የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከቀናት በፊት ሲጠናቀቁ ሊነሱ ይገባቸዋል ያልናቸውን ትኩረት የሳቡ ዐበይት ጉዳዮች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።
👉 ሀድያ ሆሳዕና እና ትኩረት የሚስበው ቀዳሚ አሰላለፍ
ባለፉት ዓመታት በግዢ ከሚታወቁ ክለቦች ውስጥ የነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ዘንድሮ በተሻለ መልኩ የታዳጊ ቡድን ተጫዋቾቻቸው መጠቀም ጀምረዋል። ሀድያዎች ምንም እንኳ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ማሳካት እና ግቦች ማስቆጠር ቢሳናቸውም ሲዳማ ቡናን በገጠሙበት ጨዋታ ላይ ግን ስድስት ከታዳጊ ቡድን ያሳደጓቸውን ቃልአብ ውብሸት ፣ መለሰ ሚሻሞ ፣ ካሌብ በየነ ፣ ብሩክ ማርቆስ ፣ ደስታ ዋሚሾ እና ተመስገን ብርሀኑን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተጠቅመዋል።
ከዚህ ቀደም አዳማ ከተማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡናን የመሳሰሉ ክለቦች መሰል ተግባራት ቢከተሉትም ሀድያ ሆሳዕና ግን ሚልዮኖች ፈሰስ በማድረግ በርካታ ዝውውሮች በመፈፀም ነበር የሚታወቀው። አሁን ግን የቀደመ መንገዱ በመተው የታዳጊ ቡድኑ ውጤቶች መጠቀም ጀምሯል። ሌላው ትኩረት እንዲስብ የሚያደርገው ግን ቡድኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታዳጊዎቹን መጠቀም መጀመሩ እና በቁጥር መብዛታቸው ነው። በ2011 የታዳጊ ቡድን አቋቁሞ የቡድኑ ፍሬ የሆኑ ተጫዋቾችን መጠቀም ከጀመረ ወዲህ በውስን መልኩ ፋይናንሱ ተረጋግቷል። ክለቡ ባለፉት ዓመታት ከደመወዝ አለመክፈል ጋር ስሙ ሲያያዝ ቢቆይም ዘንድሮ እስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ ግን መሰል ችግሮች ቀርፏል። ይህም የታዳጊ ቡድኑን መጠቀም መጀመሩን ተከትሎ የመጣ ትልቅ እና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው። ይህም ጠንካራ የታዳጊ ቡድን እያላቸው ተጫዋቾቹን መጠቀም ላልደፈሩ ክለቦች ትምህርት ይሰጣል።
👉 ግብ ያስቆጠሩ ተከላካዮች መብዛት እና የምኞት ደበበ ጉዳይ
የስድስተኛው ሳምንት የጨዋታ መርሀ ግብር በርካታ ተከላካዮች ግብ ያስቆጠሩበት ነበር። ፍራኦል መንግሥቱ ፣ አማኑኤል ተርፉ ፣ ሐቢብ መሐመድ እና ፈቱዲን ጀማል እንዲሁም በተከላካይነት ሚና የሚታወቀው ሱሌይማን ሀሚድ ኳስና መረብ ያገናኙ ተጫዋቾች ሆነዋል። የተከላካዮች ዋነኛው ስራ እንደ ስማቸው መከላከል ነው። ግባቸውን ከመጠበቅ አልፈው ግብ ባያስቆጥሩ ብዙም የሚገርም ነገር ላይኖረው ይችላል። የምኞት ደበበ ግን ይለያል ፤ ተጫዋቹ የመጨረሻ ግቡን ያስቆጠረው ከሦስት ዓመታት በፊት በሀዋሳ ከተማ ማልያ ነበር። ከመጨረሻው ግቡ በኋላም የእግርኳስ ህይወቱ ሌላ መልክ ይዟል። ከፈረሰኞቹ ጋር ሁለት የፕሪምየር ዋንጫ ስያነሳ የመጀመርያው የብሔራዊ ቡድን ጥሪ የደረሰውም ከመጨረሻው ግን በኋላ ነበር። በርካታ ተከላካዮች ግብ ባስቆጠሩበት ሳምንትም ከሦስት ዓመታት በኋላ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
👉 የቀይ ካርዶች ሳምንት
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስድስት ሣምንት ቆይታ የተለያዩ ስድስት ተጫዋቾች በቀይ ካርድ የወጡ ሲሆን ከተመዘዙ ስድስት ቀይ ካርዶች አራት የሚሆኑት ግን ባሳለፍነው የስድስተኛ ሣምንት መርሐግብሮች ላይ ብቻ የተሰጡ ናቸው። ከቀይ ካርዱ መብዛት በዘለለ ሌላ ትኩረት የሚስባው ጉዳይ ግን ካርዶቹን ተከትለው የተከሰቱ አምቧጓሮዎችና እሰጣ አገባዎች ናቸው። ውሳኔዎቹን መቀየሪያ አጋጣሚ በማይኖርበት ሁኔታ ተጫዋቾቹ ውሳኔውን ለመቀበል ያሳዩት አዝማሚያ ደካማ ሆኖ ተመልክተነዋል። ይህንን ተከትሎም ከሜዳ ለመውጣት እጅግ በመዘግየት እና የጨዋታ ደቂቃዎችን በማባከን ለተመልካችም አሰልቺ የሆነ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ ተስተውሏል። የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ከዳኞች የውሳኔ ትክክለኛነት ጋር የተጋረጡ ፈተናዎችን በማስተካከል ዙሪያ በርካታ ሥራዎች የሚጠብቁት ቢሆንም ዛሬ ላይ ልናነሳ የወደድነው የተጫዋቾቹ ስሜታቸውን መቆጣጠር ላይ የሚታይባቸው ድክመት ክለቦች በሥነልቦና ባለሙያም ጭምር የክህሎት ሥልጠናቸውን አጠናክረው እንዲሰጡ ለማመላከት ነው።
👉 ሱሌማን ሀሚድ በአዲስ ሚና
በሀገራችን እግር ኳስ የተጫዋቾች ሚና እየቀያየሩ መጠቀም የተለመደ ነው፤ በውጤታማነት ረገድ ሲታይ ግን እንደሚፈለገው አጥጋቢ አደለም። በርግጥ ከዚህ ቀደም እንደ ሙጂብ ቃሲም የመሳሰሉ ጥቂት ተጫዋቾች ቢኖሩም አብዛኞቹ የቦታ ለውጦች ግን ውጤታማ አይደሉም ወይም ቀጣይነት የላቸውም። በስድስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በፀሎት ከዚህ ቀደም በመስመር ተከላካይነት የምናውቀው ሱሌይማን ሀሚድ በመስመር አጥቂነት ተጠቅሞ ውጤታማ ሆኗል። ከዚህ ቀደም በታዳጊ ቡድን ቆይታው በአጥቂነት እንደተጫወተ የሚነገርለት ተጫዋቹ ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታም በመስመር አጥቂነት እንደሚጫወት ያወቀው በመጨረሻው የቡድን ውይይት እንደሆነ ገልጿል። ተጫዋቹ በአዲሱ ቦታው እና በውጤታማ አጀማመሩ የሚቀጥል ከሆነም ከዚህ ቀደም ሙጂብ ቃሲም በፋሲል ከነማ ማልያ የሰራውን ውጤታማ ሥራ የመድገም ዕድል ይኖረዋል።