[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
13ኛው ሳምንት በሚቋጭበት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
በሁለት የወቅታዊ ውጤት ፅንፍ ላይ የሚገኙት ሲዳማ እና ወልቂጤ በጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ቀን በየፊናቸው በሊጉ የሚኖራቸው የፉክክር ቦታ ላይ ትርጉም ያለውን ግጥሚያ ነገ ምሽት ላይ ያደርጋሉ። ከመጨረሻው ሽንፈቱ በኋላ ከአምስት ጨዋታዎች 11 ነጥቦችን ያሳካው ሲዳማ ቡና እየተሻሻለ አምስተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን ነገ ድል ከቀናው ነጥቡን ከ20 በላይ ያደረሰ አምስተኛው የሊጉ ክለብ በመሆን በፉክክሩ ውስጥ አንድ እርምጃ ይራመዳል። ውጤቱ ለወልቂጤ ከተማ ያለው ትርጉም ግን ከዚህም በላይ እጅግ ትኩረትን የሚስብ ነው። ቡድኑ ነገ ሙሉ ውጤት ካሳካ በቀጥታ ተጋጣሚው ወደያዘው አምስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችል እንዳለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ካገኘው ግን በወራጅ ቀጠናው አፋፍ 13ኛ ደረጃ ላይ ለመቅረት ይገደዳል።
ሲዳማ ቡና ሰሞንኛ መልካም ጉዞው እና በጅማ አባ ጅፋር ላይ በተዋጣለት የጨዋታ ዕቅድ ያሳካው ድል አልፎ ተርፎም ውጤቱ በዋንጫ ፉክልር ውስጥ የሚያሰጠው ቦታ በነገው ጨዋታ በከፍተኛ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ እንዲገባ ያደርገዋል። በዚህ ረገድ የተቀዛቀዘ መንፈስ ውስጥ ይገኝ የነበረው ወልቂጤ ከተማ ደግሞ እንደክለብ ያደረገው ለውጥ የተነሳሽነቱ ምንጭ ሊሆን ይችላል። ክለቡ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የመተካቱ ውሳኔ ምክንያቶች ዝርዝር እይታን ቢፈልጉም ቡድኖች መሰል የአሰልጣኝ ለውጦች ሲያደርጉ የሚታይባቸው ቅፅበታዊ መነሳሳት እና ሜዳ ላይ የሚያንፀባርቁት የጨዋታ ፍላጎት በሰራተኞቹ ቤትም የሚታይ ከሆነ ቢያንስ ለነገው ጨዋታ ሊያበረታቸው እንደሚችል ይታመናል።
ሜዳ ላይ ከሚኖረው እንቅስቃሴ አንፃር ጨዋታውን ስንመለከተው በአዲስ አሰልጣኝ እየተመራ ወደ ሜዳ የሚገባው ወልቂጤን መተንበይ ረስቸጋሪ ይሆናል። ነገር ግን አሰልጣኝ ተመስገን ከነበራቸው ውስን ቀናት አንፃር የቡድኑ መሰረታዊ መዋቅር እና የጨዋታ መንገድ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። ቡድኑ ምናልባት የተጨዋች ምርጫዎቹ ላይ ሽግሽጎችን ሊያደርግ ቢችልም በጊዮርጊሱ ጨዋታ በሦስት የኋላ ተከላካይዮች ከጀመረበት አኳኋን ከዛ በፊት ነጥቦች ወዳስገኘለት መንገድ እና የቡድን ቅርፅ በመመለስ ለኳስ ቁጥጥር ያደላ ፣ በመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ጥረት የሚታገዝ ወደ መሀል የጠበበ የአማካይ ቅርፅ ይዞ ለጨዋታው እንደሚቀርብ ይገመታል። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ከሊጉ ምርጥ የመከላከል መስመሮች አንዱ የነበረው ቡድን በአራት ጨዋታዎች 11 ግቦችን ያስተናገደበትን ድክመት ነገ አለመድገም ትልቁ የቤት ስራው ይሆናል።
በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ ሲዳማ ቡና በማጥቃቱ ረገድ የነበሩት ጠንካራ ጎኖቹ በትክክል ለነገው ጨዋታ የሚተርፉ ናቸው። በእርግጥ በተጋጣሚው ዘንድ ያለው የአሰልጣኝ ለውጥ ወልቂጤ የሚመጣበትን መንገድ ለመገምት እክል ሊሆንበት ቢችልም የማጥቃት ጥንካሬዎቹን ማስቀጠል ግን አስፈላጊው ይሆናል። በተለይም ከሁለቱ አጥቂዎች ርቀው ይንቀሳቀሱ የነበሩ የቡድኑ ፈጣሪ አማካዮች ቡድኑ ከኳስ ጋር ሲሆን አሻራቸውን ማሳረፍ የሚችሉበት የሜዳ ክፍል ላይ መገኘት መቻላቸው በጅማው ጨዋታ የታየ ጥሩ ጎኑ ነበር። ወልቂጤም የጥሩ አማካዮች ባለቤት እንደመሆኑ ሲዳማ መሀል ሜዳ ላይ በጅማው ጨዋታ የተገበረውን በመስመር ተከላካዮቹ ተሳትፎ የጎለበተ እና ለአጥቂዎቹ የመጨረሻ ዕድሎችን የሚፈጥር የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ መድገም ውጤትን ሊያስገኝለት ይችላል።
ሲዳማ ቡና ተከላካዩ ጊት ጋትጉት በልምምድ ላይ ገጥሞት ከነበረው ጉዳት ሲያገግምለት ሰለሞን ሀብቴ ግን ለጨዋታው ብቁ አይደለም። በወልቂጤ ከተማ በኩል ከዮናስ በርታ ቅጣት ሌላ ያለውን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም።
ተፈሪ አለባቸው የሳምንቱን የመጨረሻ ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ለመምራት ሲመደቡ ረዳቶቻቸው
ዳንኤል ጥበቡ እና ወጋየሁ አየለ አራተኛ ዳኛ ደግሞ ሊዲያ ታፈሰ በመሆን ተሰይመዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በተገናኙባቸው የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ዓምና ሲዳማ ቡና በሁለቱም ዙሮች ዳዊት ተፈራ ባስቆጠራቸው የፍፁም ቅጣት ምት ግቦች በተመሳሳይ የ1-0 ውጤት አሸንፏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሲዳማ ቡና (4-4-2) ዳይመንድ
ተክለማርያም ሻንቆ
አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትጉት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና
ሙሉዓለም መስፍን
ቴዎድሮስ ታፈሰ – ዳዊት ተፈራ
ፍሬው ሰለሞን
ሀብታሙ ገዛኸኝ – ይገዙ ቦጋለ
ወልቂጤ ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)
ሰዒድ ሀብታሙ
ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ
ሀብታሙ ሸዋለም
ያሬድ ታደሰ – በኃይሉ ተሻገር
አብዱልከሪም ወርቁ
ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