[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በወልቂጤ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል የሚደረገው የነገ ጨዋታ እንዲህ ተቃኝቷል።
በደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ላይ የተቀመጡት ወልቂጤ ከተማዎች እየመሩ በመከላከያ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ነገ ሦስት ነጥብ የሚያገኙበትን መንገድ እያሰላሰሉ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ከሁለት በላይ ጎሎችን በጨዋታ ተጋጣሚ ላይ ከሁለት ጊዜ የበለጠ ያላስቆጠረው ወልቂጤ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንትም አንድ ግብ ብቻ አስቆጥሮ ጨዋታን መግደል ሳይችል በመቅረት እጁ የገባውም ሦስት ነጥብ አሳልፎ ሰጥቷል። ጌታነህ ከበደን የሚያክል ሥል የሳጥን ውስጥ አጥቂ እና አብዱልከሪም ወርቁን የመሰለ የአጥቂ አማካኝ እንዲሁም ፈጣን የመስመር አጥቂዎች ያለው ቡድኑም በአንፃራዊነት እንዳለው ስብስብ ድፍረት ወስዶ ሲጫወት አይስተዋልም። በአመዛኙም የቆሙ እና ተሻጋሪ (ረጃጅም) ኳሶችን ለግብ ምንጭነት ሲጠቀም ይታያል። ይህ አጨዋወት ለቡድኑ አዎንታዊ ውጤት እያስገኘው ቢሆንም በክፍት ጨዋታ ሳይገመት ግቦችን ለማግኘት መታተር እንዳለበት ይታመናል። ከዚህ በተጨማሪም ነገ የመስመር ተከላካዮቹ በማጥቃቱ ረገድ ፍቃድ ተሰጥቷቸው ሜዳውን አስፍተው የጊዮርጊስ ተከላካዮች እንዲለጠጡ በማድረግ ክፍተቶች እንዲገኙ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ወልቁጤ በዚህ ሰዓት የሚያሳስበው ዋነኛው ነገር የግብ ዘብ ጉዳይ ይመስላል። አይቮሪኮስታዊው ግብ ጠባቂ ሲልቫይን ግቦሆ በፊፋ መቀጣቱን ተከትሎ ቦታውን ያገኘው ሰዒድ ሀብታሙ በጨዋታ ላይ የሚሰራቸው ስህተቶች ቡድኑን ዋጋ እያስከፈለው ነው። በመከላከያ ሲረቱም ግብ ጠባቂው ሁለቱ ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ስህተት ሰርቶ ነበር። በተለይ ተሻጋሪ ኳሶችን ለማምከን የሚወስናቸው ጊዜያቸውን ያልጠበቁ ውሳኔዎች እና መጠነኛ የትኩረት ክፍተቶች ለተጋጣሚ አጥቂዎች የልብ ልብ እየሰጠ ነው። ለዚህ ማጠናከሪያ ደግሞ ሰዒድ መሰለፍ ከጀመረ በኋላ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ብቻ ቡድኑ ላይ የተቆጠሩት ግቦች በውድድር ዓመቱ ከተቆጠሩት 63.6 % (7) የሚሆኑ ናቸው። የነገ የቡድኑ ተጋጣሚ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ጎል ፊት ስል ስለሆነ ይህንን ችግር እንዴት ይቀርፉታል የሚለው የሚጠበቅ ነው።
የወቅቱ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስሩ የሚገኙት ፋሲል እና ሀዋሳ ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን ለማጥበብ እና ያለመሸነፍ ሪከርዱን ወደ 12 ከፍ ለማድረግ ከሽንፈት መልስ ከመጣው ወልቂጤ ቀላል ፈተና እንደማይጠብቀው ይታመናል።
እስካሁን አንድም ጨዋታ ያልተሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወቅታዊ ብቃቱ እጅግ ጥሩ ይመስላል። አራት ተከታታይ ጨዋታዎችንም አሸንፏል። በተለይ በወረቀት ላይ የዋንጫ ተፎካካሪ ተደርገው የሚወሰዱትን ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማን ያሸነፈበት መንገድ ብዙዎችን ጠንካራ ብቃቱ ላይ እንዳለ ያሳመነ ነበር። በዋናነት ደግሞ የሚገኙ ኳሶችን በቶሎ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመውሰድ ፍሬያማ ለማድረግ ሲጥር ይታያል። በዚህ ሂደት ሦስቱ አጥቂዎች (አጎሮ፣ አማኑኤል እና አቤል) ፍጥነታቸውን በመጠቀም የተጋጣሚን ተከላካዮች ለማስጨነቅ የሚያደርጉት ጥረት የሚደነቅ ነው። ነገም ካስቆጠሩት ጎል እኩል ግብ ያስተናገዱትን (11) ወልቂጤዎች ለማስከፈት በአመዛኙ ቀጥተኛ አጨዋወትን ሊከተሉ እንደሚችሉ ቀድሞ መናገር ይቻላል።
በሊጉ ትንሽ ግቦችን ያስተናገደ ክለብ የሆነው ጊዮርጊስ ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች ከተሰነዘሩበት 11 ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች አንዱንም አላስተናገደም። እንደውም በሁለቱ ጨዋታ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያስተናግድ ነበር የወጣው። ይህ ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ ግን በሽግግሮች ወቅት ፈጣን የሆኑትን የወልቂጤ አጥቂዎች ጥቃት ነገ ለማቆም ጥሩ ዘዴ ማሰላሰል ይጠበቅበታል። በተለይ የቀድሞ አጥቂያቸው ጌታነህ የተጋጣሚ ተከላካዮችን እየሳበ ወደ መሐል ሜዳ በመምጣት ለአጋሮቹ ሁለተኛ ኳስ እና ክፍት ሜዳ ለማመቻቸት የሚጥርበትን መንገድ ማስወገድ አለባቸው።
ወልቂጤ ከተማ በፊፋ ቅጣት ከተላለፈበት ሲልቪያን ግቦሆ ውጪ በነገው ጨዋታ የሚያጣው ተጨዋች የሌለ ሲሆን ጉዳት ላይ የነበረው አቡበከር ሳኒም ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ልምምድ መጀመሩ ለቡድኑ መልካም ዜና ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ሀይደር ሸረፋን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ ከነዓን ማርክነህን እና አዲስ ግደይን ግን በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ ማድረጉ ተጠቁሟል።
ኃይለየሱስ ባዘዘው ጨዋታውን በመሐል አልቢትርነት ሲመሩት ይበቃል ደሳለኝ እና ካሳሁን ፍፁም የመስመር ረዳት ዳኞች ማኑሄ ወልደፃዲቅ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው እንደሚያገለግሉ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ግምታዊ አሠላለፍ
ወልቂጤ ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)
ሰዒድ ሀብታሙ
ተስፋዬ ነጋሽ – ዮናስ በርታ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ
ሀብታሙ ሸዋለም
ያሬድ ታደሰ – ጫላ ተሺታ
አብዱልከሪም ወርቁ
ጌታነህ ከበደ – አህመድ ሁሴን
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)
ቻርለስ ሉክዋጎ
ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሔኖክ አዱኛ
የአብስራ ተስፋዬ – ጋቶች ፓኖም – ሀይደር ሸረፋ
አቤል ያለው – እስማኤል አውሮ-አጎሮ- አማኑኤል ገብረሚካኤል