በ2016 የኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ በኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 ተሸንፈው ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ወላይታ ድቻዎች የብር ሜዳሊያ ሽልማታቸውን ሳይቀበሉ ከስታዲየም ወጥተዋል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፣ ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ በሚሳተፉ 46 ቡድኖች መካከል የተካሄደው የኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ ፍጻሜውን ሲያገኝ ኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 በሆነ ውጤት ወላይታ ድቻን በመርታት በታሪኩ ለ6ኛ ጊዜ ዋንጫውን ተቀዳጅቷል።
ጨዋታውን ወላይታ ድቻ በ53ኛ ደቂቃ የአበባየሁ ሀጂሶ ጎል መምራት ቢችልም ቡናማዎቹ 67ኛው ደቂቃ ላይ በዋሳዋ ጄኦፍሪ የፍጹም ቅጣት ምት ጎል አቻ ሆነው መደበኛው ክፍለጊዜ 1-1 ተጠናቆ በተጨመሩ 30 ደቂቃዎች ውስጥ 116ኛው ደቂቃ ላይ ዋሳዋ ጄኦፍሪ ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛ የፍጹም ቅጣት ምት ጎል አስቆጥሮ ቡናማዎቹ ቻምፒዮን ሆነዋል።
ጨዋታው ተጠናቆ የሽልማት መርሐግብሩ ቢጀመርም በዳኝነቱ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ የነበራቸው ወላይታ ድቻዎች የብር ሜዳሊያ እንዲወስዱ ቢጠየቁም ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።