​የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-1 መከላከያ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

መከላከያ አዳማ ላይ ሦስት ነጥብ ካገኘበት የምሽቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ – መከላከያ

ስለ ጨዋታው…?

ያው የምንፈልገው ነው፡፡ የውጤት ጨዋታ ነው። በአሁኑ ሰዓት የምንጫወተው የቡድኑን ደረጃ ከፍ ለማድረግ የምትወጣበት ስለሆነ ቅድም የጠየከኝ ጥያቄ መልስ እያገኘ ነው። ወጣቶች እያገቡ ነው። ስለዚህ በወጣቶች አሁንም እቀጥላለሁ። ነባሮቹ ደግሞ ያለውን አስጠብቆ ለመውጣት እንደ እነ አሌክስ ፣ቢኒያም አይነቱ በመምራት ወጣቶቹ ደግሞ በምንፈልገው ጊዜ ስራ ይሰሩልናል፡፡ጨወታው ያምራል አያምርም ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ሦስት ነጥብ አግኝተናል፡፡

በጨዋታው ስለ ምታሳየው አካላዊ ገፅታ…?

የጨዋታው አንድ አካል ነው፡፡እንቅስቃሴዎች ከምን ጋር የሚገናኝ ነው ነጥቡን ከመፈለግ ውጤቱን ከመፈለግ የመጣ ነው፡፡ ነጥቡን ከመፈለግ ውጤቱን ከመፈለግ የምታመጣቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ዮርዳኖስ በአሰራራችን ጨዋታ ይመራል እኔ ልምምድ እመራለሁ። ግን አንዳንድ ነገሮች ላይ ከኋላ ሆነህ ከዮርዳኖስ የተሻለ ስለምታይ ነጥቡን በመፈለግ የምረዳው ዮርዳኖስን ነው። የምትረዳው በእዛን ሰአት እሱ ያላያቸውን ነገር እኔ ከኋላ ስለሆንኩኝ ማየት ስለምችል ያንን ለማድረግ ነው። ዞሮ ዞሮ ነጥቡን ለመፈለግ የምናደርጋቸው ናቸው፡፡

አሰልጣኝ ፋሲል ተካለኝ – አዳማ ከተማ 

የሽንፈቱ ምክንያት…?

በመጀመሪያ ተጋጣሚያችን ሦስት ነጥብ ስላገኘ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ከዛ ውጪ የግል ስህተቶቻችን እና በመጀመሪያው አስር አስራ አምስት ደቂቃ የምንሰራቸው የትኩረት ማነስ እሰካላሻሻልን ድረስ አስቸጋሪ እየሆነብን ነው የሚመጣው። ጎሉ ከገባብን በኋላ ተጋጣሚያችን ወደ ኋላ ገፍቶ እንደሚከላከል ከመጀመሪያውም ገምተናል፡፡ ቦታዎች ከዳር እና ዳር ነው ያሉት ያንን ለመጠቀም ነው የሞከርነው። ግን የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ ኳሶቻችን ልክ ስላልነበሩ የምንፈልገው ውጤት ማግኘት አልቻልንም፡፡

የግል ስህተቶች በቀጣይ ጨዋታ ቅያሪ ሊያስከትሉ ይችላሉ?

እሱ ዛሬ ላይ ሆኜ መናገር አልችልም። ግን የግል ስህተቶችን በቡድን ውስጥ ነው ማየት የምፈልገው። የግል ስህቶችን ስትቀንስ ቡድን ከፍ ይላል። እንደ ቡድንስ ደግሞ ምን እያደረግን ነበር የሚለውን በደንብ እናያለን። በሁሉም መልኩ ብልጫ ነበረን። ሜዳ ላይ ውጤቱም ይገባናል ብዬ አላስብም። ዞሮ ዞሮ እግር ኳስ ነው፡፡

የዳዋ እና የሚሊዮን አለመኖር ጉዳቱ ምን ድረስ ነው?

ምንም ጥያቄ የለውም እስከ አሁን በነበሩ ጨዋታዎቻችን የመጀመሪያ ምርጫዎቻችን ናቸው። ያላቸው የግል ችሎታ እና ልምድ ቡድናችንን ይጠቅም እንደ ነበር መናገር ግልፅ ነው፡፡ግን ዞሮ ዞሮ ሜዳ ላይ ያስገባነው ቡድን ይሄን ጨዋታ ለማሸነፍ በቂ አቅም ነበረው ብዬ ነው የማስበው። ያው ስህተቶቻችን መቀነስ ነው ለቀጣይ ጨዋታ ራሳችንን እናዘጋጃለን፡፡

ያጋሩ