የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ሲመለስ የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
ሁለት ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ወደ ሜዳ የሚገቡ ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ የሊጉን መመለስ ያበስራል።
በአራት ነጥቦች በአስራ ሁለተኛ ደረጃነት የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ከአምስቱ ጨዋታዎች በሦስቱ ሽንፈት ሲያስተናገዱ በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ድልና የአቻ ውጤቶች አስመዝግበዋል። ብርቱካናማዎቹ በመጀመርያው ሣምንት ሀምበሪቾን ካሸነፉ በኋላ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት አልቻሉም። ከሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ ሲለያዩ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በአዳማ ከተማ ሽንፈት አስተናግደዋል። በመጨረሻዎቹ አራት የሊጉ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦችም አንዱን ብቻ አሳክተዋል። በመጀመርያዎቹ ሣምንታት በሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የሚባል የተከላካይ ክፍል የገነቡት አሰልጣኝ አስራት አባተ ቡድናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥንካሬያቸው እየቀነሰ መጥቷል። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ማናስተናገዳቸውም ለዚ ማሳያ ነው። አሰልጣኙ ከተጠቀሰው ክፍተት በተጨማሪም የማጥቃት ክፍላቸው ጥራት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ሁለት ድል ፣ ሁለት ሽንፈትና አንድ የአቻ ውጤት አስመዝግበው ሰባት ነጥቦች የሰበሰቡት ወላይታ ድቻዎች በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ማራኪ አጨዋወት ያለው ቡድን ቢገነቡም በውጤት ረገድ ትልቅ የወጥነት ችግር ይስተዋልባቸዋል። በሊጉም በተከታታይ ማሸነፍ አልቻሉም። የጦና ንቦች በየጨዋታው ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች ቢፈጥሩም ወደ ግብነት የመቀየር ችግራቸው ግን የቡድኑ ትልቁ ችግር ነው ፤ በአምስት ሣምንታት አራት ግቦች ብቻ ማስቆጠራቸውም ለቡድኑ የማጥቃት ድክመት አንድ ምሳሌ ነው። ሆኖም አራት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ጠጣር የተከላካይ ክፍል ከአማካይ ክፍሉ ጋር በጋራ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ላለመጣል ዕድሎች መጠቀም ያልቻለው የማጥቃት ክፍል ላይ ውስን ለውጦች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የሁለቱንም ቡድኖች የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሁለቱን ክለቦች እስካሁን ካገናኟቸው 14 ጨዋታዎች ውስጥ አራቱ ነጥብ በመጋራት ሲጠናቀቁ 14 ግቦች ያስቆጠሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ሰባት እንዲሁም 11 ግቦች ያስቆጠሩት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ የአምናዎቹን ሁለት ድሎች ጨምሮ ሦስት ድሎችን አስመዝግበዋል።
ሀምበሪቾ ከ ፋሲል ከነማ
በሦስተኛውና አራተኛ ሣምንት ላይ ባስመዘገቧቸው የአቻ ውጤቶች ሁለት ነጥቦች የሰበሰቡት ሀምበሪቾዎች በአስራ አራተኛው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በታሪካቸው የመጀመርያው የፕሪምየር ሊግ ድል ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት ሀምበሪቾዎች በመጀመርያዎች ሦስት ጨዋታዎች በየጨዋታው ሁለት ሁለት በማስተናገድ ደካማ ክብረወሰን ቢያስመዘግቡም
የተከላካይ ክፍላቸው በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ትልቅ መሻሻል አሳይቷል ፤ በተጠቀሱት ጨዋታዎችም አንድ ግብ ብቻ ነው ያስተናገደው። ሆኖም ቡድኑ ግቦችን በማስቆጠሩ ረገድ ክፍተቶች ይታይበታል፤ በየጨዋታው በአማካይ 0.8 ግቦች ማስቆጠራቸውም አንዱ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ በነገው ጨዋታ በዋነኝነት ፍሬያማ መሆን ያልቻለው የአጥቂ ክፍላቸው ላይ ማስተካከያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ተጋጣሚያቸው በሦስት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን እንደመሆኑ ፈተናው ቀላል አይሆንም። ከዚ በተጨማሪ በአብዛኞቹ ጨዋታዎች በመጀመርያው አጋማሽ የሚታይባቸውን መቀዛቀዝም መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል።
በሊጉ ምንም ሽንፈት ያላስተናገዱት ዐፄዎቹ በሁለት ጨዋታዎች ድል ሲያደርጉ በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ የአቻ ውጤት አስመዝግበው ዘጠኝ ነጥቦች ሰብስበዋል። ፋሲሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ መሻሻሎች አሳይተዋል ፤ በተለይም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት የሚታይ ለውጥ አምጥቷል። ሆኖም ለአጥቂ ክፍሉ በብዛት እና በጥራት የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻለው የአማካይ ክፍል ለውጦች እንደሚያስፈልጉት የቡድኑ የግብ መጠን እንደ ማሳያ ማንሳት ይቻላል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በነገው ጨዋታ ያላቸውን የመከላከል ጥንካሬ ከማስቀጠል ባለፈ የማጥቃት አማራጮቻቸውን የማስፋት ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።
ዐፄዎቹ በነገው ጨዋታ በቅጣትም ሆነ በጉዳትም የሚያጡት ተጫዋች የለም። የሀምበሪቾን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም።