​የአሰልጣኝ ጳውሎስ እና ወልቂጤ እህል ውሃ ያበቃ ይመስላል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ወልቂጤ ከተማ እና አሰልጣኙ ከዛሬው የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ሽንፈት በኋላ የተለያዩ ይመስላል።

በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ወልቂጤ ከተማን ባለፈው ዓመት ከወረደበት ሊጉ በማሟያ ጨዋታዎች ወደ ፕሪምየር ሊጉ በመመለስ ስራቸውን ከክለቡ ጋር የጀመሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በማሟያው የሀዋሳ ውድድር ላይ ቡድኑን ይዘው ባሳዩት አቋም መነሻነት በያዝነው ዓመት ወርሀ መስከረም ክለቡን በይፋ በአንድ ዓመት ውል ተረክበዋል። በዘንድሮው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን እሰከ ዛሬው የቅዱስ ጊዮርጊስ የ12ኛ ሳምንት ጨዋታ ድረስ ሰሞኑን ከገጠማቸው ህመም በማገገም እየመሩ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

ከሰዓታት በፊት በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ ሰራተኞቹ በፈረሰኞቹ 4-0 ሲረቱ ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ አሰልጣኝ ጳውሎስ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከክለቡ ጋር ሊለያዩ የሚችሉባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመው የነበረ ሲሆን ይሄንንም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አስቀድመው የተናገሩትን ቃል እንደሚፈፅሙ እና ከክለቡ ጋር ስለ መለያየታቸው የማይቀር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ከዛሬው ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ በሳለፍነው ሳምንት ክለቡ አዲስ አሰልጣኝ ሊቀጥር እንደሆነ ሲናፈስ በነበረው ዜና ስሜታቸው መነካቱን በመግለፅ ተከታዩን ስንብት ነክ ንግግር አድርገዋል፡፡

“ወልቂጤ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊጉ አስገብቻለሁ። አሁንም መጥፎ ደረጃ ላይ አይደለም ያለው ጥሩ ላይ ነው ያለው ቡድኑ። ይሄ የሚደረግ ነገር አልነበረም። ሳምንቱን ሙሉ ልምምድ እየሰራህ ይሄን ነገር እየሰማህ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚሰማህ መልሱን ለወልቂጤ ህዝብ እና ለወልቂጤ ደጋፊ ተወዋለው። ቤታቸውን መምርመር የራሳቸው ጉዳይ ነው፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ያው አዲስ አሰልጣኝ መጥቷል። ከዚህ በኋላ የስንብት ነገር ይኖራል ብዬ ገምታለሁ። ምክንያቱም ሞራሌ ጥሩ አደለውም። የሚሰራው ስራ ለእኔ አግባብ ስላልሆነ ይሄም ሆን ተብሎ የታቀደ ዕቅድ ስለሆነ እኔ ደስተኛ አይደለሁም። በዚህ አጋጣሚ የሚከበረውን ፣ የሚወደደውን የወልቂጤ ደጋፊ ፣ የወልቂጤን ህዝብ በጣም ከጎኔ ሆኖ ፕሪምየር ሊግ ስገባ ያጨበጨበልኝ በዚህም ላይ ጥሩ ውጤት እያመጣው በነበረበት ሰዓት ከጎኔ ለነበሩት ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።” በማለት አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሰረት 16 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወልቂጤ ከተማ ፊቱን ወደ አዲስ አሰልጣኝ የማዞሩ ነገር እርግጥ መሆኑ የማይቀር መስሏል፡፡