ቅድመ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ወላይታ ድቻ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከድል መልስ እርስ በእርስ የሚገናኙት መከላከያ እና ወላይታ ድቻ የሚያደርጉትን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ድል ያደረጉት መከላከያዎች ጠፍቶባቸው ባገኙት የአሸናፊነት መንገድ ለመዝለቅ ከሌላኛው ከድል መልስ ከመጣው ወላይታ ድቻ ጋር መፋለም የግድ ይላቸዋል።

ከጅማ አባጅፋር ጋር በጣምራ በሊጉ ትንሽ ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረ ክለብ የሆነው መከላከያ ወልቂጤ ከተማን ከመመራት ተነስቶ 3-1 ሲያሸንፍ ያሳየው ብቃት ብዙዎች ያልጠበቁት ነበር ብሎ ማስቀመጥ የሚያስማማ ይመስላል። በተለይ በኳስ ቁጥጥር እና ተጋጣሚን አስጨንቆ በመጫወት ረገድ ክፍተት የሚታይበት ስብስቡ በጨዋታው ግን በሁሉም የሜዳ ክፍሎች የበላይ ለመሆን ሲጥር አስተውለናል። ከምንም በላይ ደግሞ በተነሳሽነት እና በፍላጎት ረገድ ታይቶ የማያውቀው ስሜት ተስተውሎባቸው በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ጠንካራ ሆነው አሳልፈዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በተደጋጋሚ በቢኒያም በላይ ላይ የተንጠለጠለ የማጥቃት አጨዋወት የሚከተለው ቡድኑ በጨዋታው በመስመሮችም ሆነ በመሐል በሚደረጉ ክፍት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በረጃጅም ኳሶች የግብ ምንጭ ሲፈጥሩ ነበር። ከዚህ በፊት የሌለውን ድፍረትም ተላብሰው በቁጥር በርከት ብለው ለማጥቃት ሲዳዱ ነበር። ይህ የጨዋታ ሀሳብ ለውጥም ነገም እንደሚቀጥል ይገመታል።

ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ድል ያደረገው ወላይታ ድቻ በበኩሉ በተከታታይ ያሸነፋቸውን ጨዋታዎች ወደ ሦስት ከፍ በማድረግ በመልካም ጉዞ ለመዝለቅ እና በደረጃ ሰንጠረዡ እድገት ለማምጣት ከመከላከያ የሚጠብቃቸውን ጠንካራ ፈተና ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ሆነው ከሚያውቁ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ወላይታ ድቻ ወቅታዊ ብቃቱ ጥሩ ይመስላል። በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ ከተረታ በኋላ ተከታታይ አምስት ጨዋታዎችን ያሸነፈበትን ብቃትም ደግሞ ያገኘ ይመስላል። ቡድኑ አዲስ አበባን 2-1 ሲረታ የሽርፍራፊ ሰከንድ ክስተት አስፈላጊ እንደነበር ይታወሳል። በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የመጀመሪያ አሰላለፍ ሲጠቀሙ የሚታዩት አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምም በጨዋታው አናጋው ባደግን በቅጣት አጥተው ተመሳሳይ አጨዋወት ተከትለው ሦስት ነጥብ ሸምተዋል። እንደውም ከዚህ ቀደም መገለጫቸው ከሆነው ቀጥተኛ አጨዋወት መጠነኛ የኳስ ቁጥጥር ፍላጎት አሳይተው ነበር። የነገ ተጋጣሚያቸው መከላከያም በአብዛኛው እንደእነርሱ ለቀጥተኝነት ቅድሚያ የሚሰጥ ስለሆነ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል ይታመናል። ከዚህ ውጪ ግን እንደተለመደው የስንታየሁን ቁመት ዒላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች እና ፈጣኖቹን የመስመር አጥቂዎች ቃልኪዳን እና ምንይሉን ያማከሉ ሽግግሮች ለግብ ማስቆጠሪያነት ሊጠቀሙ ይችላሉ።

ከላይ እንደገለፅነው መከላከያ ባሳለፍነው ጨዋታ በ10 ጨዋታዎች ካስቆጠራቸው ግቦች የተቃረበ (3) ጎሎችን ማስቆጠሩ ጎል ፊት መሻሻል እንዳሳየ ቢጠቁምም ይህ መሻሻል መቀጠል ይገባዋል። የነገ ተጋጣሚው ደግሞ በመከላከል ቅርፅ ጠጣር ስለሆነ ግብ ለማግባት ቀላል እንደማይሆንለት ይታሰባል። ከሊጉ መሪ ጊዮርጊስ እኩል 6 ጨዋታዎችን እስካሁን ያሸነፈው ወላይታ ድቻ ደግሞ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ቀድሞ ግብ ከተቆጠረበት ምላሽ በመስጠት አሸናፊ መሆን ተስኖታል። ይህንን ተከትሎም መከላከያ በጥሩ ተነሳሽነት ላይ ያለ በመሆኑ በተነሳሽነት ቀድሞ ግብ እንዳያስተናግድ መጠንቀቅ አለበት። ከዚህ አልፎም ከቀጥተኛ አጨዋወት ባለፈ የመከላከያን የኋላ መስመር ማስከፈቻ ስልት መንደፍ እንደሚገባው እሙን ነው።

መከላከያ በነገው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች እንደሌለ ሲመላከት ወላይታ ድቻ ደግሞ እድሪስ ሰዒድ ጉዳት በማስተናገዱ አማካዩን በጨዋታው የማያገኝ ይሆናል።

ይህንን ጨዋታ አልቢትር አሸብር ሰቦቃ በመሐል ዳኝነት ሲመሩት ትግል ግዛው እና ፍሬዝጊ ተስፋዬ ረዳት ሄኖክ አክሊሉ ደግሞ አረተኛ ዳኛ ሆነው እንዲያገለግሉ መመደባቸውን አውቀናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች 12 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 5 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መከላከያ 3 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 4 ግንኙነቶች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። የጦና ንቦች 14፣ ጦሩ 12 ግቦችን በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-2-3-1)

ክሌመንት ቦዬ

ልደቱ ጌታቸው – ኢብራሂም ሁሴን – አሌክስ ተሰማ – ዳዊት ማሞ

ኢማኑኤል ላርዬ – ግሩም ሀጎስ

ሰመረ ሀፍተይ – ቢኒያም በላይ – ብሩክ ሰሙ

ተሾመ በላቸው

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ወንድወሰን አሸናፊ

ያሬድ ዳዊት – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – አናጋው ባደግ

አዲስ ህንፃ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሐብታሙ ንጉሤ

ቃልኪዳን ዘላለም – ስንታየሁ መንግስቱ – ምንይሉ ወንድሙ

ያጋሩ