ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በጨዋታ ሳምንቱ በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች መነሻነት የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋች ነክ ጉዳዮች የሁለተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 መሳይ አያኖ በድንቅ ብቃት ተመልሷል

በዘንድሮ የውድድር ዘመን ሁለት ጨዋታዎች ላይ ብቻ (ከፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ) የሀዲያን ግብ እንዲጠብቅ ሀላፊነት ተሰጥቶት የነበረው መሳይ አያኖ ቡድኑ በ12ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ሰበታን ሲረታ የመሰለፍ ዕድል አግኝቶ ጥሩ ብቃቱን አሳይቷል።

የአሠልጣኝ ሙሉጌታ እና የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ቅዱስ ቀዳሚ ተመራጭ የሆነው ቶጎዋዊው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳ በ11ኛ ሳምንት ጨዋታ ቡድኑ በጅማ ሲረታ አራት ግቦችን ማስተናገዱ ብቻ ሳይሆን በግል ሲሰራቸው የነበሩ ስህተቶች በዚህኛው ሳምንት ተጠባባቂ ወንበር ላይ ጊዜ እንዲያሳልፍ ያደረገ ይመስላል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከሲዳማ ቡና ከቤራዎቹ ቤት የደረሰው መሳይ ደግሞ ያገኘውን አጋጣሚ በቀጣይም ላለማጣት ሲጥር አስተውለናል።

ከወትሮ በተለየ ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩትን ሰበታዎች በጥሩ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የሰዓት አጠባበቅ እና ቅልጥፍና ሲያድን የነበረበት መንገድም ለዘጠኝ ጨዋታዎች በተጠባባቂ ወንበር ላይ የከረመ አይመስልም። በተለይ ቦታው ከፍተኛ የትኩረት ደረጃን የሚፈልግ መሆኑ እና ይህ ትኩረት ደግሞ በጨዋታ ሪትም የሚመጣ አያይዞም የራስ መተማመንን የሚገነባ መሆኑ ሲታወስ ተጫዋቹ ከጨዋታ ርቆ ይህንን ብቃት ማሳየቱ የሚያስደንቀወወ ነው። በቀጣይ ጨዋታስ ተጫዋቹ በግብ ብረቶቹ መሐከል ይሆናል ወይስ የሚለውን ደግሞ አብረን የምናይ ይሆናል።

👉 የአብዱልከሪም መሐመድ ነገር

በክረምቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቆ ወደ ፋሲል ከነማ ያመራው የቀኝ መስመር ተከላካዮ በአፄዎቹ ቤት ቀሪ የ19 ወር ኮንትራት ቢቀረውም በጋራ ስምምነት ውሉን አቋርጦ ከክለቡ መለያየቱ እርግጥ ሆኗል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በተለይ በ2008 ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ድራጋን ፓፖዲች ይመራ በነበረው የኢትዮጵያ ቡና ስብስብ ውስጥ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ድንቅ ጊዜያትን አሳልፏል። በተለይ በወቅቱ የሚያጠቁ የመስመር ተከላካዮች እሳቤ በሊጉ እንደ አዲስ መታየት በጀመረበት በዛ ወቅት አብዱልከሪም በኢትዮጵያ ቡና በወቅቱ የነበረውን የመስመር ተከላካዮች እሳቤን በቀየረ መልኩ አስደናቂ የማጥቃት አቅሙን መመልከት ችለን ነበር።

ጥሩ ጊዜያትን በኢትዮጵያ ቡና በማሳለፍ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያመራው አብዱልከሪም በቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው አመት የተሻለ ነገር ማሳየት ቢችልም በቀሩት ሦስት ዓመታት ግን ቀስ በቀስ ግን ተፅዕኖው እየደበዘዘ መጥቷል። የአብዱልከሪም ተፅዕኖ ስለመቀነሱ ብዙዎች የቡድኑ አጨዋወት በተለይም ከተለጠጠ አቋቋም የሚነሱ የመስመር ተጫዋቾችን ቡድኑ እንደመያዙ ለአብዱልከሪም ሁኔታዎችን አስቸጋሪ አድርገውበታል የሚሉ እና ሌሎች ምክንያቶች ቢቀርቡም ተጫዋቾች ግን በቀደመው ልክ መሆን ሳይችል ቀርቷል።

