የሳምንቱ መርሀ-ግብር መገባደጃ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን እነሆ !
አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በአንድ ነጥብ የሚበላለጡ ሁለት ቡድኖችን የሚያገናኘውን ጨዋታ የነገው ቀዳሚ ፍልሚያ ይሆናል።
በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ላይ ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ድሬዳዋ ከተማን ሁለት ለአንድ ያሸነፉት አዳማ ከተማዎች ተጋጣሚያቸውን በአንድ ነጥብ በልጠው በዘጠኝ ነጥቦች በስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አዳማዎች በሊጉ የመጀመርያ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግባቸውን ሳያስደፍሩ ቆይተው በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች አስተናግደዋል። በሊጉ ጅማሮ የቡድኑ ዋነኛው ጥንካሬ የነበረው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀትም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥንካሬውን እያጣ እንደሚገኝም ቁጥሮቹ ማሳያ ናቸው።
አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የአሸናፊነት መንገዱን ከማስቀጠል ባለፈ ይህንን የቀደመ ጥንካሬያቸው መልሰው የማግኘት የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። ቡድኑ ምንም እንኳ በመከላከሉ መቀዛቀዝ ቢታይበትም በአንፃሩ የማጥቃት ክፍሉ እጅግ ተሻሽሏል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎችም በየጨዋታው ሁለት ሁለት ግቦች አስቆጥረዋል። ይህንን የቡድኑ ክፍልም የወቅቱ ዋነኛ ጥንካሬያቸው ሆኗል። በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ግቦች ያስተናገዱት ኢትዮጵያ ቡናዎችም በዚህ የአዳማ ከተማ ጥንካሬ መፈተናቸው አይቀሪ ነው።
ድሬዳዋ ከተማን አንድ ለባዶ ካሸነፉ በኋላ ወደ ድል መመለስ ያልቻሉትና በስምንት ነጥቦች በ8ኛ ደረጃነት የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በውድድር ዓመቱ ሽንፈት ያልገጠመውን አዳማ ከተማ ይገጥማሉ። ቡናማዎቹ እንደተጋጣምያቸው ሁሉ በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ነበራቸው። ሆኖም ይህንን ዋነኛ የቡድኑ ጥንካሬ ማስቀጠል አልቻሉም። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎችም በአማካይ ሁለት ግቦች በማስተናገድ መጥፎ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችለዋል። ሰርብያዊው አሰልጣኝ በነገው ጨዋታ የቀደመው ለተጋጣሚዎች ክፍተት የማይሰጥ እና ጠጣር አቀራረባቸው መልሰው ይጠቀማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ምክንያቱም የአዳማ ከተማ የአጥቂ ጥምረት ጥሩ ወቅታዊ ብቃት ለመግታት የተሻለው መንገድ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ።
የቡድን ዜናን ስንመለከት በኢትዮጵያ ቡና በኩል አማካዩ አብዱልከሪም ወርቁ በጉዳት ምክንያት ለነገው ጨዋታ አይደርስም። አዳማ ከተማን የተመለከተ የቡድን ዜና ለማካተት ያደረግነው ጥረት ከአሰልጣኝ ቡድን አባላት ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ የሆነ አካል ባለመኖሩ ሳይሳካ ቀርቷል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 42 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 23 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አዳማ ከተማ በበኩሉ 7 ጊዜ ድል ሲቀናው በ12 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 75 ፤ አዳማ 37 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ይህንን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ በመሐል ዳኝነት ይመራዋል፤ ደረጄ አመራ እና አብዱ አሊ በረዳትነት፤ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በሊጉ ሽንፈት ያላስተናገዱ ሁለት ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ የሳምንቱ መቋጫ ይሆናል።
ካከናወኗቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት አቻና ሁለት ድል በማስመዝገብ ምንም ሽንፈት ያልቀመሱት ሀዋሳዎች በዘጠኝ ነጥቦች በ7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤት በኋላ ሲዳማ ቡናን አንድ ለባዶ አሸንፈው ወደዚህ ጨዋታ የሚቀርቡት ሀይቆቹ በሊጉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ካላቸው ክለቦች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ቡድኑ በመጀመርያው ጨዋታ በፋሲል ከነማ ሦስት ግቦች ከተቆጠረበት ወዲህ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን አላስደፈረም። አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ላለፉት ጨዋታዎች የተከተሉት ጠጣር አጨዋወት ይቀይራሉ ተብሎ ባይጠበቅም አጨዋወቱ ግን እንደሚፈለገው የግብ ዕድሎች ማምረት አልቻለም፤ የቡድኑ ሚዛን ላይም ውስን ለውጦች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩ ሲታይ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም።
ከአምስት ጨዋታዎች አስራ አንድ ነጥቦች ሰብስበው በአምስተኛ ደረጃነት የተቀመጡት ንግድ ባንኮች እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ሽንፈት አላስተናገዱም። በተከታታይ ወልቂጤና ድሬዳዋ ላይ ያስመዘገቡት ድል ለማስቀጠልም ጠጣሩን ሀዋሳ ከተማ ይገጥማሉ። ቡድኑ ባለፉት ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች በአጥቂ ክፍላቸው ላይ በጎ ለውጦች ታይተውበታል። በሊጉ ጅማሮ ላይ ግቦችን ለማስቆጠር ሲቸገሩ ቢስተዋሉም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን አምስት ግቦች በማስቆጠር ችግሩን ቀርፈዋል፤ በነገው ዕለት የሚገጥሙት ቡድን ግን ግብ ካስተናገደ 360 ደቂቃዎች ያስቆጠረ ቡድን እንደመሆኑ የአጥቂ ክፍላቸው ከወትሮው ለየት ባለ ጥንካሬ መቅረብ ይጠበቅበታል። ንግድ ባንክ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ካላቸው የሊጉ ክለቦች አንዱ ነው፤ ከአምስቱ ጨዋታዎች በሦስቱ ግቡን ሳያስደፍር ከመውጣቱም ባለፈ ድሬዳዋ ከተማን በገጠመበት ጨዋታም ብቻ ነው ከአንድ ግብ በላይ ያስተናገደው።
ሀዋሳዎች በቅጣትም በጉዳትም የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ተከላካዩ ካሌብ አማንክዋህ ከጉዳት መልስ የመጀመርያ የሊግ ጨዋታውን ያደርጋል ጉዳት ላይ የነበረው ፉአድ ፈረጃም ከጉዳት አገግሞ ወደ ልምምድ ተመልስዋል።
ከ2009 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በአጠቃላይ 35 ጊዜ የግንኙነት ታሪክ አላቸው። ንግድ ባንክ 12 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን በ13 ጨዋታ አቻ ተለያይተው ሀዋሳ 10 አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ንግድ ባንክ 35 ሀዋሳ ደግሞ 36 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ይህንን ዳኛ አዲስ አዳጊው ዳኛ መለሠ ንጉሴ የመምራት ሀላፊነቱን ሲወስድ ፣ አሸብር ታፈሠ እና ሚፍታ ሁሴን በበኩላቸው በረዳትነት ፣ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በአንፃሩ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተሰይሟል።