የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከአልጄርያ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ከሰአታት በኋላ ወደ ስፍራው ያመራል፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሶስት አትቂዎቹን ባጣው ብሄራዊ ቡድን ግብ የማስቆጠር ትልቁ ሀላፊነት የተጣለበት የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶርያው አጥቂ ጌታነህ ከበደ ከአልጄርያ ጋር በተከታታይ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የአፍሪካ ዋንጫው እጣ ፈንታቸውን እንደሚወስን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል፡፡
‹‹ የብሄራዊ ቡድን ዝግጅታችን ጥሩ ነበር፡፡ በእርግጥ እኔ ቡድኑን የተቀላቀልኩት አርብ እለት ነው፡፡ በመጣሁበት እለት እረፍት አድርጌ ቅዳሜ እና ትላንት ልምምድ ሰርቻለሁ፡፡
‹‹ ሁለቱ ጨዋታዎች የእኛን ከ2017 የአፍሪካ ዋንጫ መውጣት አልያም መግባት የሚወስኑ ጨዋታዎች ናቸው፡፡ አልጄርያዎች ጠንካራ ናቸው፡፡ ሁለቱንም ጨዋታ አሸንፈው ሙሉ ነጥብ ማሳካት ይፈልጋሉ፡፡ እኛም አላማችን የተቻለንን ያህል ጥረት አድርገን ከሁለቱ ጨዋታ ነጥብ ለመውሰድ ነው፡፡ ›› የሚለው ጌታነህ ስለአልጄርያ ጥንካሬ ከሌላው የተለየ እይታ እንደሌለውም ጨምሮ ተናግሯል
‹‹ ሁላችንም እንደምናውቀው የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን እጅግ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን ነው፡፡ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ አስፈሪነቱን አስመስክሯል፡፡ ተጫዋቾቹም በአውሮፓ መድረክ የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ስለነሱ ጥንካሬ ከሌላው የተለየ ምልከታ አይኖረኝም፡፡››
ጌታነህ ቢድቬትስ ዊትስን ለቆ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶርያን ከተቀላቀለ በኋላ የመሰለፍ እድል ማግኘት ባይችልም አሰልጣኝ ሳሚ ትሮተን ለቀው የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድ ኮከብ ሾውን ባርትሌት ቡድኑን ከተረከበ በኋላ ጌታነህ የመሰለፍ እድል ማግኘት ችሏል፡፡ በቅርብ ሳምንታት ባደረጋቸው ጨዋታዎችም መልካም እንቅስቃሴ ከማድረጉ ባሻገር ግቦችን ማስቆጠርም ችሏል፡፡ ጌታነህ የቀድሞው አሰልጣኝ ለነባር ተጫወቾች የነበረው ትኩረት የመሰለፍ እድል እንዳያገኝ እንዳደረገው ይናገራል፡፡
‹‹ ቡድኑን እንደተቀላቀልኩ የነበረው አሰልጣኝ ከቡድኑ ጋር ረጅም ጊዜ የቆየ ነበር፡፡ ክለቡን ከታችኛው ዲቪዝዮን ያሳደገው እርሱ ነበር፡፡ በቡድኑ ውስጥ ለቆዩት ነባር ተጫዋቾች ነው ትኩረት የሚሰጠው፡፡ በዚህ ምክንያት እድል ባለማግኘቴ እንጂ ሁልጊዜ ልምምዴን ጠንክሬ እሰራለሁ፡፡ አሁንም ጠንክሬ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ሾን ባርትሌት አሰልጣኝነቱን ከተረከበ በኋላ ግን የመሰለፍ እድል እያገኘሁ እገኛለሁ፡፡››
ብሄራዊ ቡድኑ ከመቼው ጊዜ በባሰ መልኩ የአጥቂዎች እጥረት ያጋጠጠመበር ወቅት ላይ ደርሷል፡፡ ሙሉአለም ጥላሁን ፣ ታፈሰ ተስፋዬ እና ሳላዲን ሰኢድ ከቡድኑ ውጪ ከሆኑ በኋላ በስብስቡ የቀሩት ብቸኛ አጥቂዎች ዳዊት እና ጌታነህ ብቻ ሆነዋል፡፡ ይህም ጫና እንደሚፈጥርባቸው ጌታነህ ያምናል፡፡
‹‹ከኛ ብዙ እንደሚጠበቅ እርግጥ ነው፡፡ ሌሎች ብሄራዊ ቡድኖች ስበስብ ውስጥ 4 እና 5 አጥቂዎች ይኖራሉ፡፡ በኛ ቡድን ውስጥ የምንገኘው የፊት አጥቂዎች ግን ዳዊት እና እኔ ብቻ ነን፡፡ የታፈሰ ፣ ሳላዲን እና ሙሉአለም አለመኖር ቡድኑ ፊት መስመር ላይ እንዲሳሳ ያደርገዋል፡፡ ያ ደግሞ ከኛ ብዙ እንዲጠበቅ የሚያደርግ በመሆኑ በጣም ጫና ይፈጥርብናል፡፡ ›› ሲል በ2005 የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ በጋራ 43 ግቦች ካስቆጠረው የሁለቱ ጥምረት ብዙ እንደሚጠበቅ ተናግሯል፡፡