አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ አስገብተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በአሁኑ ሰዓት በሥራ ገበታቸው ላይ የማይገኙት የሰበታ ከተማው አሠልጣኝ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ ማስገባታቸውን አውቀናል።

ከወራት በፊት ሰበታ ከተማን ለሦስት ዓመታት ለማሰልጠን ፊርማ አኑረው ሥራቸውን እየከወኑ የሚገኙት አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከሁለት ቀናት በፊት በክለቡ አመራሮች ጥሪ ቀርቦላቸው ከድሬዳዋ ወደ ሰበታ ጉዞ እንዳደረጉ ዘግበን ነበር። በጥሪው መሠረትም አሠልጣኙ ከክለቡ ፕሬዝዳንት ጋር ውይይት አድርገዋል። በከፍተኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ክለቡም ከአሠልጣኙ ጋር ያለውን ጉዳይ በተመለከተ እስካሁን በይፋ ያወጣው ነገር የሌለ ሲሆን ለአሠልጣኙም ምንም ነገር አልገለፀም። ይህንን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት ከቡድኑ ጋር የማይገኙት አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በወከሏቸው የሕግ አማካሪ ጠበቃ እና የእግርኳስ ስፖርትኞች ሕጋዊ ወኪል አቶ ብርሃኑ አማካኝነት በዛሬው ዕለት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

አሠልጣኙ ከክለቡ ጋር ያላቸውን ውል ገልፀው በፃፉት ደብዳቤ ሪፖርት እንዲያቀርቡ በተላለፈላቸው ጥሪ መሠረት ወደ ሰበታ ተጉዘው ሪፖርት ሲያቀርቡ የክለቡ ፕሬዝዳንት በቃል ለጊዜው የማልሰራ መሆኑን ነግረውኛል የሚል ሀሳብ አስፍረዋል። ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ በውሌ መሠረት የሥራ ግዴታዬን እንድወጣ ውሳኔ ይስጠኝ የሚል አቤቱታ አስገብተዋል።

የአሠልጣኙ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ በክለቡ በኩል የተያዘውን አቋም ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ይፋዊ መረጃ በማግኘት አልተጠናቀቀም። ዝምታን የመረጠው ክለቡም ነገ እና ከነገ በስትያ አዲስ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

በተያያዘ ዜና ክረምት ላይ የክለቡ ምክትል አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም ለሳምንታት ከክለቡ ጋር ከተለያዩ በኋላ ከትናንት በስትያ ወደ ድሬዳዋ አምርተው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ቢደረግም አሠልጣኙ ድሬዳዋ ከደረሱ በኋላ ዳግም ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ ሰምተናል። አሠልጣኙ የዘላለም ከቦታው ለጊዜው መነሳት እና እርሳቸው ከክለቡ እንዲርቁ የተደረገበት ምክንያት ቀድሞ እስካልተገለፀላቸው ድረስ ስራውን ላለመከወን አቋም እንደያዙ አውቀናል።