በፈረሰኞቹ ቤት ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ፋሲል ከተማ ያቀናው የ2010 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች በአፄዎቹ ቤትም ነገሮች በፈለገው መጠን አልሄዱለትም ፤ በአንድ ጨዋታ ብቻ በመጀመሪያ ተሰላፊነት በሊጉ መጀመር የቻለው አብዱልከሪም በሁኔታዎች ደስተኛ ባለመሆኑ የልቀቁኝ ደብዳቤ ማስገባቱን ተከትሎ ከክለቡ በያዝነው ሳምንት መለያየቱ ተሰምቷል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ተጫዋቾች ላይ በቀዳሚነት ከሚነሱ ድክመቶች አንዱ በሆነው አካላዊ ዝግጁነት ረገድ ራሱን በመጠበቅ ሆነ ሰውነቱን በአግባቡ በመከታተል ረገድ ወደር የማይገኝለት ቢሆንም በሌሎች እግርኳሱ በሚፈልጋቸው መዘርዝሮች ግን ሜዳ ገብቶ በተመለከትንባቸው የጨዋታ ደቂቃ በቀደመው ልክ ይገኛል ብሎ ለመናገር በሚያስደፍር ሁኔታ ላይ ይገኛል ለማለት ያስቸግራል።

በመሆኑም በቀጣይ ተጫዋቾች በሊጉ በሚኖረው ቆይታ ከአካል ብቃት ባለፈ ሁለንተናዊ ብቃቱ ላይ በትኩረት ሰርቶ የቀደመ ብቃቱን ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 የዊልያም ሰለሞን የደስታ አገላለጽ

በጨዋታ ሳምንቱ ኢትዮጵያ ቡና አዲስአበባ ከተማን በረታበት ጨዋታ የጨዋታውን የመክፈቻ ግብ ማስቆጠር የቻለው ዊልያም ሰለሞን ግቧን ካስቆጠረ በኃላ ያሳየው የደስታ አገላለጽ የተለየ ነበር።

ከቀናት በፊት ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ አምስት ቀናትን ከፈጀ ሂደት በኃላ የተገኘው የአምስት አመቱ ሞሮካዊው ብላቴና ራያን ኦራም በህይወት ከጉድጓድ መውጣት ቢችልም ከሰዓታት በኃላ ግን የተሰማው ህልፈቱ መላውን ዓለም ያስደነገጠ ዜና እንደነበር ይታወሳል።

ታድያ የኢትዮጵያ ቡናው ዊልያም ሰለሞንም ግብ ካስቆጠረ በኃላ ከመለያው ስር “I LOVE YOU RAYAN R.I.P” የሚል ፅሁፍ የሰፈበትን ቲሸርት አውልቆ በማሳየት በቅርብ ህይወቱ ያለፈውን ታዳጊ አስቦታል። ይህ ክስተትም በማኅበራዊ ሚድያው ላይ የጨዋታ ሳምንቱ እጅግ መነጋገርያ ጉዳይ ሆኗል።

👉 ፉአድ ፈረጃ እየተመለሰ ይሆን?

ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፈጣን መሻሻሎችን እያሳዩ ከሚገኙ ወጣቶች ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ፉአድ ፈረጃ ዘንድሮ ግን እስካሁን የቀደመ ማንነቱን በባህር ዳር ከተማ ለማሳየት እየተቸገረ ይገኛል።

ከአዳማ ከተማ የእድሜ እርከን ቡድኖች የተገኘው ተጫዋቹ በዋናው ቡድንም በተለይ በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን ድንቅ የሚባል ጊዜን ማሳለፍ ችሏል የተጠናቀቀውን የውድድሮ ዘመን በሰበታ ያሳለፈው ተጫዋቹ በክረምቱ የዝውውር መስኮት አሰልጣኝ አብርሃምን ተከትሎ ባህር ዳር ቢደርስም በተለያዩ ምክንያቶች ግን እስካሁን በባህር ዳር ቤት በተጠበቀው ልክ እየደመቀ አይገኝም።

12ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የሊጉ ውድድር በድምሩ በአምስት ጨዋታዎች ብቻ በመጀመሪያ ተመራጭነት የተሰለፈው ፉአድ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በተከታታይ ከተሰለፈባቸው ጨዋታዎች በኃላ ቀጣይ በመጀመሪያ ተሰላፊነት እድልን ለማግኘት አምስት ጨዋታዎችን መጠበቅ የነበረበት ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከሀዋሳ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ በመጀመሪያ ተመራጭነት የጀመረው ከሁለት ጨዋታዎች በፊት ነበር።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ሀዋሳ ከተማን ሲረታ አስደናቂ የሆነ ግብን በቄንጥ ያስቆጠረው ተጫዋቹ ከግቧ በኃላ በእምባ ታጅቦ ደስታውን ሲገልፅ ተመልክተናል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ ከግቡ በኃላ ስላነባበት ምክንያት ሲያስረዳ በተደጋጋሚ ጉዳት ምክንያት የአካላዊ ዝግጁነቴን ለመመለስ እየሰራ መሆኑን እና ከግብ ርቆ በመቆየቱ መነሻነት ስሜታዊ መሆኑን ተናግሯል።

👉 ሁሉን ነገር እንዲያደርግ የሚጠበቀው ቢኒያም በላይ

ከጥቂት ዓመታት የባህር ማዶ ቆይታ በኃላ ዓምና ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተመለሰው ቢኒያም በላይ ዘንድሮ በመከላከያ ቤት እየተጫወተ ይገኛል። በአዲሱ ቡድኑ ግን የተሰጠው ሀላፊነት እጅግ ከባድ እንደሆነ እየተመለከትን እንገኛለን።

የመስመር አማካዩ ቢኒያም በላይ በመከላከያ የማጥቃት ሆነ የመከላከል ጨዋታ ውስጥ ቁልፉ ሰው (Linchpin) ስለመሆኑ የቡድኑ የጨዋታ መንገድንን መመልከት በቂ ነው። ከዚህ መነሻነት መከላከያ ውጤታማ እንዲሆን ቢኒያም በላይ ጥሩ ቀን ማሳለፍ የግድ የሚለው ሲሆን ቢኒያም ከተቸገረ ቡድኑም የመቸገሩን ነገር እየተመለከትን እንገኛለን።

እንደ ቡድን 7 ግቦችን በማስቆጠር ከጅማ አባጅፋር ጋር የሊጉ ደካማውን ማጥቃት ባለቤት የሆነው ቡድኑ ቢኒያም በላይ በግሉ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥርለት በጨዋታዎች እሱ የተሰለፈበት መስመር የተሻለ የማጥቃት ስጋት ተጋጣሚዎች ላይ ሲደቅን እየተመለከትን እንገኛለን።

በባለፈው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን ሲረታ ቡድኑ እንደ ቡድን ከወትሮው የተሻለ የማጥቃት ፍላጎትን ያሳየ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ወደ ቀደመው ቢኒያም በላይ ተኮር ጨዋታ ተመልሶ ተመልክተነዋል።

