የሰባተኛ ሳምንት መርሀ-ግብር ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል ፤ ጨዋታዎቹን አስመልክተን ያዘጋጀንላችሁን መረጃዎች እንደሚከተለው እናቀርባለን።
ወልቂጤ ከተማ ከ ሀምበርቾ
በሦስት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ሰባተኛውን ሳምንት ይከፍታል።
በአምስተኛ ሳምንት ሻሸመኔ ከተማን አሸንፈው ነጥባቸውን ወደ አምስት ከፍ በማድረግ ከወራጅ ቀጠናው የወጡት ወልቂጤ ከተማዎች የአሸናፊነት መንገዳቸውን ለመቀጠልና ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ሀምበርቾን ይገጥማሉ።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ባህር ዳር ከተማ ተከታታይ ሽንፈቶች ካስተናገዱ በኋላ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያው ድላቸው ያስመዘገቡት ወልቂጤዎች ከጣፋጩ ድል በዘለለ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን አስተናግዶ መጥፎ ክብረወሰን አስመዝግቦ የነበረው የተከላካይ ክፍላቸው በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ግብ ሳያስተናግድ ወጥቷል። ይህም በቡድኑ ውስጥ ከታዩ በጎ ጎኖች ይጠቀሳል። ሌላው የወልቂጤ ከተማ ትልቁ ክፍተት የነበረው የማጥቃት ክፍሉም ከጨዋታዎች በኋላ ወደ ግብ ማስቆጠሩ ተመልሷል። ሰራተኞቹ ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ለሦስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ አላገናኙም ነበር። በመጨረሻው ጨዋታ ግን በጋዲሳ መብራቴ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ከጎል ጋር ታርቀዋል።
አሰልጣኝ ሙልጌታ ምህረት የድል መንገዱን ለማስቀጠል በዋነኝነት ይህንን የግብ ማስቆጠርና የግብ ዕድሎች የመፍጠር ችግር መቅረፍ ይጠበቅበታል። ቡድኑ ምንም እንኳ ሻሸመኔን ባሸነፈበት ጨዋታ ግብ ብያስቆጥርም የግብ ዕድሎች በጥራትና በብዛት የመፍጠር ችግር ታይቶበታል፤ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ በጉልህ የሚጠቀስ ዕድል መፍጠር አልቻለም።
የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ማስመዝገብ ያልቻሉት ሀምበሪቾዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ወልቂጤን ይገጥማሉ። ፋሲል ከነማን በገጠሙበት መጨረሻው የሊግ ጨዋታ ላይ ለሰማንያ አምስት ደቂቃዎች በጎደሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት ሀምበሪቾዎች በጨዋታው በአመዛኙ መከላከል ላይ ያተኮረ አጨዋወት ቢከተሉም የተጋጣምያቸውን ጥቃት ለመመከት የሚያስችል በቂ አቅም አልነበራቸውም። ከዚ በፊት ምንም እንኳ የውጤት በለስ ባይቀናቸውም በተሻለ መንገድ ኳስን ይዘው በሽግግሮች ለማጥቃት ጥረት ስያደርጉ የምናውቃቸው አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ በነገው ጨዋታ ቀይ ካርዱን ተከትሎ የመረጡትን መከላከል ላይ ያመዘነ አጨዋወት ይተገብሩታል ተብሎ አይጠበቅም። በነገው ዕለትም መስመሮች ላይ ትኩረት ያደረገ የማጥቃት ሽግግር ይከተላሉ ተብሎ ይገመታል። ሀምበሪቾዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች አስተናግደዋል፤ በነገው ዕለት ግን ከተጋጣምያቸው የማጥቃት ጥንካሬ አንፃር ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም በመጨረሻው ጨዋታ ተሻሽሎ የቀረበው የወልቂጤ ተከላካይ መስመር ለመፈተን ግን በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ያልቻለውን የማጥቃት ክፍላቸውን ጥራት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ወልቂጤዎች በቅጣት ላይ ያለው የተስፋዬ መላኩን ግልጋሎት አያገኙም ሀምበርቾዎችም በተመሳሳይ በመጨረሻው ጨዋታ ላይ የቀይ ካርድ የተመለከተው ቴዎድሮስ በቀለ በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም።
ይህንን ጨዋታ ተከተል ተሾመ በመሐል ዳኝነት ይመራዋል በረዳትነት ደግሞ አብዱ አሊ እና ደረጄ አመራ ሲመደቡ ሙሉቀን ያረጋል ደግሞ የጨዋታው አራተኛ ዳኛ ይሆናል።
ፋሲል ከነማ ከ ወላይታ ድቻ
ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የአፄዎቹ እና የጦና ንቦቹ ፍልሚያ ምሽት ላይ ይከናወናል።
ከወሳኙ የደርቢ ጨዋታ በኋላ ሀምበሪቾን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ዐፄዎቹ በአስራ ሁለት ነጥቦች በ4ኛ ደረጃነት ተቀምጠዋል። ወደ ሊጉ አናት ይበልጥ ለመጠጋትም የጦና ንቦችን ይገጥማሉ። ዐፄዎቹ ከጨዋታ ጨዋታ ትልቅ መሻሻሎች እያሳዩ ይገኛሉ፤ ቡድኑ ከውጤት ባሻገር አጨዋወቱ ላይ የሚታይ ለውጥ አምጥቷል። በተለይም ደግሞ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያላስተናገደው ጠንካራው የተከላካይ መስመር የቡድኑ ዋነኛው ጠንካራ ጎን ነው፤ የተከላካይ መስመሩ በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ብያስተናግድም ከዛ በኋላ በተደረጉ ጨዋታዎች ግን ግቡን አላስደፈረም። በነገው ጨዋታም ከፈጣኖቹ የወላይታ ድቻ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ቀላል የማይባል ፈተና ይጠብቃቸዋል። ሌላው በዐፄዎቹ በኩል ሊነሳ የሚገባው በጎ ጎን በጊዜ ሂደት የጎለበተው የፈጠራ አቅማቸው ነው። ምንም እንኳ እንደሚፈጥሯቸው በርካታ ዕድሎች በዛ ያሉ ግቦች ባያስቆጥሩም የቡድኑ የአማካይ ክፍል ጨዋታ ከመቆጣጠር አልፎ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል። በነገው ዕለትም በተመሳሳይ ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቅድምያ የሚሰጥ የአማካይ ጥምረት ያለው ቡድን እንደመግጠማቸው ጥሩ የመሀል ሜዳ ፉክክር ያለበት ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። የቡድኑ ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆን አምሳሉ ጥላሁን ግን ልምምድ ቢጀምርም በዚህ ጨዋታ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።
ኢትዮጵያ መድንን አንድ ለባዶ ካሸነፉ በኋላ ከድል ጋር የተራራቁት ወላይታ ድቻዎች በስምንት ነጥቦች በ8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባሉ። የጦና ንቦቹ ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው በውጤት ማጀብ አልቻሉም። ቡድኑ ምንም እንኳ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ቢገኝም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ምንም ድል አላስመዘገበም። ቡድኑ ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ ማሳካት የቻለው ሁለቱን ብቻ ነው። በነገው ጨዋታም ከተከታታይ ሁለት የአቻ ውጤቶች ለመላቀቅ ምንም ሽንፈት ያልቀመሰውን ፋሲል ከነማ ይገጥማል። የጦና ንቦቹ በፊት መስመር ላይ ያላቸው የአፈፃፀም ችግር ዋነኛው የቡድኑ ድክመት ተደርጎ ይወሰዳል። የአማካይ ክፍሉ ምንም እንኳ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ ተፅዕኖው በመጠኑ ቢቀንስም የግብ ዕድሎች ከመፍጠር ረገድ ግን አልቦዘነም፤ ድሬዳዋ ከተማን በገጠሙበት ጨዋታ ላይ ያባከኗቸው ዕድሎች፤ እንዲሁም በውድድር ዓመቱ ከአንድ ጨዋታ ውጭ በተቀሩት ከአንድ ግብ በላይ አለማስቆጠራቸውም የቡድኑ የአፈፃፀም ችግር ማሳያዎች ናቸው። በነገው ጨዋታም በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደ የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን ስለሚገጥሙ ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 12 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ፋሲል ከነማዎች ሰባት ጊዜ ድል አድርገው 16 ግቦች ሲያስቆጥሩ 12 ግቦች ያሏቸው ወላይታ ድቻዎች አራት ጊዜ አሸንፈዋል ፤ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በዋና ዳኝነት፤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ኤፍሬም ሀይለማርያም ረዳቶች ባሀሩ ተካ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን ለጨዋታው ተመድበዋል።