‹‹ በሁለቱ ጨዋታ ነጥቦች በመሰብሰብ በማጣርያው ወደ ጥሩ ምዕራፍ ለማምራት ጥረት እናደርጋለን›› አብዱልከሪም መሀመድ

ስዩም ተስፋዬ በመጎዳቱ ምክንያት በምትኩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጥሪ የደረሰው አብዱልከሪም መሀመድ ከአልጄርያ ጋር በሚደርደርጓቸው ጨዋታዎች ነጥቦች ለመሰብሰብ የተቻላቸውን ያህል እንደሚጥሩ ትላንት ወደ አልጄርያ ከማምራታቸው በፊት ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አጭር አስተያየት ተናግሯል፡፡

‹‹ ለአልጄርያው ጨዋታ እንደ ቡድንም በግልም ጥሩ ነገር ለማድረግ ጥሩ ተዘጋጅተናል፡፡ አልጄርያ ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ተጫዋቹም ልምድ ያላቸውና በአወሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ የሚቻለንን ጥረት አድርገን አሰልጣኛችን የሚነግረንን እየተገበርን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅተናል ብዬ ነው የማስበው፡፡ በሁለቱ ጨዋታ ነጥቦች በመሰብሰብ በምድብ ማጣርያው ወደ ጥሩ ምዕራፍ ለማምራት ጥረት እናደርጋለን፡፡›› ሲል ከአልጄርያው ጨዋታ ውጤት ይዘው እንደሚመለሱ ተስፋ አድርጓል፡፡

አብዱልከሪም የመጀመርያም የመጨረሻም የብሄራዊ ቡድን ጨዋው ያደረገው በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ማላዊን አስተናግዳ ካለግብ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ነበር፡፡ ከዛ ወዲህ ለብሄራዊ ቡድን መጫወት ያልቻለው አብዱልከሪም ኡን ከጉዳት ነጻ ሆኖ ዋልያዎቹን ለማገልገል እንደተዘጋጀ ተናግሯል፡፡ ‹‹ ከብሄራዊ ቡድን ለመራቄ ዋንኛው ምክንያት ጉዳት ነበር፡፡ ከማላዊው ጨዋታ በኋላ የብሄራዊ ቡድን ጥሪ ቢደረግልኝም በጉዳት ምክንያት ሳልካተት ቀርቻለሁ፡፡ አሁን ከጉዳት ነፃ ሆኜ በክለቤ ጥሩ በመንቀሳቀሴ ወደ ብሄራዊ ቡድን ተመልሻለሁ፡፡ ጥሩ አገልግሎት ለማበርከትም ዝግጁ ሆኛለሁ፡፡›› ብሏል፡፡

የቀኝ መስመር ተከላከዩ ሲዳማ ቡናን ለቆ ኢትዮጵያ ቡናን ከተቀላቀለ በኋላ እንደወትሮው ድንቅ ብቃቱን ማሳየቱን ቀጥሏል፡፡ አሰልጣን ድራጋን ፖፓዲች ከተፈጥሯዊ ቦታው ባሻገር በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ በአማካይ መስመር ላይ ሲያጫውቱት ተስተውሏል፡፡ አብዱልከሪም ሁልጊዜም ምርጫው በመስር ተከላካይነት መጫወት እደሆነ ገልፆ በየተኛውም ሚና ቢሰለፍ ግን ለመጫወት ዝግጁ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ‹‹ በእኔ ሀሳብ በግልም ሆነ ለቡድኑ የተሻለ ነገር ማበርከት የምችለው በለመድኩት የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ስሰለፍ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ አሰልጣኞች ተጫዋቾችን ራሳቸው በሚፈልጉት ቦታ ሊያሰልፉ ይችላሉ፡፡ ዋናው ነገር የሚሰጠኝን ሚና በብቃት ለመጫወት ሁሌም ራሴን ማዘጋጀቴ ነው፡፡ ››

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *