ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በመጨረሻው የትኩረታችን ክፍል በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸውን ሌሎች ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች ተዳሰውበታል።

👉 መፍትሄ የታጣለት የትጥቅ አቅራቢዎች ስብጥር

የሊጉ ክለቦች ይፋዊ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነቶችን በተለይ ከሀገር በቀሉ የትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ “ጎፈሬ” ጋር በስፋት እየፈፀሙ ቢገኝም አሁን ድረስ ግን በክለቦች ዘንድ አንዳንድ ሰብጠርጠር ያለ የትጥቅ አጠቃቀሞችን እየተመለከትን እንገኛለን።

ለአበዛኛዎቹ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ትጥቅ እያቀረበ የሚገኘው “ጎፈሬ” ከጨዋታ ዕለት መለያዎች አንስቶ የጉዞ እና የመመገቢያ ቲቨርቶችን እንዲሁም የቡድን ጃኬት እና ሱሪዎችን እያመረተ ለክለቦች እያቀረበ ይገኛል ፤ በቅርቡም ተቋሙ የተጫዋቾች የመጫወቻ ካልሲ (ካሶተኒ) ለማምረት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ስለማጠናቀቁ ገልጿል።

እርግጥ ከክለቦች እና በተቋሙ መካከል ስለተፈፀሙ ዝርዝር የውል ስምምነቶችን መመርመር ቢያስፈልግም አንዳንድ ክለቦች ከጨዋታ በፊት በሚኖራቸው ልምምድ እና በጉዞ ወቅት ሆነ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቶቻቸው እና ተጠባባቂ ተጫዋቾች የሌላ ተቀናቃኝ አቅራቢ ኩባንያ ምርቶችን ሲጠቀሙ እየተመለከትን የመገኘታችን ግን የሚያነጋግር ነው።

ለአብነትም በዚህ የጨዋታ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማዎች በሌላ ተቋም የልምምድ ትጥቅ ልምምዳቸውን ሲሰሩ የተመለከትን ሲሆን በተመሳሳይ የሀዋሳ ከተማ እንዲሁም የሲዳማ ቡና አሰልጣኞች የሌላ ተቋም ምርቶችን በጨዋታ ወቅት ለብሰው ለመታዘብ ችለናል።

እንደ አብነት ከጎፈሬ ጋር ያለውን አነሳን እንጂ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጭ ያሉ የሊጉ ክለቦች የተለያዩ የትጥቅ አቅራቢዎችን የማሰባጠራቸው ጉዳይ የተለመደ ሂደት ነው። በመሆኑም በቀጣይ እንዲህ ዓይነት መዘበራረቆች እንዳይፈጠሩ ስምምነቶች ሲፈፀሙ መሰል ጉዳዮችን በዝርዝር ውል ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ ጥረቶች ሊደረጉ ይገባል። አለፍ ሲልም የሌላ ኩባንያ ምርቶችን በመጠቀም ጥሰቶች ሲፈጠሩም በህግ አግባብ ወደሚታረሙበት አሰራር መራመድ የግድ የሚለን ጊዜ ላይ እንገኛለን።

👉 በእግርኳስ ድርድር የማያውቁት ከንቲባ

ስለኢትዮጵያ እግርኳስ አስተዳደር በተለይ አሁን ላይ ቁጥራቸው እየተበራከቱ የሚገኙት የከተማ አስተዳደር ክለቦች ስናስብ በቅድሚያ ወደ አዕምሯችንን የሚመጡት ጉዳዮች በፖለቲካዊ አሰላለፋቸው መነሻነት የክለብ አመራርነት መንበርን የሚቆናጠጡ ለእግርኳሱ በቂ ፍቅር እና ውግንና የሌላቸው ሹመኞች መሆናቸው ጥርጥር የለውም ፤ ነገርግን አሁን የምናወራላቸው ግለሰብ ግን ከዚህ የተለዩ ናቸው።

ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ ከተማ በመረብ ኳስ ተጫዋችነታቸው የሚታወቁት እና ከዚያ በኋላ በስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ሰርተው ያሳለፉት አቶ ከድር ጆሃር ከድሬዳዋ ከተማ ስፖርት ክለብ ጋር ያላቸው ቁርኝት ይበልጥ እየተናከረ የመጣው ከዚሁ ጊዜ አንስቶ ነበር።

የከተማ አስተዳደሩ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር መሆናቸውን ተከትሎ በድሬዳዋ ከተማ ስፖርት ክለብ የቦርድ አባል በመሆን የጀመረው ተሳትፏቸው በኋላ ላይ የቦርድ ሰብሳቢ እስከመሆን ድረስ በቅተዋል። በአሁኑ ወቅት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ከድር ጆሀር በከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ መንግስታዊ ኃላፊነት ላይ ቢገኙም ከሚወዱት እግርኳስ እና የኔ ከሚሉት ክለባቸው ግን ፈፅሞ ሊነጣጥላቸው አልቻለም።

