ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በውድድር ዓመቱ 100ኛ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በመሀከላቸው የሁለት ነጥብ ልዩነት ብቻ ያላቸው ከመጨረሻ ድሉ ጥሩ መነሳሳት ላይ የሚገኘው ባህር ዳር እና በደጋፊዎቹ ፊት የሚጫወተው ድሬዳዋ ነገ ጥሩ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት ድሬዳዋ ከተማዎች ከዚያ ቀደም ባስመዘገቡት ተከታታይ ድል ወቅት የነበራቸውን ብቃት መልሰው በማግኘት የሰንጠረዡን አጋማሽ ለመሻገር ይጫወታሉ። ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በጥሩ ብልጫ ከሀዋሳ ከተማ ሦስት ነጥብ መውሰድ የቻሉት ባህር ዳሮች ደግሞ የላይኛው ፉክክር እንዳይሸሻቸው የነገውን ጨዋታ ውጤት ይፈልጋሉ።

አሰልጣኝ ፉዓድ የሱፍ ቡድናቸው ኳስ ይዞ በትዕግስት እንዲጫወት ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም ከአርባምንጭ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ይህ ውጥናቸው ሜዳ ላይ መታየት የጀመረው በሁለተኛው አጋማሽ ነበር። በእነዚያ 45 ደቂቃዎች የተሻለ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር የነበረውን የቡድኑን የኳስ ምስረታ ሂደት ማስቀጠል ደግሞ የነገ የቤት ስራቸው ይሆናል። ሆኖም በዚሁ ጨዋታ ነጥብ የተጋሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በነገው ጨዋታም የአርባምንጭ ዓይነት ፈተና እንዳይገማቸው ያሰጋል። በተለይም ባህር ዳር ከተማ ሀዋሳን ሲረታ ጨዋታውን የጀመረበት መንገድ በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ ከፍ ያለ ጫናን ማሳደርን የቀላቀለ መሆኑ ድሬዎች ሊያስቡበት የሚገባ ይመስላል።

ቡድኑ አሁንም የአስር ቁጥር ሚናውን ለማን መስጠት እንዳለበት እንዳልወሰነ በሚያሳይ መልኩ በአርባምንጩ ጨዋታም አቤል እና ሱራፌልን ሲጠቀም መስተዋሉ ደግሞ ሁኔታው የነገ የማጥቃት ብቃቱን ሊወስን እንደሚችል ይጠቁማል። በዚህም ነገ በራሱ ሜዳ ላይ ከኳስ ጋር ሳለ ጥድፊያ ውስጥ ሳይገባ የተጋጣሚን ጫና አልፎ ቅብብሎችን በመከወን ከሜዳ የሚወጣ ድሬዳዋ መታየት ይኖርበታል። ይህ እንዲሆንም የማጥቃት ባህሪያቸው ከሚጎላው የግራ እና ቀኝ አማካዮች ውጪ ብበማጥቃት ወቅት ከተከላካይ ፊት ካሉት ሁለት አማካዮች አንዱ ከነገው ተመራጭ አስር ቁጥር ጋር ጥሩ ጥምረትን እንዲመሰርት ይጠበቃል።

ባህር ዳር ከተማ በሀዋሳው ድል ካሳያቸው ለውጦች ዋነኛው የተነሳሽነት ከፍታው ነበር። ቡድኑ ያኔ ወደ ውጤት ለመመለስ የተላበሰውን የቡድን መንፈስ በድሉ አጎልብቶ ለነገው ጨዋታ መድረስ አስፈልጊው ይሆናል። የዚህ ውጤት የሆነው ከኳስ ውጪ ተጋጣሚን የመቀባበያ ክፍተቶች የማሳጣት ብቃቱ ጥሩ ሆኖ መታየቱም ለድሬዳዋ በቂ ዕድገት ያላሳየ የኳስ ቁጥጥር ብቃት ፈተና ሊሆን መቻሉ አይቀርም። በመሆኑም ጥሩ ፍጥነት የተላበሱት የቡድኑ የወገብ ነላይ ተሰላፊዎች በድሬ የኳስ ምስረታ ወቅት ከካስ ውጪ የሚኖራቸው ብቃት ጨዋታው ላይ ልዩነት እንደሚፈጥር መናገር ይቻላል።

