​ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ገ ምሽት በኢትዮጵያ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ መካከል የሚደረገው ጨዋታ እንደሚከተለው ተዳሷል።

ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ሦስት ነጥብ ያገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ዳግም አሸናፊ በመሆን በደረጃ ሰንጠረዡ መሻሻል ለማግኘት ወደሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል።

ዓምና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ በወጥነት ወጥ ያልሆነ ብቃት ማሳየቱን ቀጥሏል። ከአራት ጨዋታዎች በፊት አራት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ ወደ ብቃቱ የተመለሰ የመሰለው ቡድኑ ካለፉት አራት ጨዋታዎች ግን አንዱን ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለው። የ2013 ከፍተኛ ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው ስብስቡም በተጠቀሱት አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩ ምነኛ ጠንካራ ጎኑም እንደከዳው ያመላክታል። ይህ ቢሆንም ግን የሊጉ የአንድ የውድድር ዓመት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች የሆነው አቡበከር ናስር ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሜዳ መመለሱ ትልቅ መሻሻል እንደሚሰጠው ይጠበቃል። ተጫዋቹ ከኳስ ጋር ስል መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከኳስ ውጪም የተጋጣሚን ተከላካዮች ትኩረት በመሳብ ለሌሎች አጋሮቹ የሚፈጥራቸው ቦታዎች ጥቅማቸው ከፍተኛ ነው። ነገም ከኳስ ውጪ አብዛኛውን ደቂቃ እንደሚያሳልፉ የሚገመቱት የአርባምንጭ ተከላካዮችን ለማስከፈትም የእርሱ መኖር አስፈላጊ ነው። ከዚህ ውጪ በቁጥር በርከት ብለው በታችኛው ሜዳ እንደሚያሳልፉ የሚገመቱትን የተጋጣሚ ተከላካዮች ለመዘርዘር የመስመር ላይ ሩጫዎች ሊበረክቱ ይገባል።

ለኳስ ቁጥጥር ከፍተኛ ፍላጎት ያለው የአሠልጣኝ ካሣዬ ስብስብ በኳስ ምስረታ ወቅት የሚኖሩትን መደነቃቀፎች ነገ ሊያስወግድ የግድ ይለዋል። በተለይ አርባምንጭ አሁን አሁን እየተቀዛቀዘ መጣ እንጂ ተጋጣሚን ተጭኖ በአደገኛ ቦታ ኳስ በመቀበል አደጋን መፍጠር የሚችል ቡድን ስለሆነ ቡድኑ ይህንን ብቃቱን ነገ መልሶ ካገኘ ቡና ሊቸገር ስለሚችል ከኋላ በከፍተኛ ትኩረት መጫወት ይጠበቅበታል። ከዚህ ውጪ ከተከላካይ ጀርባ የሚላኩ ኳሶችንም ማምከኛ ዘዴ መዘየድ ያስፈልገዋል።

በ12 ጨዋታዎች ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ያሸነፈው አርባምንጭ ከተማ ከገባበት የውጤት ቀውስ ለመውጣት እና ከጠፋበት ሦስት ነጥብ ጋር ለመገናኘት ጠንክሮ እንደሚጫወት ይታመናል።

ያለፉትን ስምንት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉት አዞዎቹ በዋናነት ጎል ፊት ዐይናፋር ይመስላሉ። በእንቅስቃሴ ደረጃ መጥፎ ብቃት በየጨዋታዎቹ የማያሳየው እና በመከላከሉም ረገድ የሊጉ ሦስተኛው ጠጣር የኋላ መስመር ባለቤት የሆነው ቡድኑ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ግብ ማስቆጠር እንዳለበት የገባው አይመስልም። ካስቆጠሯቸውም ጎሎች የፍፁም ቅጣት ምቶች እና የቅጣት ምቶች መኖራቸው ሲታወስ በእንቅስቃሴ ኳስ እና መረብን ማገናኛ መፍትሔ በአግባቡ እንዳላገኙ ያመላክታል። ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች በድምሩ ስምንት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ ማድረጋቸው እና አንድ ጎል ብቻ ማስቆጠራቸው እንዳለ ቢሆንም የአጨዋወት ዘይቤያቸው ከፍ ብሎ የሚከላከል ቡድን ሲያገኝ ስለሚመቸው ነገ ከተከላካይ ጀርባ ቶሎ ቶሎ እየገቡ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ይገመታል። በተለይ ፈጣኖቹ የመስመር ተጫዋቾች በዚህ ሂደት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሊደረግ ይችላል። ከዚህ ውጪም ኤሪክ ካፓይቶን ያነጣጠሩ ረጃጅም ኳሶችም እንደ ጎል ምንጭነት ሊያገለግሉ ይችላሉ።

አርባምንጭ በተጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ደካማ ቢሆንም በራሱ ሳጥን ግን ጠጣር ነው። ቡድኑም በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ አስተናግዶ አያውቅም። ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ በመቀጠልም የሊጉ ሦስተኛው ትንሽ ግብ ያስተናገደ ክለብ ነው። ይህ ደግሞ ምን ያህል የኋላ መስመሩ አስተማማኝ እንደሆነ ይነግረናል። ከዚህ መነሻነት ኢትዮጵያ ቡና መረቡን ለማግኘት እንደሚቸገር ቀድሞ መናገር ይቻላል። ግን ደግሞ በዚህ ጠንካራ መስመር ዋነኛ አበርክቶ የነበረው በርናን ኦቺንግ በቅጣት ምክንያት አለመኖሩ መጠነኛ መሳሳት ሊያመጣባቸው ይችላል።

ኢትዮጵያ ቡና በጨዋታው በጉዳት እና በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች አለመኖሩ ተመላክቷል። በአዲስ አበባው ጨዋታ በ65ኛው ደቂቃ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ የወጣው ወንድሜነህ ደረጄም ከጉዳቱ አገግሞ ተከታታይ ቀናት ልምምድ እንደሰራ አውቀናል። በአርባምንጭ በኩል ሀቢብ ከማል ከቅጣት መልስ ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆን ከላይ እንደገለፅነው በርናድ ኦቺንግ ግን በቅጣት በጨዋታው አይኖርም።

9 ሰዓት ሲል የሚጀምረውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ከረዳቶቿ ዳንኤል ጥበቡ እና አበራ አብርደው እንዲሁም ከአራተኛ ዳኛው አዳነ ወርቁ ጋር በመሆን ትመራዋለች።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡናማዎቹ እና አዞዎቹ 14 ጊዜ ተገናኝተው እኩል 5 ጊዜ ተሸናንፈው አራቱን አቻ ተለያይተዋል። ቡና 15 ፣ አርባምንጭ 14 ጎሎችንም አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረተንሳይ – አበበ ጥላሁን – ወንድሜነህ ደረጄ – ሥዩም ተስፋዬ

ታፈሠ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊልያም ሰለሞን

አቤል እንዳለ – አቡበከር ናስር- አስራት ቱንጆ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ሙና በቀለ – ደረጄ ፍሬው – አሸናፊ ፊዳ – ተካልኝ ደጀኔ

ፀጋዬ አበራ – እንዳልካቸው መስፍን – አቡበከር ሸሚል – አሸናፊ ኤሊያስ

ሀቢብ ከማል – ኤሪክ ካፓይቶ