[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
👉 “ተክለማርያም፣ ያሬድ እና አሰቻለው ኳሱን ወደ ኋላ በማድረግ ሲጫወቱ ማየት አንፈልግም።”
👉 “ውበቱ ይህን ስላላደረገ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውበቱን ማሰናበት … ?”
👉 “አደገኛ ቦታ ላይ ኳሱን ይዘው መሳቀቅ አንፈልግም።”
👉 ” ሊጉ ደካማ ነው በሚል አማርኛ መርጠን ቃል መዘን ስንዘረዝር ከምንውል ከድክመታችን ተነስተን መሥራት አለብን።”
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቻቸው የካሜሩን ቆይታቸው አስመልክቶ የአስራ ስድስቱ ፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች፣ ምክትል አሰልጣኞች እና የቡድን መሪዎች ተገኙበት በድሬዳዋ ራስ ሆቴል በዛሬው ዕለት ገለፃ አድርገዋል። ለሦስት ሰዓት በቆየው ውይይት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከዝግጅት ጀምሮ እስከተከናወኑት ሦስት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ድረስ ቡድናቸው ምን እንደሚመስል ሪፖርት አቅርበዋል።
በማስከተል የአካል ብቃት ባለሙያው ዶ/ር ዘሩ ያለፈውን አንድ ዓመት በአካል ብቃት ዙርያ ያሉትን ሥራዎች በዝርዝር ካስረዱ በኃላ ከሻይ ሰዓት መልስ ከተሳታፊዎቹ በርከት ያሉ ትኩረትን የሚስቡ ሀሳቦች የተነሱ ቢሆንም አቶ ኢሳይያስ ጅራ በመርሐግብሩ መጠናቀቂያ ላይ የተናገሩዋቸው ነጥቦች ላይ የተናገሩት ትኩረትን የሚስብ በመሆኑ እንዲህ አድርገን አቅርበነዋል።
“ግብጠባቂዎችን በተመለከተ ባለው ክፍተት ከሊግ ካምፓኒ ጋር ተነጋግረናል። መጀመርያ ከላ ማሲያ አካዳሚ አንድ የግብጠባቂዎች አሰልጣኝ ለማምጣት አስበን ነበር። ሆኖም ገንዘቡን ስላበዛብን በዚህ ምክንያት እርሱን ትተን በአሜሪካ የሚገኝ አንድ ባለሙያ አግኝተናል፤ በቅርቡ ይመጣል። በዚህም በሊጉ ያሉ የግብጠባቂዎች አሰልጣኞች አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ስልጠና የሚሰጥ ይሆናል። በተጨማሪም አሁን ያሉት ግብጠባቂዎች ከአሜሪካ ከሚመጣው ባለሙያ ጋር የሚገናኙበት እራሳቸውን የሚለውጡበት ስልጠና እንዲያገኙ ተነጋግረን ጨርሰን ተስማምተናል። አሁን ከሊጉ ካምፓኒው ጋር ተነጋግረናል፤ የእናተን ክለቦችን ይሁንታ ነው የምንጠብቀው።
” እንደ ፕሬዝዳንት ኳስን ከራስ ከሜዳ በሰከንድ ውስጥ ተቀባብሎ በተጋጣሚ ሜዳ የሚጫወት ቡድን እንደምፈልግ ለአሰልጣኝ ውበቱ በግምገማችን ወቅት ነግሬዋለው። ስለ ተጫዋች ምርጫ፣ ስለ አሰላለፍ ሥራዬ ስላልሆነ አውርቼ አላውቅም ማውራትም አልፈልግም። ነገር ግን ሊሰራ ስለሚገባው ነገር ግብ አስቀምጠናል። አሁን መጋቢት ውስጥ ከምናደርገው የወዳጅነት ጨዋታ ጀምሮ ፍሰት ያለው እግርኳስ ነው የምንጫወተው። በግምገማው ወቅት ከውበቱ ጋር ስንነጋገር ተክለማርያም ሻንቆ፣ ያሬድ ባዬ እና አሰቻለው ታመነ ኳሱን ወደ ኃላ በማድረግ ሲጫወቱ ማየት እንደማንፈልግ፤ ወደ ፊት በመሄድ የሚያጠቃ ቡድን እንደተቋም እንደምንፈልግ ገልፀናል። ይህ እንዴት ይሆናል የሚለው ቴክኒካል ጉዳይ ነው። ለባለሙያ የምተወው ጉዳይ ነው። ግን እዛው አደገኛ ቦታ ላይ ኳሱን ይዘው መሳቀቅ አልፈልግም። መጫወት ካለብን መጫወት ባለብን አግባብ መሆን አለበት። እግርኳስ ስለሆነ እቅዳችን ወደፊት የሚጫወት ልጅ ነው የሚያስፈልገው። በዚህ ዙርያ ሁላችሁም ትስማማላችሁ ብዬ ነው የማስበው። ከካሜሩን ጋር የመጀመርያ አርባ አምስት እንዴት ጥሩ መንቀሳቀስ ቻልን የሚለውን ትኩረት ሰጥተን ይህን ማሳደግ ይገባናል። ወደ ሊጋችንም እንዴት አውርደን እናምጣው የሚለውም የሁላችንም ሥራ ነው።
” ከሊጉ ጋር በተያያዘ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ሊጉ ደካማ ነው በሚል በገለፀው ድክመቱ የሁላችንም ነው። አማርኛ መርጠን ቃል መዘን እርሱን ስንዘረዝር ከምንውል መሥራት የሚገባንን ነገር ከድክመታችን ተነስተን መሥራት አለብን። መሐል ሜዳ ጎል የሚገባበት በረኛን እንደዚህ ዝለል ብሎ መቼም ደሳለኝ አያስተምርም። ሁሉም ነገር ከአሰልጣኙ መጠበቅ የለበትም። ስለዚህ ድክመቱ የሁላችንም በመሆኑ በጋራ መሥራቱ የተሻለ ነው።
” ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ያደረጋቸው ጨዋታዎች ጠቅመውታል፤ ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል። ግን በአፍሪካ ዋንጫ በዚህ ደረጃ አልተንቀሳቀስም። ይሄን ገምግመናል። ውበቱ ይህን ስላላደረገ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውበቱን ማሰናበት፤ ኢሳይያስ መልቀቅ አለበት የሚል ዘገባ የምንሰራ ከሆነ ይህ ስህተት ነው። ተቋም የሚመራው በስርዓት ነው። ዋናው የሚፈለገው ዛሬ የተነጋገርንበትን ልጆቻቹ ላይ ትኩረት ማድረግ ክፍተቶቻችን ላይ መሥራት ነው። የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ከአየር አይመጣም ከክለብ ነው የሚመጣው። ስለዚህ መቶ ፐርሰንት ጨርሶ መላክ ባይቻል እንኳን አሻሽሎ መላክ ያስፈልጋል። ብሔራዊ ቡድን በዘጠኝ ቀን የማቀናጀት ሥራ ነው የሚሰራው እንጂ ብዙ ለውጥ አመጣለው ብለህ አታስብም። ስለዚህ ግብ አስቀምጠን ከምድብ አለማለፋችን እንደ ተቋም ያስቆጨናል።”