​ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ጅማ አባጅፋር

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በ15 ነጥቦች እና በ11 ደረጃዎች ተለያይተው አራተኛ እና አስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ድቻ እና ጅማ የሚያደርጉት ጨዋታ እንዲህ ተቃኝቷል።

ከሦስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ድል ያደረገው ወላይታ ድቻ በአሸናፊነት በመዝለቅ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ነጥቡን የሚያሳድግበትን ሦስት ነጥብ ማግኘትን እያለመ ጨዋታውን ይጀምራል።

በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ ከተረታ በኋላ ለተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሳይሸነፍ ተጉዞ የነበረው ድቻ በመቀጠል በአንፃራዊነት በሊጉ ጠንካራ ቡድኖችን ሲያገኝ የአሸናፊነት መንገዱ ተደነቃቅፎ ነበር። ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ግን አጥቶት የነበረውን ሦስት ነጥብ ሦስት ጊዜ የራሱ አድርጎ ጥሩ ብቃቱን ያገኘ ይመስላል። ከኳስ ጋር ጊዜን በማሳለፍም ሆነ ያለ ኳስ ዘለግ ያሉ ደቂቃዎችን በመግፋት ቀጥተኛ አጨዋወትን በመከተል የጨዋታዎችን የሀይል ሚዛን ወደ ራሱ ለማድረግ የሚጥረው ድቻ ባሳለፍነው ሳምንት መከላከያን በአንተነህ ጉግሳ ግብ ሲረታ ተለዋዋጭ አቀራተብ በመከተል ለተጋጣሚ የማይመች ሆኖ ታይቷል። በወሳኝ የጨዋታ ምዕራፎችም ብልጫን በመውሰድ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ወጥቷል። በዋናነት ደግሞ ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረጉ ሽግግሮችን እና የቆሙ ኳሶችን እንደ ዋነኛ ግብ ማግኛ መሳሪያ በመጠቀም ሲንቀሳቀሱ እና ፍሬያማ ሲሆኑ ተስተውሏል። ነገም በተመሳሳይ የጨዋታ ሀሳብ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ሲጠበቅ ኳሱን ለተጋጣሚ ሰጥተው በረጃጅም ኳሶች ቁመታሙን አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱን እና ፈጣኖቹን የመስመር አጥቂዎች ያማከለ የማጥቃት እንቅስቃሴን በመከተል ጅማን ለማስጨነቅ እንደሚጥሩ ይታሰባል።

ከዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ከድል ጋር ታርቀው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን አሸንፈው የነበረው ጅማ አባጅፋሮች ባሳለፍነው ሳምንት ከገጠማቸው ሽንፈት በማገገም ዳግም ሦስት ነጥብ ለማግኘት ነገ ጠንክረው ወደሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል።

በሊጉ ጥቂት ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረ የመጀመሪያው ክለብ የሆነው ጅማ አባጅፋር ካከናወናቸው 13 ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። ይህ በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች (በራሱ እና በተጋጣሚ) ድክመት እንዳለበት ያመላክታል። የተለያዩ ጥምረቶችን በኋላ መስመሩ ላይ ሲያስመለክት የነበረው ቡድኑም አሁን ላይ ኢያሱ እና የአብስራን በቦታው ላይ ቀዳሚ ተመራጭ ያደረገ ይመስላል። ይህ ቢሆንም ግን በአስራ ሁለት ጨዋታዎች አስራ ሁለት የግብ ዕዳ ያለበት ስብስቡም በቶሎ ከወራጅ ቀጠናው ለማውጣት ግቦችን እያስተናገደ መዝለቅ አይገባውም። በተቃራኒውም ግቦችን እያስቆጠረ ጨዋታዎችን መወሰን ይጠበቅበታል። ኳስን ለመቆጠቀጠር የሚመቹ አማካዮች ያሉት ጅማ በፍጥነት የተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ እየተገኘ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር አቅሙ እምብዛም ነው። እርግጥ ፈጣን አጥቂዎች ቢኖሩትም ቡድኑ በቁጥር በዝቶ የመጨረሻው የሜዳ ሲሶ ላይ ስለማይገኝ ከወገብ በላይ መባከን ይስተዋልበታል። ይህ ቢሆንም ግን ጥሩ ብቃታቸው ላይ ያሉ የሚመስለው መሐመድኑር እና እዮብ ለወላይታ ድቻዎች የራስ ምታት ሊሰጡ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ ወረድ ብሎ እንደሚከላከል የሚገመተውን የተጋጣሚ መረብ ለማግኘት ከሳጥን ውጪ በርካታ ሙከራዎችን ሊያደርግ ይችላል።

ከሳምንቱ መጀመሪያ አንስቶ በጅማ በኩል መነጋገሪያ የነበረው ጉዳይ የተጫዋቾች ልምምድ ማቆም ነበር። የወራት ደሞዝ አልተከፈለንም በሚል ሁሉም ተጫዋቾቹ ለሦስት ቀናት በአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ እየተመሩ ልምምድ አለመስራታቸው በነገው ጨዋታ ተፅዕኖ ሊያመጣ ይችላል። ተጫዋቾቹ ሁለት ቀን ልምምድ ባይሰሩም በሦስተኛው ቀን ለብቻቸው ልምምድ ከሰሩ በኋላ ጥያቄያቸው በከፊል ሲመለስ ትናንት እና ዛሬ መደበኛ ልምምዳቸውን ሰርተዋል።

ወላይታ ድቻ በነገው ጨዋታ አማካዩ እድሪስ ሰዒድን ከጉዳት እንደሚያገኝ ሲገለፅ የመስመር ተጫዋቹ ያሬድ ዳዊት ግን መጠነኛ ህመም ላይ በመሆኑ ከጨዋታው ውጪ ነው። ጅማ አባጅፋር በጉዳት እና በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች አለመኖሩ ሲመላከት ጉዳት ላይ የነበረው ቁመታሙ የግብ ዘብ አላዛር ማርቆስ ደግሞ አገግሞ ለጨዋታው ዝግጁ ነው ተብሏል።

ይህንን ጨዋታ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሐል አልቢትርነት ከረዳቶቹ ክንዴ ሙሴ እና ሙስጠፋ መኪ እንዲሁም አራተኛ ዳኛው ቴዎድሮስ ምትኩ ጋር በመሆን እንደሚመራው ታውቋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል። እኩል 2 ጊዜ ሲሸናነፉ በቀሪው ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ድቻ 8 ሲያስቆጥር ጅማ 6 አስቆጥሯል።


ግምታዊ አሠላለፍ


ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ወንድወሰን አሸናፊ

በረከት ወልደዮሐንስ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – አናጋው ባደግ

አዲስ ህንፃ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሐብታሙ ንጉሤ 

ቃልኪዳን ዘላለም – ስንታየሁ መንግስቱ – ምንይሉ ወንድሙ


ጅማ አባ ጅፋር (4-2-3-1)

አላዛር ማርቆስ

ወንድማገኝ ማርቆስ – እያሱ ለገሰ – የአብስራ ሙሉጌታ – ተስፋዬ መላኩ

መስዑድ መሐመድ – ዳዊት እስጢፋኖስ

ዱላ ሙላቱ – በላይ አባይነህ – እዮብ ዓለማየሁ

መሐመድኑር ናስር

ያጋሩ