አፄዎቹ የቀድሞው አጥቂያቸውን በድጋሚ አግኝተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከሳምንታት በፊት ከአልጄሪያው ክለብ ጋር የተለያየው አጥቂው ሙጂብ ቃሲም ወደ ፋሲል ከነማ መመለሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ያለፉትን ሁለት ዓመታት ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደመቀው የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ተጫዋች አጥቂው ሙጂብ ቃሲም በ2011 የውድድር ዘመን አዳማ ከተማን ከለቀቀ በኋላ ፋሲል ከነማን ተቀላቅሎ እስከ ተጠናናቀቀው የውድድር ዓመት ድረስ በክለቡ ቆይታ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ሽግግር ካደረገ በኋላ በፋሲል ከነማ በተደጋጋሚ በሚያስቆጥራቸው ግቦቹ ስሙ የገነነው ግዙፉ አጥቂ በያዝነው ዓመት መስከረም ወር ላይ የአልጄሪያውን ክለብ ጄ ኤ ስ ካቢሌን በሦስት ዓመት ውል ተቀላቅሎም ነበር። ሆኖም የአምስት ወራት የደመወዝ ክፍያ አለማግኘቱን ተከትሎ ከአስር ቀናቶች በፊት ከክለቡ ጋር በመለያየት የቀረው ደመወዝ እንዲከፈለው ጉዳዩን ወደ ፊፋ በመውሰድ ወደ ሀገሩ መመለሱ የሚታወስ ነው። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችሁ መረጃ መሠረት ደግሞ አጥቂው በነገው ዕለት ወደ ድሬዳዋ ካመራ በኋላ እስከ ሰኔ 30 2014 ድረስ በፋሲል ከነማ ለመጫወት በመስማማት የመጀመሪያ ልምምዱን የሚያደርግ ይሆናል፡፡