ለባህር ዳር ጥሩ ትዝታ በሆነው የሀዋሳው ጨዋታ ከሁሉም በላይ ዋና ነጥብ የነበረው ግን የአብዱልከሪም ኒማ የሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ሚና ትኩረትን ይስባል። ከኦሴይ ማዉሊ ጉዳት በኋላ አስፈሪ የወገብ በላይ ቅርፅን የተገበሩት ባህር ዳሮች በማጥቃት ወቅት የተጋጣሚን ተከላካዮች ግምት ሲያዛንፍ በነበረው የኒኪማ እንቅስቃሴ በጣሙን ተጠቃሚ ሆነው ነበር። ውሳኔው ባህር ዳር በማጥቃት ወቅት በፍፁም ዓለሙ ላይ ብቻ ተመስርቶ ይታይ የነበረበትን ድክመትም ያቃለለ ጥሩ ታክቲካዊ መላ ሆኖ ታይቷል። በነገው ጨዋታ ግን ይህ አቀራረብ በተጋጣሚው ተገማች መሆኑ ስለማይቀር በግብ ፊት ያለውን የአፈፃፀም ደረጃ ማሳደግ ከአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ቡድን ይጠበቃል።

የድሬዳዋ ከተማዎቹ ጋዲሳ መብራቴ እና እንየው ካሳሁን አሁንም በጉዳት ለነገው ጨዋታው አይደርሱም። ባለፈው ጨዋታ ተመልሶ የነበረው ብሩክ ቃልቦሬም ለነገው ጨዋታ ብቁ አለመሆኑን ሰምተናል። በሌላ በኩል በገጠመው የግል ችግር የተነሳ ከቡድኑ ጋር ያልነበረው ጋናዊው ተከላካይ አውዱ ናፊውም ገና ነገ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለስ በመሆኑ ጨዋታው ያልፈዋል። ባህር ዳር ከተማዎች ኦሴይ ማዉሊ ከጉዳት ያልተመለሰላቸው ሲሆን አህመድ ረሺድ እና ዜናው ፈረደ ደግሞ ሌሎች ጉዳት ያገኛቸው ተጨዋቾች ሆነዋል። ለቡድኑ ጥሩ ዜና የሚሆነው የግርማ ዲሳሳ ቅጣቱን ጨርሶ ወደ ሜዳ የሚመለስ መሆኑ ነው።

በላይ ታደሰ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የሚመሩ ሲሆን ክንዴ ሙሴ እና ወጋየው አየለ ረዳቶች ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበዋል

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– የነገ ተጋጣሚዎቹ እስካሁን አራት የሊግ ጨዋታዎችን አድርገዋል። ባህር ዳር ከተማ ሁለቴ ድሬዳዋ ደግሞ አንዴ ድል ሲቀናቸው የመጨረሻ ጨዋታቸው በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። በግንኙነቶቹ ባህር ዳር አምስት ድሬዳዋ ደግሞ አራት ግቦች አሏቸው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

ዐወት ገብረሚካኤል – አቤል አሰበ – መሳይ ጳውሎስ – ሄኖክ ኢሳይያስ

ዳንኤል ደምሴ – ዳንኤል ኃይሉ

አብዱርሀማን ሙባረክ – ሱራፌል ጌታቸው – አብዱለጢፍ መሀመድ

ማማዱ ሲዲቤ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ፋሲል ገብረሚካኤል

ሳለአምላክ ተገኘ – ፈቱዲን ጀማል – ሰለሞን ወዴሳ – ግርማ ዲሳሳ

አለልኝ አዘነ – በረከት ጥጋቡ

ዓሊ ሱለይማን – ፍፁም ዓለሙ – ፉዓድ ፈረጃ

አብዱልከሪም ኒኪማ

ያጋሩ