በድሬዳዋ ከተማ የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ ጥሩ ስምነት መገንባት የቻሉት አቶ ከድር ክለባቸውን በሜዳ ተገኝተው ከማበረታት አንስተው አሁን አቅማቸው በፈቀደ መልኩ ለድሬዳዋ ከተማ ስፖርቱ ክለብ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ቀጥለዋል።

ከሰሞኑ አድናቆቶች እየተቸሩት የሚገኘው የድሬዳዋ ዓለምዓቀፍ ስታዲየምን የመጫወቻ ሜዳ ሆነ ሌሎች የስታዲየሙ ማሻሻያ ስራዎች ላይ የነበራቸው ተሳትፎ የላቀ ነበር። እያንዳንዱን የግንባታ ሂደቶች በአካል ተገኝተው የስራ ሂደቶችን በመከታተልም ሆነ አስፈላጊውን በጀት ከአስተዳደራቸው እንዲለቀቅ በማድረግ ጉልህ ሚናን ተወጥተዋል።

በክለባቸው መለያ ደምቀው በስታዲየም የሚታደሙት ከንቲባው የስራ ጉዳይ ካልገደባቸው በስተቀር በድሬዳዋ እየተደረገ በሚገኘው ውድድር የሌሎች ክለቦች ጨዋታዎችን ለመታደም እንዲሁ በስታዲየም ሲገኙ እየተመለከትን እንገኛለን።

እግርኳሳችን እግርኳስን በሚወዱ እና የእግርኳስ አስተዳደርን ጠንቅቀው የተረዱ አመራሮችን በሚሻበት በዚህ ወቅት እንደ አቶ ከድር ጆሃር ያሉ ለእግርኳስ የወገኑ አመራሮችን መመልከት ተስፋ የሚሰጥ ሲሆን ሌሎች መሰል አመራሮች ወደ ፊት ብቅ እንዲሉም ምኞታችን ነው።

👉የደጋፊዎች ይቅርታ

በተጠናቀቀው የጨዋታ ሳምንት ቅጣት ላይ የሰነበቱት የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ሲመለሱ የክለባቸውን ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት እንዲሁም የሊግ አክሲዮን ማህበሩን ይቅርታ መጠየቃቸውን ተመልክተን ነበር። አሁን ደግሞ ተረኞቹ የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች ሆነዋል።

በ11ኛ የጨዋታ ሳምንት ቡድናቸው በሀዋሳ ከተማ በጭማሪ ደቂቃ በተቆጠረችባቸው ግብ 3-2 በተሸነፉበት ጨዋታ ጨዋታውን በመሩት አልቢትር ላይ ባልተገቡ ቃላት ዘልፈዋል በሚል የሊግ አክሲዮን ማህበሩ ክለቡ ላይ የ50ሺህ ብር ቅጣት መጣሉ አይዘነጋም።

ታድያ ከዚህ ቅጣት በኋላ ቡድኑ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች ”ለፈጠርነው ስህተት ይቅርታ ፤ አይለመደንም” የሚል መልዕክት በስታዲየም ይዘው በመገኘት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለሀገራችን እግርኳስ አዲስ ልምምድ በሆነው ይህ “ይቅርታ” በመልካምነት የሚወሰድ ቢሆንም ምን ያህሎቹ ድርጊቶቹ ያልተገባ ስለመሆኑ ተገንዘበው በቀጣይ ታርመው ይቀርባሉ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉ማራኪው የአዳማ ከተማ መለያ

በጨዋታ ሳምንቱ ፋሲል ከነማን የገጠሙት አዳማ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በማራኪ መለያ ብቅ ብለዋል።

በጨዋታው አዳማ ከተማ ከዚህ ቀደም ይጠቁሙባቸው የነበሩት ሁለቱም መለያዎች ማለትም ነጭ በቀይ እና ነጭ በሰማያዊ መለያቸው ከተጋጣሚያቸው ፋሲል ከነማ የመጀመሪያም ሆነ ሁለተኛ መለያ ጋር የሚመሳሰሉ መሆናቸውን ተከትሎ ባለሜዳ የነበረው ፋሲል የመጀመሪያ ምርጫውን እንዲጠቀም ሲደረግ አዳማ ከተማዎች ግን አማራጭ ሦስተኛ መለያ እንዲያቀርቡ ተገደዋል።

በዚህ ሂደትም ታድያ ለሴቶች ቡድኑ ትጥቅ በማቅረብ ላይ የሚገኘው “ጎፈሬ” እጅግ ማራኪ ንድፍ ያለውን እና የክለቡ መለያ ቀለሞችን በሚገባ ያሰባጠረ መለያን በፍጥነት በማምረት ለጨዋታው ያደረሰ ሲሆን በዚህ ሂደት የክለቡ አመራሮችም ሆኑ የትጥቅ አቅራቢው ኩባንያ ሰዎች ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነው።

በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ ምላሽን ያገኘው መለያው በጨዋታ ሳምንቱ በስፋት ሲያነጋግሩ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ ነበር። በተያያዘም ክለቡ እና “ጎፈሬ” አብሮ ለመስራት በሚያስችላቸው ሂደት ላይ ገንቢ ውይይቶችን እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን ምናልባት በቅርቡ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።