[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
እስካሁን በሊጉ ስድስት ስድስት ጨዋታዎችን ያሸነፉት ሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከነማ የሚያረጉትን የ13ኛ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ-ግብር በሚከተለው መልኩ ዳሰነዋል።
ከአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ግስጋሴ በኋላ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በባህር ዳር ከተማ የተረታው ሀዋሳ ከተማ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመዝለቅ እና የነገ ተጋጣሚውን ፋሲል ቦታ ለመረከብ ማሸነፍ የግድ ይለዋል።
በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ያለ የሚመስለው ሀዋሳ ከተማ በባህር ዳር ከተማ ከመረታቱ በፊት በየጨዋታው በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥር፣ ግቦችን የሚያገባ፣ ታታሪ እና ተመርቶም ቢሆን ውጤት ለመለወጥ የሚጥር ቡድን ነበር። በተለይ ሦስት ነጥብ ካስረከበበት ጨዋታ በፊት በ5 ጨዋታዎች ብቻ 50 የግብ ማግባት ሙከራዎችን ተጋጣሚ ላይ ሰንዝሯል። ከተጠቀሱት ጨዋታዎች ላይ ደግሞ ሦስቱ ላይ ቀድሞ ግብ ተቆጥሮባቸው ሁለቱን ሲያሸንፉ አንዱን አቻ ተለያይተዋል። ከጣና ሞገዶቹ ጋር ሲጫወቱ ግን የወትሮ መታተር እና ግብ ጋር በፈጣን ሽግግሮች መድረስ አይስተዋልባቸውም ነበር። ይህ ድካም መሰል ነገር በድሬዳዋው ጨዋታ ካወጡት እጅግ ከፍተኛ ጉልበት እንደመጣ የሚገመት ሲሆን ከነገው ጨዋታው በፊት ባገኙት የአምስት ቀን እረፍት ግን አገግመው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ እና የወትሮ ብቃታቸውን እንደሚያሳዩ ይታመናል።
በ12 የጨዋታ ሳምንታት ቡድኑ ተጋጣሚ ላይ ካስቆጠራቸው 14 ግቦች 78.5 % የሚሆነውን ከመረብ ያገናኙት ፈጣኖቹ አጥቂዎች ብሩክ፣ መስፍን እና ኤፍሬም ነገም የፋሲሎች የራስ ምታት እንደሚሆኑ እሙን ነው። በዋናነት ደግሞ ዘለግ ያሉ ደቂቃዎችን ከኳስ ውጪ እንደሚያሳልፍ የሚታሰበው ቡድኑ በሽግግሮች ከፍ ብሎ የሚከላከለው የፋሲል ተከላካዮች ጀርባ ተጫዋቾቹ እንዲገኙ እያደረገ ግብ ለማግኘት እንደሚጥር ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ግን እምብዛም የኋላ መስመር እንከን የማይስተዋልበት ቡድኑ በባህር ዳሩ ጨዋታ የተቆጠሩበት ሁለት ጎሎች መጠነኛ ጥገና እንደሚሻው አሳባቂ ነበሩ። የመጀመሪያውን ግብ ንኪማ ሲያስቆጥር በቡድናዊ መዋቅር ከመግባባት ክፍተት የተፈጠረ ስህተት ሲታይ ሁለተኛውን ግብ ደግሞ ፉዐድ በሳቢ ሁኔታ ሲያገባ በተመሳሳይ የቆመን ኳስ በአግባቡ የመከላከል ችግር እንዳለ አይተናል። የነገ ተጋጣሚው ፋሲል ጎል ፊት ርህራሄ ቢስ ስለሆነ ግን ይህንን እንከን አርሞ ጨዋታውን መጀመር ይጠበቅበታል።
ሊጉን በጥሩ ብቃት ጀምሮ የነበረው ፋሲል ከነማ አሁናዊውን ወጥ ያልሆነ ጉዞ ለማስተካከል እና ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ከሆኑ ቡድኖች ለመራቅ እንዲሁም ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ማሸነፍን እያሰበ ጨዋታውን እንደሚቀርብ ይታለማል።
የወቅቱ የሊጉ ባለክብር ፋሲል ከነማ በወጥነት ጨዋታዎችን በተከታታይ ማሸነፍ ካቃተው 9 የጨዋታ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ቡድኑ በእንቅስቃሴ ደረጃ ለትችት የሚዳርገው ብቃት ባያስመለክትም ነጥብ በተጋራበት የአዳማ መርሐ-ግብር በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ግን ሲቸገር አስተውለናል። ከቆመ ኳስ ውጪ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠርም ሲከብደው ነበር። እርግጥ ይህ በሁለተኛው አጋማሽ ቢሻሻልም ደቂቃዎች እያለቁ በሄዱ ጊዜ መጣደፍ ውስጥ ከሚገባ በቶሎ ጨዋታን መቆጣጠር ያለበት ይመስላል። በዋናነት ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ሁለተኛው የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለብ የሆነው ስብስቡ የሚተማመንበት ጎል አዳኝ ያለው አይመስልም። ቡድኑ ካስቆጠራቸው 19 ጎሎች ዘጠኝ ተጫዋቾች ስማቸው መኖሩ የጎል ማግባት ስብጥሩን ቢያሳይም ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሆነ የሚታመነው ቡድኑ እንደሚፈጥራቸው ዕድሎች ለጎል ቅርብ ከሆነ ተጫዋች ግቦችን ማግኘት እንሚኖርበት ይታሰባል። ይህ ቢሆንም ግን የአማካይ መስመሩን እና የአጥቂ መስመሩን በሚገባ ሲያገናኝ የሚታየው ሱራፌል በቆመ ኳስም ሆነ በክፍት ጨዋታ የሚፈጥራቸው ዕድሎች ነገ ለሀዋሳዎች ፈታኝ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ በመቀጠል ከአርባምንጭ ጋር በጣምራ የሊጉ ሦስተኛው ትንሽ ግብ ያስተናገደ የኋላ መስመር ባለቤት የሆነው ፋሲል በድፍረት ወደ መሐል ሜዳ ተጠግቶ የሚከላከልበት መንገድ ነገ ፈተና ላይ እንዳይጥለው ያሰጋል። በተለይ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ እንደተቸገረበት አጋጣሚ በሽግግሮች የራስ ምታት እንዳይበዛባቸው ቀድመው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። በተለይ የሀዋሳ አጥቂዎች ፈጣን መሆናቸው ሲታወስ ደግሞ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ እንረዳለን። በተቃራኒው በሁለቱም መስመሮች እንዲሁም በመሐል ለመሐል በቁጥር በርከት ብሎ የሚያጠቃው ቡድኑም ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑን ለማስመስከር በከፍተኛ ፍላጎት እንደሚጫወት ስለሚገመት ሀዋሳም በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ መሰረት ሊኖረው ይገባል።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና አለመኖሩ ተመላክቷል። ይህንን ጨዋታም ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በመሐል አልቢትርነት ሲመራው ፋሲካ የኃላሸት እና ሙስጠፋ መኪ ረዳት ተከተል ተሾመ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው እንዲያገለግሉ እንደተመደቡ አውቀናል።
ግምታዊ አሠላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)
መሐመድ ሙንታሪ
ዳንኤል ደርቤ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – መድሀኔ ብርሀኔ
ወንድማገኝ ኃይሉ – አብዱልባስጥ ከማል – በቃሉ ገነነ
ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ
ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)
ሚኬል ሳማኬ
ሰዒድ ሁሴን – አስቻለው ታመነ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው – ሀብታሙ ተከስተ
ሽመክት ጉግሳ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ
ኦኪኪ አፎላቢ