​የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከተቋረጠበት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ለኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የተቋረጠው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድር የሚጀመርበት ቀን ይፋ ሆኗል።

የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድር የተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር ወደ 13 አሳድጎ ከታህሣሥ 16 ጀምሮ ሲከናወን እንደነበረ ይታወቃል። በሀዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም የአራት ሳምንታት ጨዋታዎችን ያከናወነው ሊጉም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነት ለኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ፍልሚያዎች ታህሣሥ 29 ተቋርጦ ነበር። ብሔራዊ ቡድኑም በአራተኛ ዙር ማጣሪጣ የታንዛኒያ አቻውን በደርሶ መልስ ጨዋታ 2-1 አሸንፎ ወደ መጨረሻው ዙር ጨዋታ ማለፉን ተከትሎ የሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ውድድር የመጀመሪያው ቀን ዳግም ተራዝሟል።

ለእድሜ እርከን ብሔራዊ ቡድን ዋናው ሊግ መቋረጡ አግራሞትን የሚጭር ጉዳይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሊጉ መጋቢት 24 እንዲቀጥል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽ እንደወሰነ አውቀናል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የ2013 የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድር የተገባደደው መጋቢት 19 መሆኑ እና የዘንድሮ ውድድር ገና የ5ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ማድረግ የሚጀምረው መጋቢት 24 መሆኑ ሲታወስ ሊጉ ምን ያህል በወጥነት እየተደረገ እንዳልሆነ ያመላክታል።

በሌላ ዜና የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ኮከቦች እስካሁን እውቅና ሳይሰጣቸው መቆየቱ የሊጉን የበላይ አካል (የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን) እያስተቸ ይገኛል። ለሴቶች ሊግ ብቻ ሳይሆን በወንዶቹም ይህ የተለመደው የዓመቱ ኮከቦች ሽልማት ከቅጥ በላይ መዘግየቱ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።