[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ወላይታ ድቻ እና ጅማ አባጅፋር ያደረጉት ጨዋታ እዮብ ዓለማየሁ የቀድሞ ቡድኑ ላይ ባስቆጠረው ግብ ጅማን አሸናፊ አድርጓል።
ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ለዛሬው ጨዋታ የተዘጋጁት ወላይታ ድቻዎች ባሳለፍነው ሳምንት መከላከያን አንድ ለምንም ከረቱበት ጨዋታ መጠነኛ ህመም ያጋጠመው ያሬድ ዳዊትን ብቻ በምንይሉ ወንድሙ ተክተዋል። ከሁለት ድሎች በኋላ በ12ኛ ሳምንት በሲዳማ ቡና ሁለት ለባዶ የተረቱት ጅማ አባጅፋሮች በበኩላቸው ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ የግብ ዘቡ አላዛር ማርቆስን በዮሐንስ በዛብህ፣ አዛህሪ አልመሃዲን በዱላ ሙላቱ እንዲሁም ዳዊት ፍቃዱን በተስፋዬ መላኩ ምትክ በመጀመሪያ አሰላለፍ አስገብተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ገና ከጅምሩ ቀልብን መሳብ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን የሚደረግ ምልልስ ተስተውሎበታል። በ2ኛው ደቂቃ ወላይታ ድቻ በአዲስ ህንፃ የቅጣት ምት የመጀመሪያ ጥቃት ሲፈፅም ጅማ አባጅፋር ደግሞ በ5 እና 6ኛው ደቂቃ በጥሩ የኳስ ፍሰት በመስዑድ መሐመድ እና መሐመድኑር ናስር አማካኝነት ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ጥሯል። ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም የጅማን የግብ ክልል መጎብኘት የያዙት ድቻዎች በ16ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ አጨዋወት እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም በረጅሙ የተላከውን ኳስ ስንታየሁ በግንባሩ ሁለተኛ ኳስ ሲያመቻች ተከላካዩ ኢያሱ ለገሰ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ቃልኪዳን ቢያገኘውም ግብ ጠባቂው አላዓዛር የአጋሩን ስህተት አርሞለት ዕድሉ መክኗል።
በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ጅማዎች ቀስ በቀስ ወረድ ያለ እንቅስቃሴ ማስመልከት ጀምረው ጫናዎች በርክቶባቸዋል። በ19ኛው ደቂቃም ምንይሉ ከቀኝ መስመር የሞከረውን ኳስ ተከላካዮች ሲመልሱት ስንታየሁ አግኝቶት በድጋሜ ወደ ግብ ልኮት የነበረ ቢሆንም አላዛር ኳሱን አክሽፎታል። ድንቅ ድንቅ ኳሶችን በማምከን ቡድኑን በጨዋታው እንዲቆይ ያደረገው አላዛር በ22ኛው ደቂቃ ቃልኪዳን ከቀኝ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ተገኝቶ የሞከረውን ኳስም ከግብነት ታድጎታል።
ኳሱን ለድቻ የተውት ጅማዎች በ35ኛው ደቂቃ እጅግ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሰንዝረው ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም መሐመድኑር ከመስዑድ የተላከውን ኳስ በግራ መስመር ፈጥኖ በማግኘት ራሱን ነፃ አድርጎ ለቆመው እዮብ ዓለማየሁ አቀብሎት እዮብ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። በጥሩ ታታሪነት በመጫወት መሪ የሆኑት ጅማዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት በአምበላቸው መስዑድ ቮሊ ሙከራ መሪነታቸውን ለማሳደግ ሞክረዋል። በቀሪ ደቂቃዎች ሌላ ሙከራ ሳይስተናገድ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ጅማ በአስገዳጅ ሁኔታ አጥቂውን ሲለውጥ ድቻ ደግሞ ጨዋታውን ለመቆጣጠር አማካይ ወደ ጨዋታው አስገብቷል። በተለይ ድቻ የኳስ ቁጥጥሩን በዓላማ ሦስተኛው ሜዳ ላይ ለማድረስ ሞክሯል። መሪዎቹ ጅማዎች ደግሞ ግብ ያገኙበትን የመልሶ ማጥቃት እየጠበቁ ጨዋታውን ቀጥለዋል። እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያሉ ሙከራዎችን ከማስተናገድ የተቆጠበው ይህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እስከ 70ኛው ደቂቃ ድረስ የጠራ ዕድል አልታየበትም። በተጠቀሰው ደቂቃም አናጋው ባደግ ፈጣን የመስመር ላይ ሩጫ በማድረግ ከስንታየሁ የደረሰውን ኳስ ከመረብ ጋር ለመዋሀድ ጥሮ ነበር። ይህ ሙከራ በግብ ጠባቂው ወደ ውጪ መውጣቱን ተከትሎ የተገኘውን የመዓዘን ምትም ቁመታሙ ተከላካይ በረከት ለመጠቀም ዳድቶ ወጥቶበታል።
በተደጋጋሚ የማጥቃት ሲሶ ላይ እየደረሰ የሚገኘው አናጋው በ79ኛው ደቂቃ ሌላ ሙከራ አድርጎ ቡድኑን አቻ ለማድረግ ጥሯል። ጅማ አባጅፋር ቀሪ ደቂቃዎችን በመከላከል ቅርፅ በመሆን ቀድሞ ያገኘውን አንድ ግብ እንደምንም አስጠብቆ ወጥቷል። የአሠልጣኝ ፀጋዬ ተጫዋቾች በበኩላቸው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከፍተኛ ጫና ቢፈጥሩም ፍሬያማ ሳይሆኑ እጅ ሰጥተው ጨዋታው ተገባዷል።
የውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ድላቸውን ያገኙት ጅማ አባጅፋሮች ከወራጅ ቀጠናው ባይወጡም ነጥባቸውን 10 አድርሰዋል። እስከ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድል የነበራቸው ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ሽንፈቱን ተከትሎ በ22 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ቀጥለዋል።