ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙትን ቡድኖች ጨዋታ የተመለከተ ዳሰሳችንን እነሆ።

በደረጃ ሰንጠረዡ የወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆነው የመጀመሪያ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን የሚያደርጉት ሰበታ እና አዲስ አበባ በጥቂቱ ተንፈስ ለማለት የሚረዳ ቀለል ያለ ተጋጣሚ የሚገኙበትን ጨዋታ ይከውናሉ። ሆኖም ከእስካሁኑ ውጤት አንፃር ደካማ ተጋጣሚን ያግኙ እንጂ ተመሳሳይ ችግር ላይ መሆናቸው የጨዋታውን ፉክክር ከፍ እንደሚያደርገው ይገመታል። ተጋጣሚዎቹ በመጨረሻ አራት ጨዋታዎቻቸው በሙሉ ሽንፈት አስተናግደው ለነገ ምሽቱ ጨዋታ ሲደርሱ በጅማ ሽንፈት የመጨረሻ ደረጃ ላይ ከመቀመጥ የተረፈው ሰበታ አንድ ድል ለአራት ሳምንታት ብቻ የዘለቀ ጥሩ አቋም አሳይቶ የነበረው አዲስ አበባ ደግሞ ሦስት ድሎችን አሳክተዋል።

ሰበታ ከተማ ከቡድን መዋቅር አንፃር ከተጋጣሚው በባሰ ችግር ውስጥ ያለ ይመስላል። ተለዋዋጭ የተጨዋቾች ምርጫን እየተከተለ የቀጠለው ቡድኑ የኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርቶ ለመጫወት ሀሳብ ያለው ቢመስልም በተግባር ግን ይህ አካሄዱ ለተጋጣሚዎቹ አሳልፎ ሲሰጠው እንጂ የሚያልመውን ውጤት ሲያስገኝለት አይስተዋልም። በተለይም ከራሱ ሜዳ ኳስ መስርቶ የሚወጣበት ሂደት ሁነኛ በሆነ እና በድግግሞች በጎለበተ እንዲሁም የሚተማመንበት የጨዋታ አቀጣጣይ ባለው የአማካይ ክፍል የሚታገዝ ባለመሆኑ ተጋጣሚዎቹ በቀላሉ ለማቋረጥ ሲቸገሩ አይታይም። በየጨዋታው በእንቅስቃሴም ሆነ በቆሙ ኳሶች የተለያዩ ዓይነት እክሎች የማያጡት የኋላ ክፍሉም ከአጠቃላይ የቡድኑ በስሜት የወረደ የማሸነፍ ሥነ ልቦና ጋር ተዳምሮ ችግር አላጣው ብሏል። ነገም አዲስ አበባዎች የመልሶ ማጥቃት ቀመራቸውን መልሰው ካገኙ የሰበታ እነዚህ ደካማ ጎኖች ችግር ሊሆኑበት መቻላቸው አይቀርም።

ከሰበታ የተሻለ ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ ድክመትም ብዙ ነው። ቡድኑ ጥሩ ውጤቶችን ባስመዘገበባቸው ጨዋታዎች የነበረውን ጠንካራ ጎን በሚገባው መጠን መመዘን አለመቻሉ ግን ዋነኛው እንደሆነ የኢትዮጵያ ቡናው ሽንፈት አሳይቶን አልፏል። በዛ ጨዋታ እስከምን ድረስ እንደሆነ ባይታወቅም በሙሉ አቅም የመከላከል እቅድ ያለው ይመስል የነበረው አዲስ አበባ በመጀመሪያ የተጨዋቾች ምርጫው አንድም የተሳካ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበት ሳይፈጥር እንዲሁም መከላከሉንም በቅጡ ሳይተገብር ግብ አስተናግዶ ፍፁም የተረበሸ ቡድን ሆኖ ነበር።

በቀጣዩ አጋማሽ ደግሞ ለቀጥተኛ አጨዋወቱ የሚሆኑትን ቅያሪዎች አድርጎ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ተጋጣሚ ሳጥን ደርሶ ዕድሎችን መፍጠር እንደሚችል በተደጋጋሚ አሳይቷል። ከዕድሎቹ አንፃር ወደ ግብ የመቀየር ችግሩ ከፋ እንጂ ጨዋታውን በሰፊ ጎል የማሸነፍ ዕድል ነበረው። ይህንን ለተመለከተ አዲስ አበባዎች በትክክለኛው የጨዋታ ዕቅድ እና የተጨዋቾች ምርጫ ሰበታን በመልሶ ማጥቃት ለማግኘት ያልተዛነፈ ዕቅድ ይኖራቸው ይሆን ? ብሎ እንዲጠይቅ ያስገድደዋል።

ሰበታ ከተማ ቢያድግልኝ ኤልያስ እና አስቻለው ታደሰን በጉዳት ሲያጣ ወልደአማኑኤል ጌቱ በጉዳት መሰለፉ አጠራጣሪ ሆኗል። በተጨማሪም የመስመር አጥቂው ዮናስ አቡሌ ከክለቡ ጋር አለመግባባት ውስጥ በመሆኑ ጨዋታው ያልፈዋል። በሌላ በኩል ምንም የቅጣት ዜና የሌለበት አዲስ አበባ ከተማ ከነብዩ ዱላ እና ፈይሰል ሙዘሚል ውጪ በጉዳት ተጫዋች አያጣም። ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ዜና ግን በወቅታዊ የቡድኑ ውጤት ብቃታቸው ወርዷል ለተባሉ እና ስማቸው እንዲገለፅ ያልተፈለጉ ተጫዋቾች ከትናንት በስትያ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደተሰጣቸው ሰምተናል።

ጨዋታውን አባይነህ ሙላት በዋና ዳኝነት ዳዊት ገብሬ እና ዘሪሁን ኪዳኑ በረዳትነት እንዲሁም ዮናስ ማርቆስ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ሰለሞን ደምሴ

ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

በኃይሉ ግርማ – ሀምዛ አብዱልሀሚን

ሳሙኤል ሳሊሶ -አብዱልሀቪዝ ቶፊቅ – ፍፁም ገብረማሪያም

ዘካሪያስ ፍቅሬ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ሳሙኤል አስፈሪ – ዘሪሁን አንሼቦ – ሳሙኤል ተስፋዬ

ኤልያስ አህመድ – ቻርለስ ሪባኑ – ሙሉቀን አዲሱ

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ አዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን

ያጋሩ