[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
መከላከያን በአንተነህ ጉግሳ ብቸኛ ግብ መርታት የቻለው ወላይታ ድቻ በሦተኛ ተከታታይ ድል ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።
መከላከያ ከወልቂጤ ከተማው ድል ልደቱ ጌታቸውን በታዳጊው ኢብራሂም መሐመድ ሲተካ ምንይሉ ወንድሙ እና እንድሪስ ሰዒድ ደግሞ ወላይታ ድቻ አዲስ አበባን ከረታበት ጨዋታ በአናጋው ባደግ እና አዲስ ህንፃ የተተኩ ተጫዋቾች ሆነዋል።
በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል ፈጠን ባለ ሽግግር ወደ ግብ ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶች እየታዩበት የጀመረው ጨዋታ በጊዜ ግብ አስተናግዷል። 7ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ህንፃ ከቃልኪዳን ዘላለም የማዕዘን ምት የተቀበለውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ሳጥን ውስጥ ለነበረው አንተነህ ጉግሳ ሲያሳልፍለት የመሀል ተከላካዩ በተዘናጉት የመከላካያ ተከላካዮች መሀል ራሱን ነፃ በማድረግ ጎል አድርጎታል።
በፍጥነት መሪ መሆን የቻሉት ወላይታ ድቻዎች ከግቡ በኋላ የማጥቃት ጥረታቸው ቀነስ ብሎ ሲታይ መከላከያዎች ደግሞ አቻ ለመሆን መጠነኛ ጫና ፈጥረዋል። ነገር ግን የቡድኑ ሙከራዎች ከሳጥን ውጪ እና ከቆመ ኳስ የመነጩ ብቻ ሆነዋል። 14ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ሰሙ ኢማኑኤል ላሪያ የድቻን ማጥቃት አቋርጦ ካቀበለው ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ ወንድወሰን አሸናፊ አድኖበታል። 21ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ግሩም ሀጎስ የግሉ ከሆነው ከግራ ወዳደላ ቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ጨርፎ ወጥቷል።
ከውሀ ዕረፍቱ በኋላ ጦሩ በተሻለ ሁኔታ የማጥቃት ሂደቶችን ለመጀመር ሲጥሩ ይታይ ነበር። ሆኖም ወላይታ ድቻዎች በቶሎ የመከላከል ቅርፃቸውን በመያዝ የጦሩን ፍጥነት የሌለው የኳስ ምስረታ በየቦታው ላይ በሚፈጥሩት የቁጥር ብልጫ ደጋግመው በቶሎ ለማቋረጥ ችለዋል። 34ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ይነሳ የነበረው ቢኒያም በላይ ከርቀት ያደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ የአጋማሹ ሌላኛው የተሻለ የመከላከያ ዕድል ሆኖ አልፏል።
ከዕረፍት መስልም የመከላከያ የግብ ፍለጋ ቀጥሏል። ቀዳሚው አደገኛ ሙከራ ግን በድቻ በኩል የታየ ነበር።48ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወልደዮሐንስ ከአዲስ ህንፃ የግራ ቅጣት ምት በግንባር ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። በግሩም ሀጎስ ሌላ የ52ኛ ደቂቃ የቅጣት ምት ሙከራ ያደረጉት መከላከያዎች በማጥቃት ሂደት መስመር ላይ በድቻ ተጫዋቾች የሚወሰድባቸው ብልጫ ቀጥሎ ታይቷል። 60ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ ቢኒያም በላይ ከግራ ከሁለት የድቻ ተጫዋቾች ጋር ታግሎ ያሻማውን ኳስ ኢብራሂም መሐመድ አብርዶ ለመምታት ሲዘጋጅ አጥቂው ተሾመ በላቸው ቀደሞ ወደ ግብ ልኮት በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በአዲስ ህንፃ ተቀይሮ የገባው አበባየሁ አጪሶ የድቻን መልሶ ማጥቃት ፈጠን ማድረግ ሲችል 69ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ካስ ከቀኝ ወደ ሳጥን አድርሶ ስንታየሁ መንግሥቱ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ውጤት ከማስጠበቅ ይልቅ የማጥቃት ቅያሪዎችን በማድረግ ሌላ ግብ ፍለጋ በመልሶ ማጥቃት መሄድን መርጫቸው ያደረጉት ድቻዎች የጦሩን የመጨረሻ ደቂቃዎች የጫና ጥረት ከረጅም ርቀት ሙከራዎች እንዳይዘል ማድረግ ችለዋል። በዚህም የ1-0 ውጤታቸውን አስጠብቀው ጨዋታውን ፈፅመዋል።
የጦና ንቦቹ ያሳኩትን ተከታታይ ሦስተኛ ድል ተከትሎ ነጥባቸውን ከፋሲል ከነማ ጋር በማስተካከል ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።