የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገም ሲቀጥል የዕለቱን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበናል።
ኢትዮጵያ መድን ከ መቻል
በሊጉ የእርስበርስ ታሪካቸው አንድ ጊዜ ብቻ ነጥብ የተጋሩት መድን እና መቻል የነገ ቀዳሚዎቹ ተጋጣሚዎች ናቸው።
አንድ ድል፣ ሁለት አቻና ሁለት ሽንፈት ያስተናገዱት መድኖች በአምስት ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። መድኖች በመጀመርያው ሳምንት ላይ ባህርዳር ከተማን ሦስት ለ ሁለት ካሸነፉ በኋላ ከድል ጋር ተራርቀዋል። በአራቱም ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦችም ሁለቱን ብቻ ነው ያሳኩት። ቡድኑ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ውጤት ከማጣቱም በተጨማሪ በከባድ የግብ ድርቅ ውስጥ ይገኛል። ለወትሮ በርካታ ግቦች ስያስቆጥር የምባውቀው ቡድን ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩም የቡድኑ ግብ የማስቆጠር ችግር ምን ያህል ትልቅ መሆኑ መረዳት ይቻላል።
ይህንን ተከትሎም አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በርካታ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ ቡድኑ በጉዳት ላይ የነበሩ ወሳኝ ተጫዋቾች መልሶ ያገኛል ተብሎ ስለሚታሰብም በአጨዋወት ይሁን በቋሚ አሰላለፍ ምርጫ ላይ ለውጦች ማድረጋቸው አይቀሬ ነው። መድኖች በነገው ጨዋታ በዋነኝነት በማጥቃት ክፍላቸው ላይ ያለውን ድክመት መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል። በአንፃሩ የተከላካይ ክፍላቸውን ጥንካሬ ማስቀጠልም ሌላው የቤት ስራቸው ነው። የተከላካይ ክፍሉ ምንም እንኳ በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ሦስት ግቦች ብያስተናግድም ከዛ በፊት በነበሩት ጨዋታዎች ግን ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይቷል፤ በተጠቀሱት አራት ጨዋታዎችም አራት ግቦች ብቻ ነበር ያስተናገደው።
ሦስት ድል፡ አንድ ሽንፈትና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት መቻሎች በአስር ነጥብ በ3ኛ ደረጃነት ተቀምጠዋል። መቻሎች በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች በተመሳሳይ የአንድ ለባዶ ድሎች አስመዝግበው ነጥባቸውና ደረጃቸው ከፍ ማድረግ ችለዋል። ቡድኑ ምንም እንኳ እንቅስቃሴው ወጥነት ቢጎድለውም በውጤት ረገድ ግን ጥሩ ጎኖች አሉት። በባህርዳር ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎችም ሰባት ነጥቦች ሰብስበዋል።
አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በመጀመርያዎቹ ሳምንታት የመከላከል ችግር የነበረበት ቡድን በጥሩ መንገድ አሻሽለውታል። ቡድኑ በመጀመርያዎቹ ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች አራት ግቦች ቢያስተናግዱም የኋላ ኋላ የሚታይ ለውጥ አሳይተዋል፤ ያስመዘገቡት የመከላከል ቁጥርም ይህንን ያስመለክታል ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሦስት ሳምንታት አንድ ግብ ብቻ ነው ያስተናገደው። ሆኖም የቡድኑ የማጥቃት ክፍል እንደሚፈለገው ግቦችን ማምራት አልቻለም፤ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎችም ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር አልቻሉም። በነገው ጨዋታም ይህንን ግብ የማስቆጠርና የግብ ዕድሎች የመፍጠር ችግር መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል።
በመቻል በኩል በብሔራዊ ቡድን ቆይታቸው ወቅት ጉዳት ያስተናገዱት ከነዓን ማርክነህ እና በረከት ደስታ ጨዋታው ያልፋቸዋል፤ መድኖችም የሀቢብ ከማልን ግልጋሎት አያገኙም።
ሁለቱ ክለቦች ነገ ለ14ኛ ጊዜ ይገናኛሉ። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ መድኖች 17 ግቦችን በማስቆጠር ሰባት ጨዋታዎችን በድል ሲወጡ 5 ጊዜ መርታት የቻሉት መቻሎች ደግሞ 16 ግቦች አሏቸው። ከ13 ግንኙነቶቻቸው መካከል አንድ ጊዜ ብቻ ነጥብ በመጋራት ተለያይተዋል።
ሻሸመኔ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ
ሁለት የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገቡ እና በአንድ ነጥብ ተበላልጠው በሊጉ ግርጌ የሚገኙ ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ ምሽት 12:00 ይጀምራል።
በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ ከተከታታይ አራት ሽንፈቶች በኋላ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር አቻ ተለያይተው የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ነጥብ ማስመዝገብ የቻሉት ሻሸመኔ ከተማዎች በነገው ጨዋታ ድል የሚቀናቸው ከሆነ ከሊጉ ግርጌ የሚላቀቁበት ዕድል ስለሚኖራቸው ለየት ባለ መንፈስ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይገመታል። ሻሸመኔዎች በመጀመርያዎቹ ሁለት ሳምንታት ከሌሎች የቡድኑ ክፍሎች በአንፃራዊነት የተሻለና ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ የተከላካይ ክፍል የነበራቸው ከዛ በኋላ ባደረጓቸው ተከታታይ ጨዋታዎች ግን ስድስት ግቦች አስተናግደው ጥንካሬያቸውን አጥተዋል።
በነገው ጨዋታም የተከላካይ ክፍሉ ወደ ቀድሞ ጠንካራነት የመመለሱ የአሰልጣኝ ትልቁ የቤት ስራ ይሆናል ተብሎ ይታመናል። ቡድኑ ከተጋጣሚው ከበደ ያለ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ባይታሰብም በመጨረሻው ጨዋታ ላይ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ግቡን ሳያስደፍር የወጣው ክፍል ግን ለውጦች እንደሚያስፈልጉት ከሲዳማ ቡናና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ተስተውሏል።
ሦስት ሽንፈትና ሁለት የአቻ ውጤቶች አስመዝግበው ሁለት ነጥቦች በመሰብሰብ ከነገው ተጋጣምያቸው በአንድ ነጥብ ከፍ ብለው የተቀመጡት ወልቂጤዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ወደ ሜዳ ይገባሉ። በበርካታ የሜዳ ውጭ ጉዳዮች ተፈትነው ጨዋታዎቻቸው ያከናወኑት ሰራተኞቹ በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ከባባድ መርሀ-ግብሮች አከናውነዋል። ሦስቱ የሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስቆጠሩትን ክለቦች በገጠሙባቸው ጨዋታዎችም ሽንፈት አስተናግደዋል። ወልቂጤዎች በውድድር ዓመቱ ሁለት ግቦች ብቻ ነው ያስቆጠሩት፤ እሱም ብቻ ሳይሆን በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። ይህ ችግርም የቡድኑ ትልቁ ክፍተት ነው። ቡድኑ ምንም እንኳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ጥረት የሚያደርግ ቢሆንም ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት አለው ብሎ ደፍሮ ለመናገር አይቻልም። ያስመዘገቧቸው ቁጥሮችም የዚህ ማሳያ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች የተቆጠረበት የተከላካይ ክፍልም ጥገናዎችን ይሻል።
በነገው ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማ እዮብ ገብረማርያምን በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም ፤ በወልቂጤ ከተማ በኩልም የዳንኤል ደምሱ፣ በቃሉ ገነነ፣ አሜ መሐመድ፣ ፋሪስ ሄኖክ ኢሳያስ የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።