ሪፖርት | ድሬዳዋ እና ባህር ዳር ነጥብ ተጋርተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በምሽቱ ጨዋታ የተሻሉ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ በመለያየት ደጋፊዎቻቸውን በድል ለመካስ የነበራቸው ውጥን ሳይሰምር ቀርቷል።

ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ከአርባምንጭ ከተማ አቻ ከተለያየው ስብስብ ብሩክ ቃልቦሬን እና አቤል ከበደን አስወጥተው በምትካቸው ዳንኤል ኃይሉ እና ማማዱ ሲዲቤን የመጀመሪያ ስብስባቸው አካል በማድረግ ሲጀምሩ በባህርዳር ከተማዎች በኩል ሀዋሳን ከረታው ስብስብ ሦስት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም አህመድ ረሺድ ፣ ፈቱዲን ጀማል እና አለልኝ አዘን አስወጥተው በምትካቸውም መናፍ ዐወል ፣ ግርማ ዲሳሳ እና ፍቅረሚካኤል ዓለሙን ተከትተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ባህር ዳር ከተማዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና የማጥቃት ፍላጎት ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን ፍፁም ዓለሙ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር በኩል ተደጋጋሚ የማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ሙከራ ሲያደርጉ ተመልክተናል። ነገር ግን በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ነገርግን በሂደት ወደ ጨዋታው መግባት የቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች የኃይል ሚዛኑን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩ ሲሆን የመጀመሪያውን አጋማሽ በበላይነት ማጠናቀቅ ችለዋል።

 

በዚህ ሂደትም በ23ኛው ደቂቃ ዐወት ገብረሚካኤል ሳጥን ውስጥ ደርሶ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት እንዲሁም በ30ኛው ደቂቃ ሄኖክ ኢሳያስ ከግራ መስመር ወደ ግብ የላካት እና ፋሲል ገብረሚካኤል ያዳነበት ኳስ ጨምሮ ዳንኤል ደምሴ በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ አከታትሎ ያደረጋቸው ሦስት ሙከራዎች በአጋማሹ የተመለከትናቸው የተሻሉ ሙከራዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ ክፍት ሆኖ በጀመረው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማዎች በቅብብሎች እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በፈጣን ሽግግሮች ወደ ተጋጣሚ የማጥቂያ ሲሶ መድረስ ቢችሉም የግብ ዕድሎችን በክፍት ጨዋታ ለመፍጠር ተቸግረው ተስውሏል። በአጋማሹ የተፈጠሩት የተሻሉ የግብ አጋጣሚዎች ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ከተመቱ ኳሶች የተገኙ ነበሩ።

በ60ኛው ደቂቃ አብዱረህማን ሙባረክ በግል ጥረቱ የነጠቀውን ኳስ ከመስመር ሰብሮ ወደ ውስጥ በመግባት በቀጥታ የላካት እንዲሁም በ64ኛው ደቂቃ ሙኸዲን ሙሳ ከሳጥን ውጪ በተመሳሳይ የመታው እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ በድሬዳዋ በኩል የተመለከትናቸው ሲሆን አለልኝ አዘነም እንዲሁ በባህር ዳር በኩል ተጠቃሽ ሙከራን ከሳጥን ውጪ ማድረግ ችሏል።

ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ፍለጋ አዎንታዊ ለውጦችን በማድረግ በቀሩት የሁለተኛው አጋማሽ ደቂቃዎች ጥረት ቢያደርጉም ውጤቱን መቀየር ግን አልተቻላቸውም። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግርማ ዲሳሳ አብዱለጢፍ መሀመድ ላይ በሰራው ጥፍት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ ይህን ተከትሎ ከተገኘው የቅጣት ምት ዳንኤል ኃይሉ ወደ ግብ የላካት ኳስ በግቡ አግዳሚን ጨርፋ ወደ ውጭ በመውጣቷ ጨዋታው 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ባህር ዳር ከተማዎች በ18 ነጥብ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ ድሬዳዋ ከተማዎች በ16 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።