[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የ13ኛ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ-ግብር የሆነው የሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ አስደናቂ የሁለተኛ አጋማሽ ፉክክር አስመልክቶ በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ የተረቱት ሀዋሳ ከተማዎች የጨዋታ አቀራረብ ቅርፅ እና ተጫዋች ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል። አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ባደረጉት ለውጥም ፀጋሰው ድማሙ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ እና ተባረክ ሔፋሞን በአዲስዓለም ተስፋዬ፣ አብዱልባሲጥ ከማል እና ብሩክ በየነ ምትክ በአሰላለፋቸው አስገብተዋል። ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ አቻ ተለያይተው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ፋሲል ከነማዎች ደግሞ ሁለት ነጥብ ከጣሉበት ፍልሚያ በተመሳሳይ የተጫዋች አደራደር ቅርፅ እና ተጫዋች ለውጠዋል። በዚህም አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ሰዒድ ሀሰን፣ አምሳሉ ጥላሁን እና ሀብታሙ ተከስተን አሳርፈው ሳሙኤል ዮሐንስ፣ ያሬድ ባየህ እና ዓለምብርሃን ይግዛውን አሰልፈዋል።
የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ይህ ጨዋታ አጀማመሩ ላይ የፋሲል ከነማ የበላይነት የታየበት ነበር። ቡድኑም ተደጋጋሚ የቆሙ ኳሶችን በማግኘት በጊዜ መሪ ለመሆን ሲጥር ነበር። በደቂቃዎች ልዩነት ከተገኙት በርካታ የቆሙ ኳሶች መካከል ደግሞ በ7ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ዮሐንስ ወደ ግብ የላከው ኳስ ሙንታሪን የፈተነ ነበር። በተቃራኒው ወደራሳቸው ግብ ተጠግተው ለመከላከል ያሰቡት ሀዋሳዎች የመልሶ ማጥቃቶችን እንደዋነኛ የግብ ምንጭነት ለመጠቀም ሲጥሩ አስተውለናል።
በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉት ፋሲሎች የውሀ እረፍት ከማምራታቸው ከሰደንዶች በፊት ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ጫፍ አክርሮ በመታው ኳስ አስደንጋጭ ጥቃት ፈፅመዋል። በ32ኛው ደቂቃ ደግሞ የቀኝ መስመር ተመላላሹ ዓለምብርሃን ይግዛው ከፀጋሰው ድማሙ ጋር ታግሎ ወደ መሐል መሬት ለመሬት የላከውን ኳስ ኦኪኪ አፎላቢ በግራ እግሩ ከግብ ጋር ለማዋሀድ ጥሮ ወጥቶበታል። ለዚህ ሥል ጥቃት ምላሽ ለመስጠት የፈለጉ የሚመስሉት ሀዋሳዎች በቀኝ መስመር ተባረክ በሞከረው ኳስ የፋሲልን ግብ ፈትሸው ተመልሰዋል። አጋማሹም ጥሩ የታክቲካል ፍልሚያ ቢታይበትም ተመልካችን ቁጭ ብድግ የሚያሰኝ የግብ ማግባት ዕድል ሳይበረክትበት ተጠናቋል።
ፋሲል ጨዋታውን ከኳስ ጋር ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ከኳስ ውጪ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት በሁለተኛውም አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቀጥለዋል። አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በመጀመሪያው አጋማሽ ያላደረጉት ሀዋሳዎች በ56ኛው ደቂቃ በመስፍን አማካኝነት ሌላ ጥቃት ለመሰንዘር ቢዳዱም በግቡ ብረቶቹ መሐከል አሁንም ኳስ መላክ አልቻሉም። ይሁ አጥቂ ከደቂቃ በኋላም ሌላ ኳስ ከግራ መስመር በግራ እግሩ ሞክሮ ወጥቶበታል።
ጨዋታው 60ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ኳስ እና መረብ ተገናኝቶ ሀዋሳ ከተማ ወደ መሪነት ተሸጋግሯል። በዚህም መሐመድ ሙንታሪ በረጅሙ የላከውን ኳስ ሔኖክ ድልቢ በግንባሩ ሁለተኛ ኳስ ለማመቻቸት ሲጥር የመሐል ተከላካዩ ከድር ኩሊባሊ ለግብ ዘቡ ሚኬል ሳማኪ አቀብላለው ሲል ግብ ጠባቂው ክልሉን ለቆ በመውጣቱ ኳሱ መረብ ላይ አርፏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ፍጥነቱ እጅግ ጨምሮ የታየው ይህ ጨዋታ ወዲያው የአቻነት ጎል ሊያስተናግድ ነበር። በዚህም ሽመክት ጉግሳ ጥሩ ኳስ ሞክሮ ተከላካዮች አምክነውበታል። ወደ መሪነት የተሸጋገሩት ሀዋሳዎች ከግቡ በኋላ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ሙከራዎችን በተባረክ አማካኝነት አድርገው ነበር።
ለስምንት ደቂቃዎች ብቻ የተመሩት ዐፄዎቹ ያደረጓቸው የተጫዋች ለውጦች ፍሬ አፍርቶላቸው አቻ ሆነዋል። በዚህም ግብ ካስተናገዱ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ቀይረው ያስገቧቸው ሰዒድ ሀሰን እና ፍቃዱ ዓለሙ በድንቅ ሁኔታ ተገናኝተው ለቡድናቸው ግብ አስገኝተዋል። በ68ኛው ደቂቃም ሰዒድ በድንቅ ሁኔታ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ፍቃዱ ከተከላካዮች አፈትልኮ በመውጣት በግራ እግሩ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
እንደ አጀማመሩ ያልዘለቀው ይህ ጨዋታ እጅግ በርካታ ሙከራዎች ማስተናገድ ይዟል። በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድራማዊ ክስተቶች ተስተናግዷበታል። በ85ኛው ደቂቃ የቆመ ኳስ ያገኙት ፋሲሎች ኳሱን ወደ ሳጥን ልከው ሽመክት አግኝቶት ወደ ግብ ሲልከው የግቡ አግዳሚ መልሶታል። ይህ ሙከራ ያላስደነገጣቸው ሀዋሳዎች ይህንኑ ኳስ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ግብ አድርገውታል። በዚህም ወንድማገኝ ኃይሉ እጅግ በአስደናቂ ሁኔታ ከ50 ሜትር በላይ ኳስ ገፍቶ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳ ባለቀ ሰዓት ወደ ፈንጠዝያ አምርቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሀዋሳ አሸናፊነት ተገባዷል።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 23 አድርሶ የፋሲልን ሁለተኛ ደረጃ ሲረከብ ፋሲል በ22 ነጥቦች ወደ ሦስተኛ ደረጃ ተንሸራቷል።