ኳስ መስርቶ የመጫወት ፍላጎት የነበረው ቡድኑ የምስረታ ሂደቱ ግን እጅግ ቀርፈፍ ያለ ነበር። በተመሳሳይ በመስመሮች በኩል የማጥቃት ፍላጎት የነበረው ቡድኑ እንደወትሮው ሁሉ ቢኒያም በላይ በተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል አደጋ ለመፍጠር ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ተጫዋቹን ለማቆም ወላይታ ድቻዎች ሁለት (በረከት ወ/ዮሀንስ እና ያሬድ ዳዊት) በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ በሦስተኛ ተጫዋች ወደ እርሱ እያስጠጉ ለመከላከል ጥረት በማድረጋቸው ቢኒያም በላይ ይህን ጥምረት ለብቻው ሰብሮ ለመውጣት በግሉ ከፍተኛ ጥረቶችን ቢያደርግም ከተጫዋቹ በጣም ርቀው ከነበሩት የአጥቂ እና የአማካይ ተጫዋቾች በቂ ድጋፍ ማግኘት አለመቻሉን ተከትሎ ጥረቱ መና ቀርቷል።

በተመሳሳይ ቡድኑ ከፊት ጫና አሳድሮ ለመጫወት በሚጥርባቸው ቅፅበቶች እንዲሁ ቢኒያም በላይ የዚህ ሂደት አስጀማሪ እንደመሆኑ በግሉ ብዙ ርቀቶችን እንዲያካልልም ሲገደድም አስተውለናል። በዚህ ሂደት ተጫዋቹ አብዛኞቹ እንቅስቃሴዎቹ ከቡድን አጋሮቹ ድጋፍ አለማግኘቱን ተከትሎ ሲባክን ተመልከተናል።

በመሆኑም ቡድን እንደ ወላይታ ድቻ አይነት የተጋጣሚን ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋቾች ከጨዋታ እንቅስቃሴ ለማጥፋት ስልትን ይዘው የሚመጡ ተጋጣሚዎች ሲገጥሙት ቡድኑ ምና ያህል እንደሚቸገር የወላይታ ድቻው ጨዋታ አይነተኛ ማሳያ ነው። በመሆኑ ቡድኑ በቀጣይ እንደ ቡድን በመንቀሳቀስ እና ሌሎች መንገዶችን በመፍጠር የማጥቃት ሆነ የመከላከል ሂደታቸውን የተወሰኑ ለውጦች ማድረግ ካልቻሉ በተለይ ቢኒያም በላይ መስጠት የሚችለው ነገር አማጦ ከመጠቀም አንፃር ተጫዋቾች እንዳያባክኑት ያሰጋል።

👉 አማኑኤል ገብረሚካኤል ከ357 ቀናት በኃላ አስቆጥሯል

አንድ ዓመት ለተጠጋ ጊዜ ለክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ማስቆጠር ተስኖት የቆየው አማኑኤል ገብረሚካኤል በስተመጨረሻም ከፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ የግብ ርሃቡን አስታግሷል።

በ2009 ክረምት ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ለቆ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ካመራ በኋላ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር እንዲያድግ በማስቻል በዓመቱ የከፍተኛ ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሆነ ማጠናቀቅ ሲችል በ2011 ደግሞ መቐለ ሊጉን ሲያሸንፍ በ18 ግቦች በግሉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቁ አይዘነጋም።

በመቐለ መለያ ከ50 የላቁ ግቦችን ማስቆጠር የቻለው አማኑኤል የመቐለ አድራጊ ፈጣሪ ነበር ማለት ይቻላል፤ ታድያ እግርኳሳዊ ባልሆኑ ምክንያቶች መቐለን ለቆ በመጨረሻ ሰዓት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያመራው አማኑኤል ገብረሚካኤል በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ግን በሚፈለገው ልክ አገልግሎት ለመስጠት ተቸግሯል።

የ2011 የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በ2013 የውድድር ዘመን ግን የማጥቃት ቁጥሮቹ በአስደንጋጭ መልኩ ነበር የወረዱት። የR&D Group ቁጥሮች እንደሚያሳዩት ከሆነ አማኑኤል የግብ እድሎችን ወደ ግብነት የመቀየር ንፃሬው 6% የነበረ ሲሆን በጨዋታም 0.7 ብቻ ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎችን እንዲሁም በጨዋታ 0.1 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን የማቀበል ቁጥሮችን አስመዝግቦ የውድድር ዘመኑን አጠናቋል።

