​ሪፖርት | አዞዎቹ እና ብርቱካናማዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከደቂቃዎች በፊት በተጠናቀቀው ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ከሲዳማ ቡና ጋር አንድ ነጥብ ተጋርተው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት አርባምንጭ ከተማዎች ከመጨረሻው ጨዋታ በላይ ታደሰን በአብነት ተሾመ እንዲሁም ፀጋዬ አበራን በደረጄ ፍሬው ምትክ ወደ ሜዳ ሲያስገቡ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ አስገራሚ ከነበረው የሀዋሳ ጨዋታ ዳንኤል ኃይሉ እና ቢኒያም ጥዑመልሳንን አሳርፈው ብሩክ ቃልቦሬ እና አቤል ከበደን በመጀመሪያ አሰላለፍ አካተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

በርከት ባሉ የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች ታጅቦ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና በጊዜ ጥሩ ፉክክር ማስመልከት ይዟል። በ5ኛው ደቂቃ ደግሞ የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ተፈጥሯል። በዚህም በረጅሙ የተላከን ኳስ የአርባምንጭ ተጫዋቾች በሚገባ ማፅዳት ሳይችሉ አብዱለጢፊ መሐመድ አግኝቶት ወደ ግብ ሲልከው አብዱረህማን ሙባረክ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ያለቀለት አጋጣሚ አድርጎት ለጥቂት ወጥቶበታል። ከ10 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አርባምንጭ ከመልስ ውርወራ የተነሳን ኳስ አቡበከር ሻሚል በአስገራሚ የግል ብቃት ኳስ እየገፋ ተከላካዮችን ቀንሶ ወደ ቀኝ ያደላ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ተገኝቶ የፈጠረውን አጋጣሚ በላይ ታደሰ ከብርቱካናማዎቹ ተከላካይ ጋር ታግሎ ለመጠቀም ቢጥርም ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ቀርቷል።

ወደ ግብ በመድረስ ረገድ የተሻሉት አርባምንጮች በ19ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ወደ ድሬ የግብ ክልል ደርሰው ሙና በቀለ አሻምቶት ኤሪክ ካፓይቶ በግንባሩ በሞከረው ኳስ መሪ ሊሆኑ ነበር። ቶሎ ቶሎ ኳስ መነጣጠቅ የበዛበት ጨዋታው ቀጥሎ በ32ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ የመዓዘን ምት አስተናግዶ ሌላ ጥቃት ተደርጎበታል። በዚህም ድሬዳዋን መፈተን የቀጠሉት አዞዎቹ በበላይ አማካኝነት የግብ ዘቡን ፍሬው ፈትነዋል። እንደ አጀማመሩ ያልዘለቀው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጨማሪ ሙከራ ሳያስተናግድ ያለ ግብ ተጠናቋል።

አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ አጋማሹን ያገባደዱት ድሬዳዋዎች በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው በማስገባት ቀዳሚ ለመሆን ጥረዋል። በ48ኛው ደቂቃም ተቀይሮ የገባው ዳንኤል ኃይሉ ከቅጣት ምት ኳስ አሻምቶ ዳንኤል ደምሱ በግንባሩ ለማስቆጠር ዳድቶ ነበር። ተሻሽለው የቀረቡት ድሬዳዋዎች የሚያደርጉትን ጫና መመከት ላይ ተጠምደው የታዩት የአርባምንጭ ተጫዋቾች በ56 እና 57ኛው ደቂቃ በራምኬል ሎክ እና በርናንድ ኦቺንግ አማካኝነት ኳስን ከመረብ ሊያዋህዱ ነበር። ነገርግን ሁለቱንም አደገኛ ኳሶች ፍሬው ጌታሁን አምክኗቸዋል።

ማማዱ ሲዲቤን ወደ ሜዳ ያስገባው ድሬዳዋ በ76ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጓል። በዚህም ቁመታሙ አጥቂ በደረቱ ያመቻቸውን ኳስ አብዱረህማን ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶት ነበር። ይሁ አጥቂ በ81ኛው ደቂቃም የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ተከላካዮችን በማለፍ ወደ ግብ የመታው ኳስ በአስቆጪ ሁኔታ ዒላማውን ስቷል። እንደ መጀመሪያው አጋማሽ መንቀሳቀስ ያልቻሉት የአሠልጣኝ መሳይ ተጫዋቾች ረጃጅም ኳሶችን ለግብ ምንጭነት ለመጠቀም ቢንቀሳቀሱም ውጥናቸው እምብዛም ሲሰምር አልታየም። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ የአርባምንጩ ተካላከይ በርናንድ ኦቺንግ የዳኛን ውሳኔ በመቃወም ሁለተኛ ቢጫ ካርድ አይቶ (ቀድሞ በ52ኛው ደቂቃ ቢጫ አይቶ ነበር) ከሜዳ እንዲሰናበት ሆኗል። ጨዋታውን ያለ ግብ 0-0 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 13 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 15 ቢያደርሱም በደረጃ መሻሻል ሳያሳዩ በቅደም ተከተል 13ኛ እና 11ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።

ያጋሩ