኃላ የታረቁት ባህር ዳር ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 17 በማሳደግ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችሉ በአንፃሩ ከመሪው ጋር የመስተካከል ዕድል የነበራቸው ሀዋሳ ከተማዎች በ20 ነጥብ አሁንም 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።