የኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ዛሬም በሦስት ከተሞች በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች ቀጥሎ ውሏል።
የ 07፡00 ጨዋታዎች
በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም መቻል እና ወልቂጤ ከተማ ሲገናኙ ቀዝቃዛ በነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በነበራቸው መቻሎች በኩል ምንይሉ ወንድሙ 6ኛው ደቂቃ ላይ በግቡ የቀኝ ቋሚ የተመለሰ 19ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ሞክሮት በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት በወጣበት ኳስ ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ሲያደርግ 33ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ዮሐንስ መንግሥቱ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የሞከረውን ኳስ የሠራተኞቹ ግብ ጠባቂ ናትናኤል ጃምቦ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል። በ ‘ደሞዝ አልተከፈለንም’ ቅሬታ በርካታ ቋሚ ተጫዋቾችን ያላገኘው እና በታዳጊ ተጫዋቾች ለመግባት በተገደደው ወልቂጤ ከተማ በኩልም የተሻለው የግብ ዕድል 41ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጠር በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም መሐመድ ናስር በዓየር ላይ እንዳለ ሞክሮት በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶበታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ይበልጥ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች አይፈጠሩ እንጂ በኳስ ቁጥጥሩ ሰፊ ብልጫ የነበራቸው መቻሎች 63ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ዳዊት ማሞ በሳጥኑ የግራ ክፍል እየገፋ የወሰደውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። በቀሪ ደቂቃዎችም መቻሎች ተጨማሪ ግብ የሚያስቆጥሩበትን ዕድል ፈጥረው ግሩም ሀጎስ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ናይጄሪያዊው አጥቂ ቺጂኦኬ ናምዲ አኩኔቶ ተገልብጦ ያደረገውን ግሩም ሙከራ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል። ጨዋታውም በመቻል 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
አዳማ ላይ ዕድለኛ ያልነበሩት ኦሮሚያ ፖሊስ በአርባምንጭ ከተማ በመለያ ምት በተሸነፉበት የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ በሁለቱም በኩል ረጃጅም ኳሶች እየበዙበት ጅማሬውን እያደረገ ቢቀጥልም 14ኛው ደቂቃ የጨዋታው የመጀመርያ ጎል ተገኝቷል። ሀብታሙ መስፍን ከቀኝ መስመር በተካላካዮች መሐል አፈትልኮ በመውጣት በጥሩ መንገድ ያሻገረውን አጥቂው ዳንኤል ዳርጌ ኳሱን ተረጋግቶ በመቆጣጠር ኦሮምያ ፖሊስን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።
ያልጠበቁት ብልጫ የተወሰደባቸው አርባምንጮች በመሪሁን መስቀላ ከሳጥን ውጭ በተመታ ኳስ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ቢሞክሩም ከዚህ የተሻለ ዕድል በአጋማሹ መፍጠር ሳይችሉ ሲቀሩ ኦሮሚያ ፖሊሶች ጨዋታውን በሚፈለጉት መልኩ ተቆጣጥረው ወጥተዋል።
ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ በሙሉ አቅማቸው ወደ ማጥቃት የገቡት አርባምንጮች በ56ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን በቀኝ መስመር ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተጫዋች በመቀነስ አመቻችቶ ያቀበለውን ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ተገኝ ወደ ጎልነት ቀይሮት ቡድኑን አቻ አድርጓል።
ከጎሉ በኋላ አርባምጮች ሲቀዛቀዙ በአንፃሩ ኦሮምያ ፖሊሶች ብልጫ ወስደው መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን በአንድ አጋጣሚ እጅግ ለጎል የቀረበ አጋጣሚ ልዑልሰገድ አለምዬ ያልተጠቀመበት ኳስ የሚያስቆጭ ነበር። ጨዋታውም በአንድ አቻ ውጤት በመጠናቀቁ በተሰጠው መለያ ምት አርባምንጭ ከተማ 10-9 በማሸነፍ ወደ ተከታዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።
ሀዋሳ ሠው ሠራሽ ሜዳ ላይ የተከናወነው የሻሸመኔ ከተማ እና ካፋ ቡና የጥሎ ማለፉ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ያለ ጎል በመጠናቀቁ በተሰጠው የመለያ ምት ሻሸመኔ ከተማ 5ለ4 በማሸነፍ ወደ ሦስተኛው ዙር አልፏል።
የ 09፡30 ጨዋታዎች
አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ኢትዮጵያ ቡና እና ወልዲያ ሲገናኙ ጨዋታው በተጀመረ በ 2ኛው ደቂቃ ቡናማዎቹ ግብ አስቆጥረዋል። በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ ከአንድ ጊዜ መቋረጥ በኋላ ያገኘው ብሩክ በየነ ከሳጥን ውጪ በአስደናቂ ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ መረቡ ላይ አርፏል። ወልዲያዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት በማድረግ በተለይም ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። ሆኖም ግን 27ኛው ደቂቃ ላይ ልፋታቸው ላይ ውሃ የሚቸልስ አጋጣሚ ተፈጥሮባቸዋል። ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ብሩክ በየነ ግብ ጠባቂውን በግራ በኩል ጥሎ በቀኝ አስቆጥሮታል። በአጋማሹ የመጨረሻ 10 ደቂቃዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ወልዲያዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ቢኒያም ላንቃሞ በግሩም ክህሎት ባመቻቸው ኳስ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥም ወልዲያዎች ተጨማሪ ወርቃማ ዕድል ፈጥረው ከቢኒያም ላንቃሞ በተሰጠነቀለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው በኃይሉ ተስፋዬ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ግለት በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል ሁለቱም ቡድኖች በሚያገኙት ኳስ ሁሉ በፈጣን ሽግግር ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። 55ኛው ደቂቃ ላይም አማኑኤል ዮሐንስ ተቀይሮ በገባበት ቅፅበት ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ጫላ ተሺታ ግብ አድርጎታል። በአራት ደቂቃዎች ልዩነትም የወልዲያው በኃይሉ ተስፋዬ በተሰነጠቀለት ኳስ በድጋሚ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ኳሱን በረከት አማረ መልሶበታል። መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት የቀጠለው ጨዋታም ሊጠናቀቅ የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅ መሐመድኑር ናስር የወልዲያው ግብ ጠባቂ ስንታየሁ ታምራት በሠራው ስህተት ያገኘውን ኳስ በቀላሉ አስቆጥሮት ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም አዲስ የተቋቋመውን ሸገር ከተማ እና ባህር ዳር ከተማን ቀጥሎ ባገናኘው ሁለተኛ ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ አስመልክቶን በጣና ሞገዶቹ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል። በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ የተሻሉ የነበሩት ሸገሮች ፋሲል አስማማው ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ብቻውን ከግብጠበቂ ጋር ተገናኝቶ ወደ ጎልነት ቀየረው ሲባል በቀላሉ ያመከነው ኳስ ለወሰዱት ብልጫ ጥሩ ምላሽ የሚሆን ነበር።
አልፎ አልፎም ቢሆን ባልተደራጀ ሁኔታ የጎል ዕድል ለመፍጠር የሞከሩት ባህርዳሮች በአባይነህ ፌኖ እና በሱሌማን ትራኦሬ አማካኝነት ጥቃት ሰንዝረው የነበረ ቢሆንም ወደ ጎልነት መቀየር አልቻሉም። ይህም ቢሆን በጨዋታውን መምራት የቻሉበትን ጎል በ39ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በተቃራኒው የማዕዘን ምት መምቻው በረጅሙ የሄደውን ኳስ ፍሬዘር ካሳ አግኝቶ ከሳጥን ውጭ ካልተጠበቀ አቅጣጫ ግሩም ጎል አስቆጥሯል። ወደ ዕረፍት መዳረሻ ላይ የሸገሩ አላዛር ሽመልስ ቡድኑን አቻ ማድረግ የሚችል ኳስ ከፋሲል አስማማው ተቀብሎ ወደ ጎል ቢመታውም ግብጠባቂው አላዛር እንደምንም አድኖበታል።
በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ዕረፍት አልባ ምልልሶች የተከናወኑበት ማራኪ እንቅስቃሴ አስመልክቶናል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ሸገሮች ተቀይሮ የገባው ዱላ ሙላቱ ሳጥን ውስጥ ኳስ አግኝቶ ወደ ጎል የመታው ግብጠባቂውን አላዛርን ቢያልፍም ተከላካዩ መሳይ አገኘሁ ያወጣበት እንዲሁም በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አላዛር ሽመልስ ያመከነው ለቡድኑ ጥሩ የጎል አጋጣሚዎች ነበሩ። የባህር ዳሩ መሳይ አገኘሁ የጨዋታው መጠናቀቂያ አስር ደቂቃ ሲቀረው በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ የቁጥር ብልጫውን ለመጠቀም ሸገሮች ወደፊት በመሄድ መንቀሳቀስ ቢችሉም ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ በመሆን የጣና ሞገዶቹ አጥቂ ሱሌማን ትራኦሬ በቀላሉ የሚያመክናቸው ኳሶች ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድባቸው በጨዋታው ተሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።
በሀዋሳ ሠውሠራሽ ሜዳ በረዳት አሰልጣኙ አረጋዊ ወንድሙ መሪነት ጨዋታውን በሜዳው ያደረገው ሲዳማ ቡና በአዳማ ከተማ አራት ግቦችን አስተናግዶ ሽንፈት ቀምሷል። በመጀመሪያው የጨዋታ ደቂቃ 16ኛው ደቂቃ ላይ ሙሴ ኪሮስ ከቢኒያም አይተን የደረሰውን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጦ አዳማን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። አጋማሹ ሊገባደድ 41ኛ ደቂቃ ላይ መስዑድ መሐመድ የሲዳማ ተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ ከቀኝ የሲዳማ የግብ ክልል የደረሰውን ኳስ በተረጋጋ መልኩ ጎል በማድረግ የአዳማን የግብ መጠን ወደ ሁለት አሳድጓል። ጨዋታው ከዕረፍት ተመልሶ ሲቀጥል ከራስ ሜዳ ኳስን በማስጀመር 51ኛው ደቂቃ ላይ መሐሪ መና የአዳማ አጥቂዎች የፈጠሩት ጫና ለማረጋጋት ወደ ኋላ የመለሰውን ኳስ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ ኳሷ ሾልካ መረቡ ላይ አርፋ የግቦቹ መጠን ወደ 3ለ0 ተሸጋግሯል። መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ሰዓት ተቀይሮ የገባው ነቢል ኑሪ በጥሩ ቅብብል ራሱ ያስጀመራትን ኳስ በማስቆጠር ጨዋታው በአዳማ ከተማ 4ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል። በውጤቱም አዳማ ከተማ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።