የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 2-1 ፋሲል ከነማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ጥሩ ፉክክር ባስተናገደው እና በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ጨዋታው እንዳሰቡት ስለመሄዱ

“ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች ይሻላል። ነገር ግን ግብ ለማግኘት ያደረግናቸው ነገሮች ጥሩ አልነበሩም። ከሌላው ጊዜ በተሻለ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጥሩ ለመሆን ሞክረናል። ያ ጨዋታ በውጤት ቢታጀብ ነበር መልካም የሚሆነው። ከዕረፍት መልስም ያንን ለማስቀጠል ነበር የተነጋገርነው። በጎል የቀደሙበት ሁኔታ የእኛን ስሜት ሲጎዳ እነሱን አነሳስቷል። ከዛም ልጆቼ ጥረት አድርገዋል ፤ አቻ የመሆን ዕድልም ገጥሞናል። የሁለተኛው ጎል መንስኤ ጉጉት ነው። ምክንያቱም ዓላማችንም ዕቅዳችንም ይህንን ጨዋታ ለማሸነፍ ነበር። ያን ለማድረግ በተሄደበት ሰዓት በነበረው መልሶ ማጥቃት ቅርፃችንን አለመያዛችን ሁለተኛ ጎል አስከትሏል። አሁንም ቢሆን ከፊት ካለው ግሩፕ ጋር ያለን ስለሆንን ይሄንን በትዕግስት ማየት ያስፈልጋል ፤ በሰከነ መልኩ ማየት ያስፈልጋል። ገና ብዙ ውድድር አለ አሻሽለን እንመጣለን ብዬ ነው የማስበው።

ፋሲል አሁንም ፉክክር ውስጥ ስለመሆኑ

“በትክክል ፤ እንደምታየው እኛ ብቻ ሳንሆን ከእኛ በታች ያሉት በሙሉ አንድ ቋት ውስጥ ነው ያለው። ከዛ ቋት ለመውጣት ነው የሁላችንም ጥረት። የዛሬው ውጤታችን እኛንም ደጋፊያችንንም እንደሚያስከፋ እርግጠኛ ነኝ። ከዚህ ለማሻሻል ግን ትዕግስት እና ጥረት ያስፈልጋል ብዬ ነው የማስበው።”

ሰልጣኝ ዘርዓይ መሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ይመስገን። ያሸነፍንበት አንደኛ መጀመሪያም ለመግለፅ እንደሞከርኩት ከመስመር በሚሄዱ ኳሶች የሚያጠቃ ቡድን ነው ፋሲል። በተመሳሳይ ግን ባልጠበቅነው መንገድ እነሱም የእኛን ፎርሜሽን ነው ሲጠቀሙ የነበረው ፤ እነሱም ሦስት ተከላካይ ነበር የተጠቀሙት። ይህንን አጋጣሚ እንደምናገኝ እርግጠኛ ነበርን። ምክንያቱም ፋሲል አምና ቻምፒዮን የነበረ ቡድን ነው ፤ ዘንድሮም ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን ነው። ተከላካዮቹ ነቅለው እንደሚወጡ መቶ ፐርሰንት እርግጠኛ ነበርን። በአጋጣሚ ጎሉን አገባን ጫና ስንፈጥርባቸው እንደገና ጫና ፈጥረው መጡ ፤ አቻ ሆኑ። ሁለተኛ ጎል ለማግባት ግን በተደጋጋሚ እንደሚመጡ እርግጠኞች ነበርን። ስለዚህ ባገኘው አጋጣሚ ያንን የእነሱን ድክመት ተጠቅመን ሁለተኛውን ጎል አስቆጥረናል እና ታክቲካሊ ብዙ ነገር የታየበት ጨዋታ ነው ብዬ አስባለሁ።

ስላሳዩት የደስታ አገላለፅ

“አንዳንዴ ከትልቅ በድን ጋር ስትጫወት ራስህንም የምትፈትንበት ነው። የልጆችህንም አቅም የምታይበት ነው። አሁን እንዴት ሆንክ ብትለኝም አላውቀውም። ምክንያቱም ጎሉን ያስቆጠርንበት ሰዓት ራሱ ሌላ ደስታ የሚፈጥር ነው። ይሄ ማለት ደግሞ ቆምን ማለት አይደለም። ቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች አሉ። የባህር ዳር ጨዋታ ለእኛ ትምህርት ነው ብዬ ነው የማስበው። እና በዛ መንገድ ቀጣይ ተጋጣሚያችንን አስበን ትኩረት አድርገን ተጫወትን ውጤት ይዘን ለመሄድ ነው የምናስበው ከድሬዳዋ።

በድጋሚ በመጨረሻ ደቂቃ የማሸነፋቸው ምስጥር

“ሚስጥሩ ትልቁ ነገር ተከላካዮቻችን ስህተት የማይሰሩ ከሆነ ሁሌ የምላቸው ፊት ላይ ያሉ አጥቂዎቻችን ፈጣን ስለሆኑ በየትኛውም ሰዓት ላይ ጎል እንደሚያስቆጥሩ እነግራቸው ነበር። ያንን ነው ዛሬም ያየነው። ሚስጥሩ ፊት ላይ ያሉን ተጫዋቾች ፈጣን መሆናቸው እና መጠቀም የሚችሉ መሆናቸው ነው።”