መቻሎች ለተከታታይ ሦስተኛ ጊዜ የ1-0 ውጤት በማስመዝገብ ኢትዮጵያ መድንን አሸንፈዋል።
መድኖች በጊዮርጊስ ሽንፈት ከደረሰበት ስብስብ ችኩውሜካ ጎድሰን በአሸብር ደረጄ ተክተው ሲገቡ፤ መቻሎች በበኩላቸው ሀምበሪቾ ላይ ድል ከተቀዳጀው ስብስብ ነስረዲን ኅልይሉ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ ግርማ ዲሳሳ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ ሽመልስ በቀለ እና በረከት ደስታ በአስቻለው ታመነ፣ ግሩም ሀጎስ፣ በኃይሉ ግርማ፣ አቤል ነጋሽ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ምንይሉ ወንድሙ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ብዙም ማራኪ ባልነበረው የመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎችና የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት ነበር። ሁለት መልክ በነበረው አጋማሽ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች መቻል የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ለመያዝ ሲሞክሩ ብልጫቸው ግን መቀጠል አልቻለም። የግብ ዕድል በመፍጠር ረገድ በአንፃራዊነት የተሻሉ የነበሩት መቻሎት ወደ ሙከራነት ያልተቀየሩ የግብ ዕድሎች ሲፈጥሩ ከቆዩ በኋላ በአስራ አራተኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። አቤል ነጋሽ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ያደረገው።
መቻሎች ከግቡ በኋላም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ግብ አስቆጣሪው አቤል ነጋሽ፤ ሳሙኤል ሳሊሶ በጥሩ ሁኔታ ያሻማለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጓል። በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች የተነቃቁት መድኖች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መያዝ ቢችሉም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ቀርበው የግብ ሙከራዎች ማድረግ አልቻሉም።
ከመጀመርያው አጋማሽ የተለየ መልክ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ መድኖች ተሽለው የታዩበት ነበር። በአንፃሩ መቻሎች በእጃቸው የገባውን ውጤት አስጠብቀው ለመውጣት አፈግፍገው ለመጫወት መርጠዋል። በተለይም ግሩም ሀጎስ በ77ኛ ደቂላ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከወጣ በኋላ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ ወደ መከላከሉ አዘንብሏል። በአጋማሹ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉት መድኖች በቼኩመካ ጎድሰን አማካኝነት ሦስት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል፤ ሁለቱ ከቆሙ ኳሶች የተደረጉ ሙከራዎች ሲሆኑ አንዱ በግንባር የተደረገ ሙከራ ነው። ተጫዋቹ በተለይም ግሩም በብሩክ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጥውን ቅጣት ምት ተጠቅሞ መቶት ግብጠባቂው ያወጣው ኳስ ለግብ የቀረበ ነበር። ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራም ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።
ውጤቱን ተከትሎ መቻሎች ተከታታይ ሦስተኛ የ1-0 ድል ስያስመዘግቡ መድኖች ለተከታታይ አራተኛ ሳምንት ኳስና መረብ ሳያገናኙ ወጥተዋል።