[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ኢትዮጵያ ቡና እና አርባምንጭ ከተማን ያገናኘው ፍልሚያ በታታሪዎቹ አርባምንጭ ከተማ አሸናፊነት ተደምድሟል።
አዲስ አበባ ከተማን በዊሊያም ሰለሞን ብቸኛ ጎል አሸንፈው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሦስት ነጥብ ካገኙበት ጨዋታ ሦስት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ወንድሜነህ ደረጄ በቴዎድሮስ በቀለ፣ ሮቤል ተክለሚካኤል በአቤል እንዳለ እንዲሁም አቡበከር ናስር በእንዳለ ደባልቄ ተተክተዋል። ባሳለፍነው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው የነበረው አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ በቅጣት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ የሆነው በርናንድ ኦቺንግ እና ራምኬል ሎክን በኡቸና ማርቲን እና ሀቢብ ከማል ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ጨዋታው ገና አንድ ደቂቃ ሳይሞላው አርባምንጭ ከተማ እጅግ ለግብ የቀረበበት አጋጣሚ ፈጥሯል። በዚህም ፀጋዬ ወደ ቀኝ ካደላ የመሐል ክፍል ወደ ግብ የላከውን ረጅም ኳስ በላይ አግኝቶት በጥሩ ሁኔታ ለካፓይቶ ቢሰጠውም ኬኒያዊው አጥቂ ዕድሉን በአስቆጪ ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በከፍተኛ ፍላጎት እና ሀይል ጨዋታውን የጀመሩት አርባምንጮች በ6ኛው ደቂቃ ፀጋዬ በሞከረው ኳስ ሌላ አስደንጋጭ ጥቃት ሰንዝረዋል። ከጅምሩ ጫና የበዛባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስ ከኋላ መስርተው ለመውጣት ቢያስቡም የአዞዎቹን የሰው ለሰው አያያዝ (Man to man marking) አምልጦ መውጫ መፍትሔ ጠፍቷቸው ታይቷል። በዚህ ሂደትም በ13ኛው ደቂቃ የመሐል ተከላካዩ ቴዎድሮስ የተሳሳተውን ኳስ በላይ ተረክቦ ከሳጥን ውጪ እንዲሁም ከደቂቃ በኋላ የግብ ዘቡ አቤል በትክክል ለአጋሩ ያላቀበለውን ኳስ ሀቢብ ሞክሮ ሊያስቆጥርባቸው ነበር።
ከኳስ ውጪ በከፍተኛ አደረጃጀት ጨዋታውን የቀጠሉት የአሠልጣኝ መሳይ ተጫዋቾች የተጋጣሚን የኳስ ቅብብል በአደገኛ ቦታ በመቀበል አደገኛ ሙከራ በማድረግ በ17ኛው ደቂቃ ሌላ ወደ ግብ የቀረቡበትን አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። በተመሳሳይ አቤል በእግሩ ኳስ አቀብላለው ሲል የተሳሳተውን ኳስ ሙና ደርሶት በቀጥታ መረብ ላይ ለማሳረፍ ጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ቡናማዎቹ በተደጋጋሚ ከራሳቸው ሜዳ ለመውጣት ሲቸገሩ ተስተውሏል። በመጀመሪያው አጋማሽም ሦስተኛው የሜዳ ሲሶ ላይ ተገኝተው የግብ ዕድል መፍጠር ተስኗቸዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ቀሪ የመጨረሻ ደቂቃዎች ደግሞ አርባምንጭ ተጭኖ መጫወቱን ጋብ ሲያደርግ በአንፃሩ ቡና በላይኛው ሜዳ ኳስ ለመቀባበል ሲጥር ነበር። ከአጥቂ ጀርባ የተሰለፈው የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ ዊሊያም በ36ኛው ደቂቃ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዶ በ41ኛው ደቂቃ በሚኪያስ ተቀይሮ ወጥቷል። ተጫዋቹም ተቀይሮ ሲወጣ ለተሻለ ህክምና በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል። ሁለቱም ቡድኖች የጠራ ሙከራ በቀሩት ደቂቃዎች ሳያደርጉ ወደ መልበሻ ክፍል ያለ ግብ አምርተዋል።
በሁለተኛውም አጋማሽ አርባምንጭ ፈጣን ጥቃት በካፓይቶ አማካኝነት በመሰንዘር ቡናን አስደንግጧል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አዞዎቹ የሚገባቸውን መሪነት አግኝተዋል። በዚህም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ የቡናን ተካላካዮች የአቋቋም ስህተት ተከትሎ ራሱን ነፃ አድርጎ የወጣው ካፓይቶ በደረቱ ኳሱን ለበላይ አመቻችቶለት በላይ ኳስ እና መረብን አገናኝጓል። የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የጣሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃሩ ሻል ያለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም አንድም ሙከራ አልሰነዘሩም። በተቃራኒው የሚፈልጉትን ያገኙት አርባምንጮች የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን አከታትለው በማስገባት በራሳቸው ሜዳ ክፍተቶችን መዝጋት ላይ ትኩረት በመስጠት መጫወት ይዘዋል።
ጨዋታው ቀጥሎ አፈግፍገው ሲጫወቱ የነበሩት አርባምንጮች በ79ኛው ደቂቃ በሙና አማካኝነት መሪነታቸውን ሊያሳድጉ ነበር። በሁሉም የሜዳ ክፍሎች እጅግ ተበልጠው የታዩት ቡናዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር መልሰው ሲያስረክቡ ታይቷል። ቡድኑም በተደጋጋሚ ራሱን ለአደጋ እየጋበዘ ስህተቶችን ማረም ሳይችል ጨዋታው ከብዶት ተስተውሏል። በጨዋታውም አንድም ሙከራ ሳያደረግ ወጥቷል። ጨዋታውንም በበላይ ብቸኛ ግብ አርባምንጭ አሸናፊ ሆኗል።
ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ድል ያደረጉት አርባምንጭ ከተማዎች ነጥባቸውን 16 በማድረስ ከነበሩበት 14ኛ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ቀድመው በሰበሰቡት 18 ነጥብ ያሉበት 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ቀጥለዋል።