ቅድመ ዳሰሳ | አርባምንጭ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በነገው የጨዋታ ዕለት ምሽት ላይ በሚደረገው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ሀሳቦች አንስተናል።

ከወራጅ ቀጠናው ከፍ ብለው የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ከአደጋው ለመሸሽ ይፋለማሉ። ከተጋጣሚው አንፃር በሁለት ነጥቦች በልጦ የተቀመጠው ድሬዳዋ በጠባብ ውጤት ካስመዘገባቸው ሁለት ድሎች በኋላ በሀዋሳ ከተማ መሸነፉ ይታወሳል። የአርባምንጭ ከተማን የአሸናፊነት ትውስታ ለማግኘት ግን ሰባት ሳምንታትን ወደ ኋላ መሄድ ይጠይቃል።

ከውጤታማነት አንፃር ቡድኖቹ የመጡበት መንገድ ለጨዋታው ከፍ ያለ ግምት ባያሰጥም የጨዋታ ምርጫቸው ግን ጥሩ ፍልሚያ ሊሆን እንደሚችል ያመላክተናል። ይኸውም የድሬዳዋ ከተማ በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርቶ ዕድሎችን የመፍጠር አካሄድ እና የአርባምንጭ ከተማ ተጋጣሚን በራሱ ሜዳ ላይ ክፍተት በመንፈግ አጋጣሚዎችን የመፍጠር አቀራረብ ነው።

ድሬዳዋ ከተማ በመጨረሻው የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በተለይም በአጀማመሩ መተግበር የሚፈልገውን በትዕግስት ኳስ መስርቶ የመውጣት ሀሳብ ከከዚህ ቀደሙ በተሻለ ለመተግበር ሲሞክር ታይቶ ነበር። ሆኖም በሂደት የሀዋሳ ፈጣን ጥቃቶች እና ስኬታማ የቆመ ኳስ አጠቃቀም በእጁ የገባውን ውጤት አሳልፎ እንዲሰጥ አድርጎታል። አርባምንጭ ከተማዎችም እንዲሁ የሲዳማ ቡናን የኳስ ፍሰት ባለሙት መልኩ በጊዜ መግታት የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች የፈጠሩባቸው ቅፅበቶች ቢገኙም የማጥቃት ሽግግራቸው ድክመት ከውጤታማነት አርቋቸው ታይተዋል።

በነገው ጨዋታ ድሬዎች በሊጉ ጥሩ ጥሩ የመከላከል ቁጥር ካለው እና ከአንድ በላይ ግብ ተቆጥሮበት ከማያውቀው አርባምንጭ ጋር ሲገናኙ የቅብብሎቻቸው ጥራት ከአዞዎቹ የፊት መስመር ጫና የሚያልፍ ብሎም እስከ ግብ አፋፍ የሚያደርሳቸው መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል። ለዚህም በመስመር ተሰላፊዎቻቸው የሜዳውን ስፋት በመጠቀም ከመጀመሪያው ጫና ወጥቶ ፈጠን ባሉ ቅብብሎች ወደ ግብ መድረስ አንዱ አማራጫቸው ሊሆን ይችላል። ከሁሉም በላይ ግን ሁነኛ የጨዋታ አቀጣጣይ የሌለው ቡድኑ በሜዳው አጋማሽ ቅብብሎቹ እንዳይቋረጡ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊው ይሆናል።

አርባምንጮች እጅግ ትጋት የሚፈልገው ከኳስ ውጪ በተቻለ መጠን ጫና ፈጥሮ ተጋጣሚን አለማረጋጋትን በሚጠይቀው አጨዋወታቸው እስካሁን ያተረፉት ጠንካራ መከላከልን ነው። ሆኖም የነገ ተጋጣሚያቸው የሚፈልገውን የኳስ ቁጥጥር አጨዋወት ከመተግበር አንፃር ተፈላጊው ደረጃ ላይ የማይገኝ በመሆኑ አደጋ ሊፈጥሩ የሚችሉ ቦታዎች ላይ ኳስ የማስጣል ዕድሉ ይኖራቸዋል። ቀጣዩ ኳሶችን ወደ አደገኛ ዕድል መቀየር እና ግቦችን ማስቆጠር ላይ ግን እጅግ ተሻሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል። በተለያዩ ተጫዋቾች እየተሞከረ ያለው የፊት መስመራቸው የእስካሁኑ ብቃት ግን ለድሬ ተከላካዮች ራስ ምታት የመሆን ዕድሉ አነስ ያለ ይመስላል።

የድሬዳዋ ከተማዎቹ ጋዲሳ መብራቴ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና እንየው ካሳሁን ከጉዳታቸው ያላገገሙ ሲሆን ጋናዊው ተከላካይ አዉዱ ናፊዩም ከስብስቡ ጋር አይገኝም። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ደግሞ አንዷዓለም አስናቀ ጉሳት ላይ ሲገኝ ከሀቢብ ከማል በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት ጨዋታው ያልፈዋል።

ይህንን ጨዋታ ባህሩ ተካ በመሀል ዳኝነት ትንሳኤ ፈለቀ እና አብዱ ይጥና በረዳትነንት ተካልኝ ለማ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኘነት

– ቡድኖቹ ስምንት ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ 3 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ 2 አሸንፏል ፤ 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ አርባምንጭ 7 ፣ ድሬዳዋ ደግሞ 5 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ሙና በቀለ – በርናንድ ኦቺንግ – አሸናፊ ፊዳ – ተካልኝ ደጀኔ

ፀጋዬ አበራ – እንዳልካቸው መስፍን – አቡበከር ሸሚል – አሸናፊ ኤሊያስ

ራምኬል ሎክ – ኤሪክ ካፓይቶ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

ዐወት ገብረሚካኤል – አቤል አሰበ – መሳይ ጳውሎስ – ሄኖክ ኢሳይያስ

ዳንኤል ደምሴ – ዳንኤል ኃይሉ

አብዱርሀማን ሙባረክ – ሱራፌል ጌታቸው – አብዱለጢፍ መሀመድ

ሙኸዲን ሙሳ

ያጋሩ