በዘንድሮውም የውድድር ዘመን ቀዝቃዛ ጊዜያትን እያሳለፈ የሚገኘው አማኑኤል በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ያስቆጠረ ሲሆን በፈረሰኞቹ መለያ የመጨረሻውን ግብ ያስቆጠረው አምና በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ አዳማ ከተማን ሲረታ እንደነበር አይዘነጋም።

በመቐለ 70 እንደርታ የቡድኑ አንፀባራቂ ኮከብ የነበረው አማኑኤል ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲመጣ ግን ከብዙ ክዋክብቶች አንዱ እንዲሆን መገደዱ በመቐለ በለመደው ደረጃ እንቅስቃሴዎች በመሉ እሱን ያማከለ አለመሆናቸውን ተከትሎ ከዚህ አዕምሮአዊ ሁኔታ ጋር እስካሁን ራሱን አስተካክሏል ብሎ ለመናገር በጣም ያስቸግራል በመሆኑም የመጀመሪያ ግቡን በዚህ የጨዋታ ሳምንት ማግኘቱ በመልካምነት የሚነሳ ሲሆን በቀጣይ የዚህች ግብ ተፅዕኖ ምን ድረስ ይወስደዋል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 የይገዙ እና ኦሮ-አጎሮ ትንቅንቅ

የመጀመሪያ ዙር ውድድር ሊጠናቀቅ የሦስት ጨዋታ እድሜ በቀረው በዚህ ጊዜ የሲዳማ ቡና አጥቂ ይገዙ ቦጋለ እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በእኩል 8 ግብ እየመሩ ይገኛል። ገና ከወዲሁ ከሌሎች ተጫዋቾች ተነጥለው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክርን እያደመቁ የሚገኙት ሁለቱ ተጫዋቾች በየራሳቸው አውድ ብቃታቸውን ለማሳየት እና ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተንደረደሩ ይገኛል።

በሲዳማ ቡና ቤት ከታችኛው ቡድን ቢያድግም በተለያዩ አጥቂዎች ጥላ ስር የቆየው ቡድኑ ከአምና የውድድር ዘመን አንስቶ የቡድኑን የፊት መስመር የመመምራት ሀላፊነት ቢጣልበትም ተደጋጋሚ ጎዳቶች በሚፈለገው ልክ ቡድኑን እንዳያገለግል እንቅፋት ሲሆንበት የተመለከትን ሲሆን ዘንድሮም ቡድኑ በዝውውር መስኮቱ ሁነኛ አጥቂ ሲያፈላልግ ቢቆይም ማግኘት ባለመቻሉ እንደ ሁለተኛ የፊት አጥቂ አማራጭ ይቆጠር የነበረው ይገዙ የሲዳማን የፊት መስመር የመምራት ሀላፊነት ተጥሎበታል።

ገና ከጅምሩ ከደጋፊዎች ተቃውሞ ሲያስተናግድ የነበረው ይገዙ አሁን ላይ ከቡድኑ አይነኬ ተጫዋቾች በቀዳሚው ተርታ ለመቀመጥ ያበቃውን አስደናቂ ጉዞ እያደረገ ይገኛል። ይህን ሂደትን በማስቀጠልም ከአዲስ ግደይ በኃላ የቡድኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋች የመሆን እና የብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ የመካተት ውጥን ይዞ ውድድሩን እያደረገ ይገኛል።

