ሪፖርት | አዲስ አበባ ከተማ ሰበታ ላይ ግቦችን አዝንቧል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በዕለቱ ሁለተኛ በነበረው እና በወራጅ ቀጠናው ትልቅ ትርጉም በነበረው ጨዋታ ምህረት የለሽ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ሰበታ ከተማ ላይ የግብ ናዳ አውርደዋል።

ሰበታ ከተማዎች በሀዲያ ሆሳዕና ከተረታው ስብስብ ስድስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ሰለሞን ደምሴ ፣ ዓለማየሁ ሙለታ ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ ዘላለም ኢሳይያስ፣ ዘካርያስ ፍቅሬ እና ፍፁም ገብረማርያምን አስወጥተው በምትካቸው ለዓለም ብርሃኑ ፣ ጌቱ ኃይለማርያም ፣ ታፈሰ ሰርካ ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ፣ መሀመድ አበራ እና አዲስ ፈራሚውን ዴሪክ ንሲባምቢን ተክተው ያስገቡ ሲሆን በአንፃሩ አዲስአበባ ከተማዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና ከተረታው ስብስብ ሳሙኤል ተስፋዬ ፣ ኤልያስ አህመድ ፣ ቢኒያም ጌታቸው እና የሺዋስ በለውን አስወጥተው በምትካቸው ሮቤል ግርማ ፣ ዋለልኝ ገብሬ ፣ እንዳለ ከበደ እና ሪችሞንድ አዶንጎን በመተካት ጨዋታውን አድርገዋል።

በእንቅስቃሴ ረገድ ቀዝቃዛ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማዎች ከግብ ፊት ምህረት አልባ የነበሩ ሲሆን በተቃራኒው ሰበታ ከተማዎች ደግሞ ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጭ ፍፁም ሀሳብ አጥሯቸው የተመለከትንበት ጨዋታ ነበር።

ከወትሮው በተለየ ኳስ የመቆጠር እምብዛም ፍላጎት ያልነበራቸው አዲስ አበባዎች በ13ኛው ደቂቃ ሳይጠበቁ መሪ መሆን ችለዋል። በተጋጣሚ ሜዳ ከነጠቁት ኳስ መነሻ ካደረገው የማጥቃት ሂደት እንዳለ ከበደ ከቀኝ መስመር ወደ ወደ ሳጥን ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን የመጀመሪያውን ኳስ ሲያሸንፍ ሪችሞንድ አዶንጎ ደግሞ ሁለተኛዋን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ የላካት ኳስ በለዓለም ብርሃኑ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታግዛ የመጀመሪያዋ ግብ ለመቆጠር በቅታለች።

ሰበታ ከተማዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በነበራቸው አጋማሽ ኳስ ከመያዝ ባለፈ ይህ ነው የሚባል አደጋ ለመፍጠር ሲቸገሩ አዲስ አበባ ከተማዎች ግን ተጨማሪ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።

በ23ኛው አማካዮ ቻርልስ ሪባኑ ከራሱ የሜዳ አጋማሽ በግሩም ሁኔታ የላካትን ኳስ ፍፁም ጥላሁን በአስደናቂ መልኩ ተቆጣጥሮ በመጨረስ የቡድኑን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ሲችል በ36ኛው ደቂቃ ደግሞ በተመሳሳይ አዲስ አበባዎች በሰበታ ከተማ አጋማሽ ከተነጠቁት ኳስ መነሻነት ዋለልኝ ገብሬ ያደረሰውን ጊዜውን የጠበቀ ኳስ ፍፁም ጥላሁን ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ የነበረችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በአጋማሹ ሰበታ ከተማዎች ሳሙኤል ሳሊሶ ካሻገረው የማዕዘን ምት በኃይሉ ግርማ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ ከወጣበት አጋጣሚ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት አዎንታዊ ቅያሬዎችን አድርገው የጀመሩት ሰበታ ከተማዎች እንደመጀመሪያው ሁሉ ኳሱን መቆጣጠር ቢችሉም አዲስ አበባዎች ግን በመልሶ ማጥቃት በአጋማሹ አስፈሪ ነበሩ።

በ60ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን የመጀመሪያ ኳስ ማሸነፉን ተከትሎ ሙሉቀን አዲሱ ያገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ሳጥን ውስጥ በመዞር የቡድኑን አራተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በ67ኛው ደቂቃ ሳሙኤል አስፈሪ ዘካርያስ ፍቅሬ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በረከት ሳሙኤል አስቆጥሮ ለሰበታዎች ተስፋ ቢፈነጥቅም ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ሮቤል ግርማ ግሩም የሆነች የቅጣት ምት ኳስ በማስቆጠር የሰበታ ከተማዎች ተስፋ ዳግም አጨልሟል።

5-1 በሆነ ውጤት ጨዋታውን መደምደም የቻሉት አዲስ አበባ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 14 በማሳደግ ደረጃቸውን ወደ 12ኛ ማሳደግ ሲችሉ ሰበታዎች ደግሞ በ7 ነጥቦች በስተመጨረሻም የሊጉን ግርጌ ከጅማ አባ ጅፋር ተረክበዋል።