​ሪፖርት | መከላከያ ድል አድርጓል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

መከላከለያ ከግሩም የመከላከል ትጋት ጋር በመጀመሪያ አጋማሽ ያስቆጠራትን ግብ አስጠብቆ አዳማ ከተማን በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።

ሁለት ቡድኖች በመጨረሻ ጨዋታ ከተጠቀሙባቸው የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ሁለት ሁለት ለውጥ ሲያደርጉ በአዳማ ከተማ በኩል ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ በቅጣት ምክንያት መሰለፍ ባልቻሉት ሚሊዮን ሰለሞን እና ዳዋ ሆቴሳ ምትክ አዲሱ ተስፋዬ እና አብዲሳ ጀማልን ሲያስገቡ በመከላከያዎች በኩል በወላይታ ድቻ ከተሸነፈው ቡድን ውስጥ ሰመረ ሀፍታይ እና ኢብራሂም መሀመድን አስወጥተው በምትካቸው አዲሱ አቱላ እና ኡኩቱ ኢማኑኤልን በመጀመሪያ ተሰላፊነት በማስጀመር ጨዋታውን አድርገዋል።

በቀጥተኛ አጨዋወት በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የመድረስ ፍላጎት ባላቸው ሁለት ቡድኖች መካከል በተደረገው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በዚህ ሂደት በተደጋጋሚ ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። 

አወዛጋቢ የነበሩ የዳኝነት ውሳኔዎችን ከመጀመሪያ ደቂቃ አንስቶ ያስተናገደው ጨዋታው በ1ኛው ደቂቃ ግሩም ሀጎስ ከቅጣት ምት ከተሻማ ኳስ ያስቆጠራት ግብ እንዲሁም ከደቂቃዎች በኋላ በቅድሚያ በእጅ የተነካን ኳስ ካስቀጠሉ በኋላ የነበረውን የተሾመ በላቸው የፍፁም ቅጣት ምት አጋጣሚዎች አነጋጋሪ ነበሩ። ያም ሆኖ በ11ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያዎች በብሩክ ሰሙ አማካኝነት ከቀኝ መስመር ያሻሙትን የቆመ ኳስ ጀማል ጣሰው በሚገባ መቆጣጠር ባለመቻሉ የተገኘችውን ኳስ አዲሱ አቱላ በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ ያደረችን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ አዳማ ከተማዎች በተወሰነ መልኩ ኳስ በመቆጣጠር እንዲሁም በመስመሮች በኩል ለማጥቃት ፍላጎት ቢኖራቸውም አብዲሳ ጀማል አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ያመከናት እንዲሁም በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ አዲስ ተስፋዬ ለጥቂት ወደ ውጭ ከወጣችበት የግንባር ኳስ ውጭ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በተቃራኒው መከላከያዎች ከጉዳት የተመለሰውን አጥቂያቸው ኡኩቱ ኢማኑኤልን ማዕከል ያደረጉ ተደጋጋሚ ረጃጅም ኳሶችን በመጣል ጥረት ቢያደረጉም በተለይ ከኳስ ውጭ ለመከላከል ያላቸው ታታሪነት አስደናቂ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ተጫዋቾችን ለውጠው የገቡት መከላከያዎች በአጋማሹ ይበልጥ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተስበው በጥንቃቄ ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ደግሞ የአቻነቷን ግብ ፍለጋ በቁጥር በርከት ብለው ለማጥቃት ጥረት ያደረጉበት አጋማሽ ነበር።

በክፍት ጨዋታ ተደጋጋሚ እድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት አዳማ ከተማዎች በ65ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ዮሐንስ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ የተመለሰችበት እንዲሁም እዮብ ማቲያስ ከግራ ያሻማውን ኳስ አሜ መሀመድ በግንባሩ ገጭቶ የሞከራት እና ለጥቂት ወደ ውጭ ከወጣችባቸው አጋጣሚ ውጭ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በመጀመሪያ አጋማሽ በተገኘችው ግብ የልባቸው የደረሰ የሚመስሉት መከላከያዎች በሁለተኛው አጋማሽ ፍፁም አስደናቂ ከነበረው የመከላከል አደረጀት ባለፈ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ይህ ነው የሚባል ፍላጎት አልተመለከትንባቸውም። 

ውጤቱን አስጠብቀው መውጣት የቻሉት መከላከያዎች ነጥባቸውን ከአዳማ ከተማ ጋር አስተካክለው ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ሽንፈት ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች ባሉበት 8ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።

ያጋሩ