በተመሳሳይ የቶጎ ዜግነት ያለው ግዙፉ አጥቂ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቅዱስ ጊዮርጊስ ጌታነህ ከበደ እና ሳላሀዲን ሰዒድን ማጣቱን ተከትሎ ይህ ቦታ በምን መልኩ ሊሸፈን ይችላል የሚለው ጥያቄ አጓጊ የነበረ ሲሆን ተጫዋቹ በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ያሳየውን ደካማ እንቅስቃሴ ተከትሎ ምናልባት ቡድኑ ካሉት በርካታ የመስመር አጥቂ/አማካዮች/ አንዱን በሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ሊጠቀም ይችላል የሚለው ጉዳይም እንዲሁ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነበር።

በሊጉ ደካማ አጀማመር ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተወሰነ መልኩ የቀደመውን ቀጥተኝነቱን ጨዋታው ላይ አክሎ መቅረቡን ተከትሎ ይህ ሂደት የተመቸው የሚመስለው ኦሮ-አጎሮ በተከታታይ ግቦችን እያስቆጠረ ይገኛል።

በ2010 የውድድር ዘመን ኦኪኪ አፎላቢ በ23 ግቦች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ካጠናቀቀ በኋላ በነበሩት ሁለት የውድድር ዘመናት በጥቅሉ ተፅዕኗቸው እየቀነሱ የሚገኙት የውጭ ሀገር ተጫዋቾች በተለይም አጥቂዎችን አሁንም ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆናቸውን የማሳየት ሀላፊነትም እዚሁ ተጫዋቾች ላይ ተጥሏል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ኦኪኪ አፎላቢ በግማሽ የውድድር ዘመን የሲዳማ ቡና ቆይታው 7 ግቦችን እንዲሁም በ2011 የውድድር ዘመን የጅማ አባጅፋሩ ማማዱ ሲዲቢ 12 ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛውን ግብ ያስቆጠሩ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋች ሲሆኑ በሁለቱም ዓመታት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆነው ካጠናቀቁ ተጫዋቾች ጋር የነበራቸው የጎል ልዩነት እና በፉክክሩ ውስጥ የነበሩ የውጭ ተጫዋቾች ቁጥር መቀነሱን ከተትሎ ብዙዎች ተፅዕኗቸው ስለመቀነሱ ሀሳቦችን እያነሱ ይገኛል።

በቀጣይ ሁለቱ ተጫዋቾች በዚህ የግብ አስቆጣሪነት ይዘልቁ ይሆን ወይንስ ሌሎች ተጫዋቾች ፉክክሩን ያደምቁት ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 ምርጥ የነበረው ዳዊት ተፈራ

ሲዳማ ቡና ጅማ አባጅፋርን በረታበት ጨዋታ ለሲዳማ ቡናዎች የዳዊት ተፈራ ተፅዕኖ የጎላ ነበር። ይገዙ ቦጋለ ላስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ እጅግ አስደናቂ የነበረች እና በርከት ያሉ የጅማ አባጅፋር ተጫዋቾችን መሀል ለመሀል ሸንሽና ያለፈችን አስደናቂ ኳስ ማቀበል የቻለው ተጫዋቹ በሁለተኛዋ አጋማሽ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ማሳደግ ችሏል።

በተወሰነ መልኩ በመከላከሉ ወቅት ካለው ደካማ አበርክቶ አንፃር ወደ ተጠባባቂ ወንበር ለመውረድ ተገዶ የነበረው ዳዊት ቡድኑ በራሱ ቅኝት ጨዋታዎችን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሲፈልግ በማጥቃቱ ረገድ ምን ማበርከት እንደሚችል የጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ አይነተኛ ማሳያ ሆኖ አልፏል።

ጫና ውስጥ የነበረው ቡድኑ ከሰሞኑ እያስመዘገባቸው በሚገኙ አዎንታዊ ውጤቶች መነሻነት በሰንጠረዡ ደረጃው እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ በቀጣይ ዳዊት ተፈራ በማጥቃቱ በተለይም የመጨረሻ ኳሶችን በማቀበል ሆነ ግቦችን በማስቆጠር አቅሙን ሊያስበት የሚችለውን እድል በተደጋጋሚ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 የውጭ ተጫዋቾች የስነምግባር ጉዳይ

የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች በከፍተኛ ወጪ ወደ ሀገራችን ሊግ እንደመምጣታቸው እያንዳንዱ ድርጊታቸው በትኩረት የመታየቱ ጉዳይ የሚጠበቅ ነው። ታድያ የዚሁ ዕይታ አንድ አካል በሆነው የስነምግባር መመዘኛዎች ግን አንዳንድ ተጫዋቾች ላይ እየተመለከትነው የምንገኘው ነገር የሚያስተዛዝብ ነው።

ከዚህ ቀደም የወልቂጤ ከተማው ግብጠባቂ ሲልቪያን ግቦሆ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበራቸው ጨዋታ በጨዋታው የመጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ከዕለቱ ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ጋር የፈጠረው አተካራ የሚታወስ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ኬኒያዊው የአርባምንጭ ከተማ ተከላካይ በርናርድ ኦቼንግ ጨዋታውን የመሩትን ዳኛ በአልተገባ የእጅ ምልክት የተሳደበበት መንገድ በትልቅ ደረጃ ከሚጫወት ተጫዋች የሚጠበቅ አልነበረም።

እርግጥ ይህ ድርጊት ሁሉንም የሚወክል ባይሆንም ይህን ሊወገዝ የሚገባ ያልተገባ ድርጊት ግን በከፍተኛው የእግርኳስ ደረጃ ከሚጫወቱ አለፍ ሲልም ከሀገራቸው ወጥተው ወደ ሌሎች ሀገራት ተጉዘው ከሚጫወቱ ዓለምዓቀፍ ተጫዋቾች የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር መሆኑ አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል።

የሜዳ ላይ በሚገባው ልክ ቡድናቸውን ለማገልገል የተቸገሩ ተጫዋቾች በመሰል ድርጊቶች ተሳትፈው ሲገኙ ደግሞ ይበልጥ ነገሩን አነጋጋሪ የሚያደርገው ሲሆን መሰል ድርጊቶች ዜግነት ሳይለያቸው ሊወገዙ እና ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ ይገባል።

👉 ቅዱስ ጊዮርጊስን እየመራ የሚገኘው ፍሪምፖንግ ማንሱ

ባለፉት ሁለት ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ ስፍራ ላይ በመሀል ሆነ በመስመር ተከላካይነት እየተጫወተ የሚገኘው ጠንካራው ጋናዊ ኤድዊን ፍሪምፖንግ ማንሱ አሁን ደግሞ በአምበልነት እየመራ ቡድኑን በከፍታ እያስጓዘ ይገኛል።

እጅግ ሲበዛ ጠንቃቃ የሆነው ተከላካዩ የአየር ላይ ኳሶችን በማሸነፍ ሆነ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች የተጋጣሚ ተጫዋቾች ላይ የበላይነት በመውሰድ ወደር የማይገኝለት እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት እንቅስቃሴ በረጃጅም ኳሶችም በማስጀመር በጣሙን የተዋጣለት ነው። ከምኞት ደበበ ጋር በመሆን አስፈሪ የመከላከል ጥምረት የፈጠሩ ሲሆን ከዚህ ባለፈም የቡድኑ ተቀዳሚ አምበል የሆኑት ናትናኤል ዘለቀ፣ ሳልሃዲን በርጊቾ እና ሀይደር ሸረፋ አለመኖራቸውን ተከትሎ ቡድኑን ባለፉት ጨዋታዎች በአምበልነት እየመራ ይገኛል።

የውጭ ሀገር ዜግነት ባላቸው ተጫዋቾች ባልተለመደ መልኩ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የሚገኘው ፍሪምፖንግ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉ አናት መቀመጥ በስተጀርባ ካሉ ቁልፍ ተጫዋቾች ተርታ የሚያስመድበው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ሆነ የመሀሪነት ክህሎት እያሳየ ይገኛል።